RSS

ኢትዮጵያዊያንን መበታተን፤ ያልተሳካው የሕወሃት ራዕይ

13 Apr

ሚያዚያ 13 2014

አንድ ቡድን ወይም ድርጅት አንድን ችግር ነቅሶ አውጥቶ ሕዝብ እንዲከተለው ለማድረግ፤ የተነሳው ሃሳብ ወይም ችግር  የሕዝብ ጥያቄ መሆን ይኖርበታል። ችግሩን የመፍታት መንገዱም በሕዝብ ሙሉ እውቅናና ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ሊሆን ይገባዋል። ብዙ ጊዜ ጥቂት የማይባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የራሳቸውን ፍላጎት በሕዝብ ስም ይዘው ቢነሱም የሕዝብ ድጋፍ በማጣታቸው እንደከሰሙ ከኢትዮጵያ የተሻለ ጥሩ ምሳሌ ልናገኝ አንችልም። እንደ ሕወሃት አይነቶቹ ደግሞ በበቀልና በጥላቻ አምጠው የወለዱት አማራን የመጥላትና ብሄሮችን የማጋጨት አባዜ የሕዝብን ይሁንታ ቢያጣም በመሳሪያ በማስፈራራት፣ በጥቅማጥቅም በመደለልና እንዲሁም እንደነሱ አይነት ጠባቦችን ከያካባቢው በማሰባሰብና ሕዝብን በመጫን የሕዝብ ጥያቄ ነው ብለው አርባ ዓመት ሙሉ የሙጥኝ እንዳሉ አሉ። ያም ቢሆን ግን የሚያፍር ህሊናና ዝም የሚል ምላስ የላቸውም እንጅ አካሄዳቸው አሁንም ትክክል እንዳልሆነና ፍጻሜያቸው ውድቀት እንደሆነ ከሕዝብ እየተነገራቸው እና እነሱም እያዩት ነው።

የሕወሃት ባለስልጣናት ከደማቸው በተወሃደው የአማራ ሕዝብ ጥላቻ እየተገፉ፤ ከሕዝብ በተዘረፈ ገንዘብ ነጋ ጠባ መልካም ነገር በማይወጣው ጉሮሯቸው በሚንቆረቆር የውስኪ ጉልበት እየተንደረደሩና በስጋ ብስናት እየታጠኑ አርባ ዓመታት ሙሉ ሰርተውት ደክመውበት ያላጠናቀቁትን የኢትዮጵያን ሕዝብ የመበታተን ራዕያቸውን ለመተግበር ዛሬም ድረስ እንቅልፍ አልተኙም። ዛሬም ሕወሃት ጉዳዩ አልጋባብ ሲወጠር እያላላ የላላ ሲመስለውም በሚመስለው መልኩ እየወጠረ ሕዝብን የማበጣበጥና የመለያየት ሰይጣናዊ ስራውን ገፍቶበታል።

ባሁኑ ሰአት ሕወሃት ሕዝብን ለማበጣበጥ እየመዘዛቸው ያሉት ብሔር ብሔረሰብ፣ ሃይማኖትና አንዳንዴም አክራሪነት የሚባሉት የወያኔ ካርዶችም ቢሆኑ የሕወሃትን ክፋት ያክል የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቃቸውና በተደጋጋሚ ተሞክሮ ያሸነፈባቸው ናቸው። ይሁን እንጅ እነኝህ ሕዝብን ማበጣበጫ ዘዴዎች በቃቸው ተብለው ታሪክ ከመሆን ይልቅ አሁንም በወያኔ ሕወሃት በመመዘዝ ላይ ያሉ መሆናቸው ነው አሳፋሪው ጉዳይ። ከስራው የማያውቀው፣ ከስህተቱ የማይማረው እንዲሁም ከሽንፈቱ የማይሰለጥነው ሕወሃት ግን አሁንም አማራውን የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጠላት አድርጎ ሌላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአማራው ላይ እንዲነሳ ለማድረግ መሞከሩን ግን አልተወም።

ሕወሃት የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ብሎ የሚጠራውንና በስፖርት ስም የፖለቲካ ቅስቀሳ ዘመቻ መድረኩን ምክንያት በማድረግ ለዘመናት ተከባብረው የኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችን ለማበጣበጥ ገና ከሳምንታት በፊት ጣጣውን ጨርሷል። ይህን የዛገ ዘዴውን ለመጠቀም ተዘጋጅቶና ጉደዩን ፈጻሚ ድራማ ሰሪዎችን አሰልጥኖ ባህርዳር የከተመው ሕወሃት የኦሮሞና አማራ ወጣቶችን ለማበጣበጥ ባሰለጠናቸው ድራማ ሰሪዎች አማካኝነት እሳት ቢጭርም ያሰበውን ያክል አልቀናውም። ይሁን እንጅ ሕወሃት በማሕበራዊ መገናኛ መድረኮች ተወካይ ካድሬዎቹን በመጠቀም የአማራው ሕዝብ አሁንም ለሌሎች ብሔሮች ክብር እንደሌለው በመዘርዘር አማራው በቀዳሚነት ከኦሮሞው ሲቀጥልም ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር እንዲጋጭና ሰላም እንዳይኖር ለማድረግ የማይሳካ የጥፋት መርዙን በመርጨት ላይ ይገኛል። ሕወሃት የደገሰው አልሰመረም እንጅ ተሳክቶ ቢሆንና እጅግ የበዛ ችግር ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ በተለመደ ዘዴው አስታራቂ ሆኖ በመግባት ጥፋቱን ሁሉ በኦነግ አልያም በግንቦት 7 በማመካኘት ሌላ አስቂኝ ድራማ ይሰራ ነበር። ምክንያቱም ይህ የተለመደና ከሕወሃት እስስታዊ ባህሪዎች አነዱና ዋነኛው ነውና።

ከዚህ በፊትም ገና የአገዛዝ ወነበሩ ጸንቶ ሳይቆም በዘረኝነት የታወሩ ቁምጣ ለባሽ  ወታደሮቹን በመጠቀም በአርሲ በባሌና በሀርር የተለያዩ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ አማራ አርሶ አደሮችን በግፍ ካስጨፈጨፈና ከነሂዎታቸው ሳይቀር ወደ ገደል ካስወረወረ በሗላ በአማራው ላይ የደረሰውን ይህን ሁሉ ግፍ ኦሮሞው ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጋር በማበር እንደፈጸመው አድርጎ ብዙ ፕሮፖጋንዳ መስራቱ የማንረሳውና በሀዘን የምናስታውሰው ታሪካችን ነው። በመሆኑም ሕወሃትን የሚያስጨንቀው ስልጣኑ እንጅ በኢትዮጵያ ሰላም መኖር አልያም ልማት መስፋፋት አይደለም። የሕወሃት ህልም እንዴት አድርጌ ለረዥም ዘመን በስልጣን ላይ እቆያለሁ ነው እንጅ አንደኛው ብሔር በሌላኛው ላይ ተነስቶ የሚያፈሰው ደም የሚጠፋው ክቡር የሰው ልጅ ሂዎት አልያም የሚወድመው የሕዝብ ሃብት አይደለም። ምክንያቱም በተለያዩ ጊዜያት እና በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ሕወሃት የጀምሩ ፊሽካ ነፍቶ ያስጀመረውን የብሔር ብሔረሰቦች የእርስ በርስ እልቂት ራሱ የጨርሱ ፊሽካ በመንፋት ሲያስቆም አይተናልና ነው። ሕወሃት ሀገራችንን የመበታተንና ሕዝባችንን የማለያየት ዓላማው ያሰበውን ያህል እየያዘለት አለመሆኑን ብንረዳም።  በዘይሴና ደራሸ፣ በጉጅና በቦረና ኦሮሞዎች፣ በሶማሊና በቦረና፣ በአፋርና በሶማሊ ሕዝብ እንዲሁም ወጋጎዳ ብሎ የፈጠረውን አርቲፊሻል ቋንቋ በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጎፋና በዳውሮ አካባቢ በሚኖረው የሀገራችን ሕዝብ ላይ ለመጫን በተንቀሳቀሰበት ወቅት የተፈጠረውን የሕዝብ ትርምስና ስቃይ ብቻ ማስታወስና በነኝህ ችግሮች ሁሉ ራሱን ነጻ እየደረገ ሌሎችን እየከሰሰ ዘብጥያ ያወረዳቸውን የገደላቸውንና ያሰደዳቸውን ወገኖቻችንን ስንቆጥር ሕወሃት ካተረማመሰን በሗላ ሁሌም አንዳችንን ላንዳችን ተጠያቂ እየደረገ የቆየና አሁንም ይህንኑ ስራውን እየተገበረ ያለ ከፋፋይ ማፍያ መሆኑን እንረዳለን። የሰሞኑ በባህርዳር ከተማ አማራውንና ኦሮሞውን ለማጋጨት የተሞከረው ሙከራም የዚያው የሕወሃት ሕዝብን የማጋጨትና መልሶ የመክሰስ አባዜው ቀጣይ እንደሆነ ለመረዳት ብዙ ምርምር ማድረግ አያስፈልግም።

ሕወሃት ራሱ አቅዶ የፈጸመውን አንዱን ለይቶ የመምታትና የማጎሳቆል አካሄድ በሌሎች ላይ የማመካኘት ጠባዩ የታወቀ ቢሆንም “የሌባ አይነደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” ነውና በተደጋጋሚ መተግበሩን ግን አልተወም። በቅርብ ከምናስታውሰውና ከሁለት ዓመታት በፊት ጀምሮ ሕወሃት እየተገበረው ያለውን አማራውን ከጉራ ፈርዳና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የማፈናቀል ድርጊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የዜና ሽፋን በማግኘቱ ከፍተኛ ትችት ማስከተሉ የታወሳል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ታዲያ ፋሽስት ወያኔ እንደገና ተገልብጦ ጉዳዩን እንደማያውቅና ድርጊቱን የፈጸሙት ሁሉ በህግ ይጠየቃሉ በማለት ጣቱን ባካባቢው ባለስልጣናት ላይ መቀሰሩን ስናስታውስ ሕወሃት የራሴ ለሚላቸውና እቅዱን እያስፈጸሙ ላሉ የአገዛዙ ቁንጮዎች እንኳ ምንም ደንታ የሌለው ከራሱ ስልጣንና የጥቅም ተጋሪዎቹ በቀር ለማንም የማይጨነቅ በሰው ቁስል እንጨት ከመክተት የማይመለስ መሆኑን እንረዳለን።

ሕወሃት ይህ ሕዝብን የመበታተን ዓላማው አርባ ዓመታት ሙሉ ለምን እንዳልተሳካ ለመመርመር ዝግጁ አይመስልም። ምክንያቱም የሕዝብ ያልሆነ ጥያቄ አንግቦ እንደሚንገታገት ያውቀዋልና ነው። የሕዝብ ጥያቄ የሆነ በሕዝብ ይደገፋል ይመራልም። የሕዝብ ያልሆኑትና በሕወሃት ጠባቦች የተፈጠሩት በብሔር ብሔረሰብ፣ በሃይማኖትና በሽብርተኝነት ስም ፕሮፓጋንዳ የሚሰራላቸው ሁሉ ግን ከፍተኛ የሕዝብ ተቃውሞ እየተነሳባቸው ያሉና ወደፊትም ታላቅ ተቃውሞ የሚያስነሱ ለመሆናቸው ጥርጥር የለም። ስለሆነም ዛሬ የብሔር ብሔረሰብ፣ የሃይማኖትና የሽብርተኝነት ችግሮች ተብለው በሀገራችን በሕወሃት እየተነሱ ያሉት ሁሉ ወያኔዎች እንዳሰቡት ሳይሆን ሕዝባችንን የበለጠ እንዲተዋወቅና እንዲተባበር አደረጉት እንጅ አላለያዩትም። ከዚህ በፊት በሕወሃት የተፈጸሙትም ሆኑ ሰሞኑን በባሕርዳር ከተማ የተሞከረው ሕዝብን የማጋጨት ድራማም ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የበለጠ አስተዋውቆን በጋራ ጠላታችን ሕወሃት ላይ በእልህ እንድንነሳ የደርገናል እንጅ አያበጣብጠንም አያለያየንምም።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on April 13, 2014 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: