RSS

ለምን ይህን መረጠ – 1

27 Jun

ሰኔ 27  2014

በታላቁ መጽሐፍ ባንድ ቦታ ”እናንተ እንኳን ዝም ብትሉ ድንጋዮች አፍ አውጥተው ያመሰግኑኛል” የሚል ታላቅ መልእክት የያዘ ሃሳብ ትዝ ይለኛል። ሃይማኖታዊ ትንታኔውን ለጊዜው ወደ ጎን ትተን ጥቅል ሃሰቡን በግርድፉ ለመመልከት ብንሞክር እንኳ ሁሉም ባንዴ ዝም አይልም፣ ፈሪ ባለበት ሁሉ ደፋርም አለ፣ ዝምተኛ ካለ ተናጋሪም አለ፣ የሚጠበቁት የተዉትን ያልተጠበቁት ያነሱታል እና ሌሎችንም ብዙ ሃሳቦችን የያዘ መሆኑን መዘርዘር እንችላለን።

ወያኔ እንደ ጠባብ ቡድንም ሆነ ወያኔዎች እንደ ግለሰብ ኢትዮጵያዊነት የሚሰማውን አንድ ድርጅት ወይም ጠንካራ ግለሰብ በማስወገድ ወይም በማዳከም ኢትዮጵያን የማፈራረስ ምኞታችንን እናሳካለን ብለው ያስባሉ። የኢትዮጵያዊነት ጠንካራ መንፈስ በደማቸው ውስጥ እየፈላና እንደ እሳተ ገሞራ ቅላጭ እየነተረ መላ ሰውነታቸውን የሚያንቀጠቅጣቸውን ኢትዮጵያዊያን በማስወገድ፣ በማጥፋት ወይም በማሰር ያን ከኢትዮጵያዊያን ልብና ደም በላይ ወጥቶ በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ሕብር አምሮ በኢትዮጵያ ሰማይ የረበበውን ሃያል የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ያጠፉና ፍላጎታቸውንም ያሳኩ ይመስላቸዋል። ለዛሬ ግን ሕወሃት በሃይማኖት ተቋማት ላይ እያደረሰው ካለው ጥቃት በመነሳት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ለምን እንደመረጠ በመመልከት እንጀምር።

ሕወሃት መራሹ ወያኔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ከቻለ ለማጥፋት ካልሆነም ለማዳከም ሲመርጥ ብዙ ጥናት ተብዬ ጥናቶችን አስጠንቶ እንደነበር ይነገራል። ኦርቶዶክስ ገና ከነገስታቱ ዘመን ጀምሮ በሀገሪቱ ሰፊ መሰረት ያለው ስለሆነ፣ በሁሉም የሀገሪቱ የማሕበረሰብ ክፍሎች በስፋት እንቅስቃሴ ያለው በመሆኑ፣ የሀገር አንድነትና ሉአላዊነት የሚሰበክበት ተቋም ከመሆኑም ባሻገር የነፃነትና የፍትህ ቦታ በመሆኑ ስለ ፍትህ ይሰበክበታል ተብሎ ስለታመነ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማሕበረሰብ ተከታዮች ያደረገ በመሆኑ፣ ሕዝብ የሚፈራቸው፣ የሚያከብራቸው እንዲሁም የሚታዘዛቸው ግለሰቦች ስብስብቦችን ያቀፈ በመሆኑና ሌሎችንም ታሳቢ በማድረግ ይህን ሃይማኖታዊ ተቋም ማጥፋት አልያም መቆጣጠር ቢቻል ወይም ከሕዝብ መነጠል ቢሳካ የኢትኦጵያዊነትንና የአንድነትን መንፈስ መስበር ይቻላል ብሎ ያምናል፤ ሕወሃት። ይሁን እንጅ ጠንካራው የኢትዮጵያ ሙስሊም ማሕበረሰብ፣ ሌሎች የክርስቲያን ወገኖችና ሃይማኖት ተከታይ ያልሆነው ኢትዮጵያዊ ክፍል ግን ብዙም ክብደት የተሰጠው አልነበረም።

በመሆኑም ፋሽስት ወያኔ ሀገራችንን ከተቆጣጠረበት ጠዋት ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ ዘመተ። በድርጊቱም ቤተክርስቲያኗ ራሷን ችላ እንዳትንቀሳቀስ ከማድረጉም በላይ ብዙ ተከታዮቿን አሰረ፣ ገረፈ፣ ገደለ አሰደደም። ቀሪዎችም ባሉበት እንዲፈዙና እኔ ምን አገባኝ እንዲሉ ብዙ ተሰራ። የክርስትናን ሃይማኖት ለመስበክ እግሮቻቸውን በሐዋሪያት ምሳሌ የተከሉት ጳጳሳት ሳይቀሩ ተገረፉ ተሰደዱ ተገደሉ። ስለሀገርና ወገን ዘግተው የሚጸልዩት ገዳማዊያንም ቀያቸው ተደፈረ፣ የክብር ድንበራቸው በወያኔ ተጣሰ። በቤተ ክርስቲያን አካባቢም ሆነ በሌላ ቦታ ለጳጳሳት፣ ለቀሳውስት፣ ለመነኮሳትና ለገዳማዊያን ስለ ሀገር አንድነትና ክብር፣ ስለ ወገንና ባንዲራ ፍቅር እንዲሁም ሰለመተባበርና መተጋገዝ መስበክ ከአሸባሪዎች ጎራ ከማሰለፉም በላይ የሞት ያህል እንዲፈራ ሕወሃት በርትቶ ሰራ። እናም ሕወሃቶች ይህን ከማንም በላይ ገኖ ከጩኸትም በላይ ጮሆ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ራእያችንን ያበላሻል ብለው የፈሩትን ኦርቶዶክስ የሚባል ጠንካራ ተቋም እንዳልነበር የማድረግ ጉዟቸውን በማፋጠን ላይ እንዳሉ፤ እናም ሕወሃቶች የዚህን ጠንካራ ሃይማኖታዊ ተቋም ተከታዮች በማዳከምና በማስፈራራት ላይ እንዳሉ ግን ሌላ የአንድነት፣ ሌላ የአልበገርም በይነት፣ ደግሞ ሌላ የአትንኩኝ ባይነት መንፈስ በሌላ በኩል ብቅ አለ። የአንድነትና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በሙሉ ኢትዮጵያና በኢትዮጵያን ላይ ሁሉ እንጅ በተወሰነ አካባቢና ለተወሰነው የማሕበረሰብ ክፍል ብቻ የተሰጠ እንዳልነበርም በገሃድ ታየ። አወ ግዙፍ የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት መንፈስ ወያኔ ብዙም ባልጠበቀው በሙስሊሙ ማሕበረሰብ በኩል ፈነዳ። ፋሽስት ወያኔ ትንኝነት እስኪሰማው ድረስ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች እጅግ እጅግ ገንነው ወጡ። ዛሬም አንድነት፣ ዛሬም ኢትዮጵያዊነት እንደገና ተዘመረ፤ ክብር ለኢትዮጵያ ይሁን።

ሲገረፉ፣ ሲደበደቡና ሲሳደዱ ይነሳሉ፣ አትንኩን ይላሉ ተብለው የተጠበቁት ኦርቶዶክሳዊያን ዝም ሲሉ ሌሎች ወንድሞች ጋሻ አነሱ። ”እናንተ ዝም ብትሉ እንኳ ድንጋዮች አፍ አውጥተው ያመሰግኑኛል” ማለት ይህ ነው። በኢትዮጵያዊያን ሙስሊም ወገኖቻችን የተነሳው ጋሻ ለወያኔ ፈተና ከመሆኑም ባሻገር ሀገር የቁሊት ታክል እንድትጠብበት አድርጓል። በመሆኑም ሕወሃት ከፈተና ወደ ፈተና ከችግር ወደ ችግር በመሸጋገር ላይም ይገኛል።

ከእንደዚህ አይነቱ የሕወሃት እንቅስቃሴ የምንገነዘበው ታላቅ እውነት ታዲያ፤ ወያኔ የሚጠነክረው፣ አንዱን ካንዱ በማጋጨት ወይም አንዱን ከሌላው ነጥሎ በማጥቃት መሆኑን ነው። ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ግን በመላ ሀገሪቱ እንደ ፀበል የተረጨው የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት ጠንካራ መንፈስ በደማችን እየተሯሯጠና እየተሰራጨ ባንዱ የደከመ የመሰለው ኢትዮጵያዊነት በሌላው ወገን እንደገና ገኖ እየወጣ ይኸው ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገን እንደዘመርን አለን። ዛሬም ሆነ ወደፊት የሕወሃት ጥቃት ሲዘነዘር ለምን ይህን ወይም ያን ለማጥቃት መረጠ? ብለን ስንጠይቅ እኛ እንደሰው እንዳልተቆጠርንና ሊተባበርና ሊረዳዳ እንደማይችል ግኡዝ ነገር የተቆጠርን መሆናችንን አንዘንጋ። በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት ተውቦ በሀገራችን ሰማይ ያረበበው የአትንኩኝ ባይነት፣ የመተሳሰብና የመረዳዳት ጠንካራ መንፈስ ያልፈነዳ እሳተ ገሞራ ሆኖ በውስጣችን እንደሚንቀሳቀስና ልባችንን እያቃጠለ እንዳለ እሙን ነው። ዛሬ ግን ታዲያ ሕወሃት እያናጠለ ሲመታን እንደፈለገ ሲያጋጨን ስናይ ይህ ያልፈመዳ እሳተገሞራ ሊፈነዳና አንዳችን ላንዳችን አለሁ ልንል ይገባል። የተጠበቁት ካልነቁ ያልተጠበቁት አለሁ እንዲሉ የግድ ነውና።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on June 27, 2014 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: