RSS

የግዳጅ ሰልፍ በማዘጋጀት ሀቅን መሸፈን አይቻልም

13 Apr

ሚያዚያ 13 2014

በመጀመሪያዎቹ የወያኔ የአገዛዝ ዘመን አካባቢ ሕወሃት ሕዝብን ለማሳመንና የተሻለ መስሎ ለማታየት እጅግ ብዙ ማስመሰያ ድራማዎችን ሲከውን እንደነበር የቅርብ ጊዜ የሀዘን ትዝታዎቻችን ናቸው። በጊዜው ምንም እንኳ በአብዛኛው የሀገራችን ሕዝብ ያልተነቃበት ቢሆንም ከምሁራን አካባቢና በተለይም የጨካ ዘመን ታሪኩን ብጥር አድርገው በሚያውቁት ግለሰቦችና ባንዳንድ ዓለማቀፍ ተቋማት ዘንድ በጥንቃቄ መታየቱ አልቀረም ነበር። በሗላ ላይ ግን የሚሰሩት ወንጀሎች አይነትና ብዛት እየበዛና በሕወሃት በኩል የሚቀርበው የሽፋን ስእላቸውም የድፍረት እና በግግምና ዝም ብላችሁ እመኑን አይነት እየሆነ ሲመጣ ግን ሁሉም ፋሽስት ወያኔ የውሸት ተዋናይ መሆኑን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን የትወና ታሪክና ዘንግ ሳይቀር መተንበይ ጀመረ። እናም ዛሬ ሕወሃት ለልቅሶ ሳይቀር ትወና አጥንቶና አስጠንቶ እስከማጭበርበር ድረስ ተዳፈረ።

በእርግጥ በፊትም የሃውዜንን ሕዝብ ራሱ ባቀነባበረው የጭካኔ ተግባር ካማስጨፍጨፉና ባዘጋጃቸው የካሜራ ሰዎች ከያቅጣጫው ጥቃቱን አስቀርጾ ለዓለም በማሰራጨት እሪታውን ከማሰማቱም በፊት ቢሆን ተመሳሳይ ድራማዎችን በትግራይና በሰሜን ወሎ አካባቢ በሚኖረው ሕዝባች ላይ በመፈጸም ኡ ኡ እኔ አይደለሁም ሲል እንደነበር ”ማን ያርዳ የቀበረ…” ነውና ድርጊቱን በመቃወም ወደ ህዝብ የተቀላቀሉ ጓዶቹ ማጋለጣቸው አይዘነጋም። እናም ሕወሃት ለሕዝብ ቆምኩ ብሎ ጠመንጃ ካነሳበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሕዝብ ላይ ሸፍጥ እንደሰራና ሕዝብን እንዳመሰ አለ። እኛም በግለሰብ ደረጃ እከሌ ጻፋቸው የማይባሉ በጣም ብዙ የሕወሃት የጥፋት ሽፋን ተውኔቶችን እንዳየን አለን።

አዲስ አበባን በመሳሰሉት ታላላቅ የሀገራችን ከተሞች ንጹሃን ዜጎቻችንን በማፈንና በመውሰድ ጠፍተዋል ብሎ ከባለጉዳይ ዘመዶች ጋር አብሮ ከመፈለግ ጀምሮ ፋሽስቱ ሕወሃት በጠራራ ፀሐይ በጥይት ደብድቦ ከገደለ በሗላ አስከሬኑ ላይ መሳሪያ በማስቀመጥ ስለተኮሰብን ገደልነው በማለት በፊልም የተቀነባበረ ዜና አዘጋጅቶ አስደምጦናል። ጠንከራ ተከራካሪ የነበሩ የማህበራት መሪዎችን በተቀነባበረ መንገድ በመኪና ጨፍልቆ ከገደለ በሗላ ድንገተኛ አደጋ አስመስሎ አሳይቶናል። አውርቶልናልም። ይሁን እንጅ ሃቁን ግን ሸፍኖ ሊያስቀረው አልቻለም።

ሕወሃት ትላንትም ሆነ ዛሬ ስልጣኔን ለማቆየት ይጠቅመኛል ብሎ እስካመነ ድረስ፣ እርዳታ ለማሰባሰብ ይረዳኛል ብሎ እስከገመተ ድረስ፣ ሌሎችን ጥሎ ለማለፍ አልያም እውቅና ለማግኘት አስፈላጊ መስሎ እስከታየው ድረስ እራሱ በከፍተኛ ዝግጅት የፈጸመውን ወንጀል እንደገና ሌላ ዘዴ በመፍጠር በሌሎች ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ላይ ለማመካኘት ያፍታ ጭንቅ እንኳ የማይሰማው የማፍያዎች ስብስብ ነው።

ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ለሀገር ልእልናና ለሕዝቦች አርነት የቆሙና በከፍተኛ ደረጃ የምናከብራቸውን ውድ ኢትዮጵያዊያን፤ ከሕወሃት ጋር ስላልተባበሩ ብቻ፣ የሕወሃት አካሄድ ኢዴሞክራሲያዊ መሆኑን ስላጋለጡ ብቻ፤ በዚህም በዚያም ብሎ ጠልፎ ለመጣል  ግንቦት 7ን ጨምሮ ኦነግና ኦብነግ ከሚባሉ የተቃውሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አላቸው በማለትና ይህንንም ሊያረጋግጥልን ይችላል ያሉትን ተውኔት ራሱ ሕወሃት በማዘጋጀትና ሆዳሞች እንዲተውኑት በማድረግ በወያኔው የውሸት ሬዲዮ እና ትሌቪዥን ጣቢያ በማሰራጨት ድራማ ሰርቷል። ይሁን እንጅ ትላንት ዛሬ እንዳልሆነ ሁሉ ሁሌ አሸሸ ገዳዎም የለም። ስለሆነም ሕወሃት በተከታታይ ይድከም እንጅ ሀቅን ሊሸፍንና ሕዝባችንን  ሊያሳምን ግን አልቻለም።

አሁን በቅርቡ በተከወነ የሕወሃት የውሸት ትእይንት ብንነሳ እንኳ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን ለመወንጀልና ዘብጥያ ለማውረድ ጅሃዳዊ ሃረካት የተሰኘ የተረት ተረት ጥርቅም ያሳየ ሲሆን የስዊድን ጋዜጠኞችንም ወንጅሎ ለማሰር አስቂኝ የሆነና ጋዜጠኞች የኦብነግ ሃይሎችን በመወከል ከሚሯሯጡ የወያኔ ወታደሮች ጋር አብረው እንዲሮጡ በማስገደድና ይህንኑ በቪዲዮ ቀርጾ በማሳየት ዓለምን አሞኛለሁ ብሎ ራሱ ሲቀል ተመልክተናል። የዚሁ ተመሳሳይና ቀጣይ የሆነውን ክፍል ነው እንግዲህ ሰሞኑን በሀረር ከተማ የተመለከትነው።

ሰሞኑን በሀረር ከተማ እንዳየነው ሕዝብ ችግር ሲያጋጥመው ጠሪ አያስፈልገውም። በራሱ መንገድ ይጠራራል። ተሰባስቦም ማድረግ ያለበትን በድብቅ ሳይሆን በተራራ ፀሐይ ያደርገዋል። በዚህ መንገድም በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ መሕበራዊ ጉዳዮችን በማንሳትና ሕወሃትን በመቃወም ሕዝብ አደባባይ ወጥቷል። ምንም እንኳ ለሕዝብ ጥያቄ ክብር የሌላቸው ሕወሃቶች መልሳቸው ቆመጥና ጥይት ቢሆንም ባራቱም የሀገራችን ማእዘናት ያለማንም ጎትጋች በሕወሃት ላይ የተነሱ ተቃውሞችን አይተናል እያየንም ነው።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት እንኳ የንግድ መደብራቸውን በማቃጠል ቦታቸውን በግፍ ለመንጠቅ የፈለጉ ሕወሃቶችና የህወሃት ጄሌዎች በሀረር ከተማ በሚገኙ የንግድ መደብሮች ላይ በተደጋጋሚ ቃጠሎ በመፈጸማቸው ሳቢያ ከልቡ የተቆጣው የሀረር ከተማ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ሕወሃትን በከፍተኛ ሁኔታ መቃወሙን ተከትሎ፤ ቃጠሎው የተከሰተው ጥንቃቄ በጎደላቸው የመደብሩ ባለቤቶች እንደሆነ ለማሳመንና የተወሰኑትንም የቃጠሎው ሰለባዎች ይህን ጉዳይ አምነው እኔ ነኝ ብለው እንዲፈርሙ ለማድረግ ሕወሃቶች እስከ እስር የደረሰ ሰቆቃ ቢፈጸሙም ባለመሳካቱና ቃጠሎውን ሕወሃቶችና ጄሌዎቻቸው እንደፈጸሙት ርግጠኛ የሆነውን የሀረርን ከተማ ሕዝብ ማሳመን ባለመቻሉ አጠቃላይ ስራ እስከማቆም የደረሰ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቷል።  ከዚህ ሁሉ ሙከራ በሗላ ግን ወያኔዎች እንደለመዱት ሕዝብን በማስፈራራትና በማስገደድ የውሸት ሰላማዊ ሰልፍ በማዘጋጀት ድርጊቱን የፈጸሙት ጸረ ሰላም ሃይሎች ናቸው ለማስባል መሞከራቸውን አይተናል። ይህም ቢሆን ታዲያ ሃቁን በሚያውቀው የሀረር ከተማ ሕዝብም ሆነ ሕወሃትን አሳምሮ በሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ፋሽስት ወያኔ ቅሌትን አተረፈለት እንጅ አልተጠቀመበትም። የግዳጅ ሰላማዊ ሰልፎችንና የውሸት የቅንብር ድራማዎችን በማዘጋጀትና ለሕዝብ በማቅረብም ሀቁን መሸፈን እንደማይቻል ሕወሃት ሰሞኑን በሀረር ከተማ ካዘጋጀው የግዳጅ ሰላማዊ ሰልፍና የህዝቡ እምነት እንዲሁም ካለፉት የወያኔ ቅሌቶች መገንዘብ ይቻላል።

ሕወሃት እስካለ ድረስና ይህን ዘርን መሰረት ያደረገው አገዛዙ እንዲቀጥል እስከፈቀድንለት ድረስ ወደፊትም ሌሎች የግዳጅ ሰላማዊ ሰልፎችን፣ ድራማዎችንና ፊልሞችን ማየታችን አይቀርም። እንዴውም ሰሞኑን ከወያኔ መንደር እንደሚሰማው ሞቅ ያለ መረጃ ከሆነ፤ ሕወሃት ጅሃዳዊ ሃረካትን የመሰለ ቅንብር ፊልም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስር በተቋቋመውና ማህበረ ቅዱሳን በሚባለው ማህበር ላይ ሰርቶ ለሕዝብ ለማቅረብ ከጫፍ እንደደረሰ እየተሰማ ነው።

ይህን መሰሉን የውሸት ትእይንት በማዘጋጀት ሀቅን መሸፈን እንደማይችል ሕወሃት ቢያውቅም እነዚህን የውሸት ቅንብሮች ማዘጋጀቱንና ለህዝብ ማቅረቡን ግን ከአንድ ነገር በቀር ሊያስቆመው አይችልም። ይህም ሁላችንም አንድ ሆነን ሕወሃትን ስናስወግደውና እኩል የምንከበርባትን ኢጥዮጵያ ስንፈጥር ብቻ ነው።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on April 13, 2014 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: