RSS

በምንም ምክንያት ቢሆን ሀገርንና ሕዝብን በመክዳት ከህሊና ወቀሳ የጸዳ ሀብትም ሆነ ክብር ማግኘት አይቻልም!!!

25 Mar

መጋቢት 25 2014

ሀገራችን ኢትዮጵያ በወጣት ህዝቦች ከተገነቡት ጥቂት የዓለማችን አገሮች አንዷ ናት። ይህ ደግሞ ከሃገር ምርታማነት፣ ሀገርን ከውጭ ወራሪ ጥቃት ከመከላከል፣ የሀገርን አመራርና አስተዳደር በአስተማማኝ ደረጃ ላይ ከማስቀመጥ እና ለውጥን በፍጥነት ተቀብሎ በሚፈለገው ጥራት ወደሚፈለገው ውጤት ከመቀየር አኳያ ሲታይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉት ሃገራት የወደፊት እድላቸው በጣም ሰፊና ያማረ እንደሚሆን በብዙ ሰዎች ይታመናል። ይህ ማለት ግን፣ ወጣቶቹ፤ መብትና ግዴታቸውን በትክክል ተገንዝበው በተገቢው ጊዜ ተገቢውን ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የመንፈስ ጥንካሬ እንደሚያሻቸው እርግጥ ከመሆኑም ባሻገር፣ መብታቸውን አስከብረው ግዴታቸውን ለመተግበር የሚያስችል ሁኔታ መኖርና አግባብ ካለው አካል ሁሉ ድጋፍና ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸው መሆኑ ሳይዘነጋ ነው።

ወጣቶች በሀገራቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ እኩል ተሳታፊ በመሆን ዘለቄታዊ እድገት እንዲያመጡ ለማድረግ፣ ለመጣው ለውጥ ወይም እድገትም የኔም አስተዋጽኦ አለበት እንዲሉና የኔነት ስሜት እንዲያዳብሩ እንዲሁም ከእድገቱም ያለ አድልዎ ተቋዳሽ ለመሆን እንዲችሉ፤ ዴሞክራሲን እና የዴሞክራሲ አሰራርን አብረው እንዲለማመዱ መደረግ አለባቸው። ይህ ደግሞ አንድ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን እየገነባሁ ነው የሚል መንግስት ከሚያደርጋቸው የመጀመሪያ እርምጃዎች አንዱና መሰረታዊው ነው። በዚህ መሰረት ቀስ በቀስ የሚገነባ ዴሞክራሲያዊ ስርአትም በተከታታይ ትውልዶች እየዳበረ ይሄድና አድገዋል፤ የዴሞክራሲን ፍሬም አይተዋል ወደምንላቸው ሀገሮች ጎራ አብሮ መሰለፍን ሊፈጥር ይችላል።

ዴሞክራሲና የዴሞክራሲ ስርአት በጉልህ ከሚገለጹባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ ደግሞ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መገንባት እና መንቀሳቀስ ነው። በዚህም መሰረት ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ለማከናወን ከሚቋቋመው ምርጫ ቦርድ ጀምሮ የሀገሪቱ ህግ አውጭ ( ፓርላማ)፣ ህግ ተርጓሚ (ፍርድ ቤት) እና ህግ አስፈጻሚ ተቋማት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መቋቋማቸውን ከመረዳት አንስቶ ያለ ተጽእኖ እየተንቀሳቀሱ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ያስፈልጋል። አማራጭ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሰብአዊ መብት ተንከባካቢ አካላት እና የሙያ ማህበራት እንዲሁም ማህበራዊ እንቅስቃሴን ለማቀላጠፍ የሚመሰረቱ ማህበራዊ ድርጅቶች ያለምንም መንግስታዊ ግፊት እና አነሳሽነት በህዝብ ፍላጎት ብቻ የተመሰረቱና በህዝብ አመራር የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ከመገንዘብ ጀምሮ የተለያዩ የሰው ልጅ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያረጋግጡ ህጎች መውጣታቸውንና መተግበራቸውንም ማረጋገጥ አስፈላጊ ይሆናል።

ከላይ የተዘረዘሩትን መሰረታዊ የዴሞክራሲ መርሆች በመመርኮዝ በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታና በወጣት ሃይል የተገነባውን ህዝባችንን በግርድፉ ስንመለከት ብዙ ያልተጣጣሙና የማያቀራርቡ ችግሮችን እንመለከታለን። ወጣቱ፤ የውጭ እርዳታ ፈሰትን ከፍ ማድረግን ኢላማ ባደረጉትና ፍጹም ዳሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ ተቋቁመው በወያኔው አገዛዝ ተጽዕኖና አፈና ምክንያት የታዘዙትን ከማስፈጸም ባሻገር ሌላ የራሳቸው የሆነ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ በማይችሉት የይስሙላ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ገብቶ እንኳ መንቀሳቀስ እንዳይችል የሕወሃት አገዛዝ የተለያዩ የማይመቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ይህን አምራች ትኩስ ሃይል ወደ ውጭ ሃገራት ለስደት ሲዳርገው ይታያል። በእድሜም ሆነ በፆታ ከሚመስሉት ወይም በሙያ ከሚቀርባቸው ወገኖቹና ጓደኞቹ ጋር፤ የወያኔው አገዛዝ ባወጣው ህገ መንግስት በሚፈቅደው መንገድ እነኳ፤ ተደራጅቶ በነጻነት ሃሳብን ለመግለጽ እና እራሱን፣ ወገኑንና ሀገሩን ለማገልገል እንዳይችልም የሕወሃቱ አገዛዝ ባምሳሉ ቀርጾ እንደፈለገ የሚያንቀሳቅሳቸውን እንጅ እንዲህ በራስ ተነሳሽነትና ፍላጎት የሚመጡትን የፖለቲካ፣ የሙያም ሆነ የሰብአዊ መብት ተንከባካቢ ድርጅቶችን የማይፈልግ ሆነ። ከተመሰረቱም በዚያም በዚህ ብሎ የመንቀሳቀሻ ምህዳሩን በማጥበብና ከራሱ የሚጠበቀውን እገዛ በመከልከል ከመጠንከራቸው በፊት እንዲከስሙ ማድረግ፤ አንዳንዴም የነዚህን ድርጅቶች መሪዎችና ጉልህ ተሳታፊ አባላትን በቅጡ ባልታየና ባልተረጋገጠ ማስረጃ፤ ሲከፋም በራሱ በወያኔ ሕወሃት ሰዎች ቀድሞ በተዘጋጀና በተቀነባበረ የውሸት ማስረጃ በአደገኛ ቦዘኔነት፣ በዘር ማጥፋት፣ በመንግስት ግልበጣ፣ በሃይማኖት አክራሪነት፣ በሙስና፣ በአሸባሪነትና በተለያዩ ሌሎች መንገዶች በመወንጀልና በመክሰስ ወደ ወህኒ መወርወር ወይም ከጫወታ ውጭ ማድረግ ወያኔ የተፈጸሙና እየተፈጸሙ ካሉት ወጣቱን የሚያስበረግጉ ችግሮች ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።

የሕወሃት አገዛዝ ያስቀመጠውን መስፈርት እንደ አንድ አማራጭ ቆጥሮ አሜን ብሎ በመቀበል “ዛሬን ልኑር ነገ የራሱ ጉዳይ” በሚል መልኩ በመንቀሳቀስ ላይ ያለው ወጣት ደግሞ ከሱ በፊት በወያኔ እንደሸንኮራ ተመጠው ከህልማቸው ሲነቁና ለምን ብለው ሲጠይቁ እንደተተፉት ወጣቶች ተራው እስኪደርስ ድረስ ሀገሩን በማድማት፣ የወገኑን ርሃብና ስቃይም በማራዘምና ራሱንም ክዶ ሌሎችን ሆኖ ይኖራል እየኖረም ነው።

በዚህም ምክንያት ላለፉት የሕወሃት አገዛዝ ዓመታት አድማሱን እያሰፋና የበለጠ ውስብስብ እየሆነ የመጣው የወያኔ ዘረኛ አገዛዝና ዘረኛነቱ የፈጠረው ክፍፍልና መለያየት በቁጥር ጥቂት የማይባለውን ወጣት ሃይል በስሩ በማሰለፍ ህሊናውን ትቶ በሆዱ እንዲያስብ ማድረጉ እሙን ነው። ይሁን እንጅ ለጊዜው እራሱንና ቤተሰቡን ያስደሰትኩ መስሎት ለሕወሃት ርካሽ ዘረኛ ፖለቲካ ራሱን የሸጠም ሆነ ለሽያጭ ያዘጋጀ የወጣት ሃይል ሁሉ ነጻነቱን ማጣቱ ሳያንሰው እድሜ ዘመኑን በሙሉ በህሊና ወቀሳ ሲሸነቆጥ የሚኖር መሆኑ አሌ የማይባል ሃቅ ከመሆኑም ባሻገር ለቀጣይ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ የሚያወርሰው ታሪክ የሌለውና ሲሰራው በኖረው ስራም ልጆቹ ሲሸማቀቁና ሲያፍሩበት እንደሚኖሩ ሲያስብ አሁን እየኖረው ያለው ህይዎት የምድር ላይ ሲኦል እንደሚሆንበት እሙን ነው።

ይሁን እንጅ፤ምንም እንኳ ሕወሃት የፈጠራቸው ውስብስብ ችግሮች የወጣቱን እይታ ቢጋርዱበትም ያለማንም ርዳታ በሙሉ ወኔ ሀገራቸውን አስከብረው፣ ማንነታቸውን ከፍ አድርገው ለዓለም ያሳዩት የአያት የቅድም አየቶቹ የአልበገርም ባይነት ውርስ በደሙ ውስጥ እየተንጠረጠረ መሆኑን መዘንጋት የለበትም። ከዚያም ሲያልፍ አሁን በሕወሃት እየተረገጠ ያለው ወጣት “እኛ በትግሉ ሂደት ብናልፍ እንኳ የወገኖቻችን ሂወት መስተካከል አለበት፣ ሀገራችን የቀደመው ክብሯና ማንነቷ መመለስ አለበት” በማለት ትምህርታቸውንም ሆነ ሌላውን  ጥቅማጥቅማቸውን ሁሉ በመተው ወደ ትግል የገቡትን  የ1960ዎቹን የኢትዮጵያ ወጣቶች እንቅስቃሴ አርአያ በማድረግ ከህሊና ወቀሳ የሚያድነውን ርምጃ መውሰድ ይኖርበታል።

ለወያኔው አገዛዝ የሸጠውን ነጻነቱን ለመመለስ ሀገራችንን በአንድ ብሔር ዘረኛ አገዛዝ እየተረገጠ ባለውና ህዝባችንንም አፍኖና ረግጦ ለድህነት፣ ለልመናና ለስደት በመዳረግ ላይ ያለውን የሕወሃትን ዘረኛ አገዛዝ ለመጣልም ተግባራዊ ርምጃ መውሰድ መጀመር አለበት። የዴሞክራሲና ያንድነት ሃይሎችም በሚኖርበት አካባቢና በሚሰራበት ቢሮ በርመድረሳቸውን አውቆ በእጁ ያለውንም ሆነ የሚያውቀውን የወያኔ ሚስጥር ለዴሞክረሲአዊ ሃይሎች በማቀበል ትግሉን ማጧጧፍ ይኖርበታል።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on March 25, 2014 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: