ይኸነው ዓለሙ
ህዳር 18 2013
ኢትዮጵያዊያን ረከስን፣ በዓለም ዙሪያ ማንም እንደፈለገ የሚዘግነን ሆንን፣ ራሳችንን ለመከላከል የማንችል፤ ስለ እኛም ቆሞ የሚከራከርንል ያጣን ምስኪን ሕዝቦች ሆንን። በሀገራችን ሳይቀር ያሰብነውን ለመከወን አቅም የሌለን፣ አቅጣጫ ጠቋሚ ኮምፓሳችንን የተነጠቅን፤ የጉዞ መቆጣጠሪያ መሪያችንን ያስረከብን ምስኪን ሕዝቦች። ባቅራቢያችን ባካባቢያችን የተፈጠረውን ለኛ ምቹ ያልሆነ ድርጊት ለመቆጣጠር መወያየትና መተባበር የተሳነን፤ ሽሽትን፣ ስደትን ሩጫን እንደ ብቸኛ አማራጭ የተቀበልን ምስኪን ሕዝቦች። በተለይ በፋሽስት ወያኔ ዘመን ረከሱ ሳይሆን ዋጋ አጡ መባል የሚገባን ምስኪን ሕዝቦች። ወያኔዎች ካንደኛው ችግር ወደ ሌላው፣ ከቀዳሚው መከራ ወደ ቀጣዩ እንደፈለጉ ሲያገለባብጡን ለምን ብለን መጠየቅ ያቃተን፤ እሽን ብቻ የተካንን ምስኪን ሕዝቦች። ፋሽስት ወያኔ ልጆቻችንን፣ ባለቤቶቻችንን፣ ወገኖቻችንን ባደባባይ በጠራራ ፀሐይ ዐይናችን እያየ በሕዝብ ፊት በጥይት ሲደፋቸው እያየን ”ሲያልፍ ያልፋል እስኪያልፍ ያለፋል” እያልን አንድም ቀን ሳይልፍልን እኛ ቀድመን በማለፍ ላይ የምንገኝ ምስኪን ሕዝቦች። ኢትየጵያኒዝም የተሰኘ የአሸናፊነት መንፈስ በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ በነበሩ አፍሪካዊያን ወገኖቻችን፣ በላቲን አሜሪካና የሰሜን አሜሪካ ጥቁር ሕዝቦች ደም ውስጥ እንዲንተከተክ ምክንያት እንዳልነበርን፤ ዛሬ በፋሽስት ወያኔ ዘመን ግን ያንን መንፈስ የምንናፍቅ፣ እንዲያጋሩን የምንሻ አሳዛኝ ሕዝቦች ሆነናል። Read the rest of this entry »