RSS

የክስና የተማጽኖ ብዛት ያላስተማረው ወያኔ ዋጋውን ከሕዝብ ክንድ የሚያገኝበት ቀን ቀርቧል

09 Mar

መጋቢት 9 2014

በዴሞክራሲአዊ አካሄድ የተመሰርቱ መንገስታት ይህን ታላቅ ሃላፊነት ያስረከባቸውን ሕዝባቸውን ያከብራሉ፤ ይፈራሉም። በመሆኑም ስልጣኑን የሰጣቸውን ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት ይጥራሉ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ አንዳች የተምታታ ነገር ቢፈጠርና  ጉዳዩን በተመለከተ ከሕዝባቸው ጥያቄ ቢነሳ ያላንዳች ማመንታት ጥያቄውን ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ካልሆነም ሕዝብ የሰጣቸውን አመኔታ አልተገበሩምና የሰጣቸውን ሃላፊነት ይነጥቃቸዋል። በዚህ የተነሳም ዴሞክራሲያዊ ነኝ የሚል መንግስት ዴሞክራሲአዊ ስርአት የሚያስፈልጉትን አሰራሮች ይተገብራል ማለት ነው።

ባሁኑ ሰአት ባለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ የየትኛውም ሀገር መንግስት ስለዴሞክራሲ ሲያውራ በሀገሩ መልካም አስተዳደር ስለመስፈኑና የዜጎች ሰብአዊ ምብት መከበሩን በጉልህ ማረጋገጥን ጨምሮ ሌሎችም የዴሞክራሲ ትሩፋቶች እየተተገበሩ ስለመሆናቸው በግልጽ ማመላከት ይኖርበታል። ይህን ካላደረገ ደግሞ የየሀገሮችን ዓመታዊ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር፣ የሕዝቦችን መሰረታዊና ፖለቲካዊ መብቶች መከበርንና የመሳሰሉትን እንቅስቃሴዎች ከሚዘግቡ ዓለማቀፍ ተቋማት ሪፖርት ጋር መፋጠጡ ግድ ይሆናል። ከዚያም ሲያልፍ የዴሞክራሲን ስርአት ከመገንባት ጋር በተያያዘ ከዓለማቀፉ ማሕበረሰብ የሚቀርቡ ብድርና እርዳታዎችን እስከመከልከል ሊደርስ ይችላል።

በዴሞክራሲ ስም የሕዝብን ድምጽ በመንጠቅ መንግስት ነኝ ያለውን አምባገነኑን ፋሽስት ወያኔን ከዚህ አጠቃላይ ሁኔታ ጋር ስናስተያይ ብዙ ነገሮች የተዘበራረቁ ሆነው እናገኛቸዋለን። ምክንያቱም ወያኔ ሕወሃት ገና ከጅምሩ የሕዝብን የበላይነት የማይቀበል ከመሆኑም በላይ እምነቱ በዘር እንጅ በእውቀት፣ በችሎታና በልምድ ላይ የተመሰረተ አሰራርን አይከተልም ወይም የሌሎችን ምክርና አስተያየት ለማድመጥ ዝግጁ አይደለምና ነው።

ወያኔ ሕወሃት ዴሞክራሲያዊ አሰራርን እንዲከተል በተለያዩ ወገኖች ከፍተኛና ተከታታይ ምክር ገና ከጫካ ዘመኑ ጀምሮ ሲሰጠው የቆየ ቢሆንም ለመተግበር ግን ዝግጁ አልነበረም። ከራሱ የድርጅት ጓዶቹ ጀምሮ ርዳታ እስከሚያቀርቡለት አንዳንድ መንግስታት ጭምር የእርምት እርምጃዎችን እንዲያደርግ ከፍተኛ ስራ ቢሰራም ”ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም” እንደሚባለው የሀገራችንን ክብር በማዋረድ፣ የነገስታቶቻችንን ማንነት በማጣጣልና በማኮሰስ ጀግነታቸውንም በማራከሱ ገፋበት። የባንዲራችንን ትርጉም በማጥፋትና በማንቋሸሽ፣ የሀገራችንን ዳር ድንበር በማስደፈሩና ታሪኳንም በመደለዙ በረታበት። በመምከሩ ያልተሳካላቸውና ይህንን በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ እየተደረገ ያለውን ደባ መቋቋም የተሳናቸው በጣት የሚቆጠሩ የራሱ አባላት እየጣሉት ወጡ። ምክርና ተግሳጽ ያልበገረው ፋሽስት ወያኔ ግን ይባስ ብሎ በዴሞክራሲ ስም ነፃነትን በመግፈፍ፣ መብትን በመርገጥ አፈናንና ፍርሃትን በሕዝባችን ላይ አንግሶ እስካሁን ቀጠለ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም እንዲደረጉለት የሚፈልገውን በተደጋጋሚ ቢያሳውቅም ፋሽስት ወያኔ ግን የሕዝብን ጥያቄ ለማዳመጥ ዝግጁ እንዳልሆነ ሰላማዊውን ጥያቄ በሃይል ተግባር በመመለስ አረጋግጧል። የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የወያኔ ሕወሃት አካሄድ ለሀገራችን፣ ለሕዝባችንና ለራሱ ለሕወሃትና ለቁንጮዎቹ ሳይቀር መልካም እንዳልሆነ ለማመለከት ቢጥሩም ያገኙት መልስ ግን የተለመደና አምባገነናዊ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ከንጉሱ ዘመን ፊውዳላዊ አገዛዝ እንዲሁም ከደርግ ፋሽስታዊ አገዛዝና አወዳደቃቸው ምንም ተሞክሮ እንዳልወሰደ የተረዱና በራሱ የይስሙላ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ያልተደሰቱ ብዙ ወገኖች እያቀረቡት ያለው የክስና የተማጽኖ ብዛት ያላስተማረው ወያኔ ሕወሃት ግን መሽቶ መንጋትን እንደድልና እንደትክክለኛነት በመቁጠር በግፍ ላይ ግፍ፤ በመከራ ላይ መከራን በመደራረቡ ቀጥሎ በሕዝባችን ተገፍትሮ ወደሚወድቅበት የመጨረሻው ጫፍ ደርሷል።

ከዚህ በፊት በራስ ተነሳሽነት በሀገራችን የተቋቋሙ ሀገር በቀል የሰብአዊ መብት ተቋማት በወያኔ ሕወሃት አገዛዝ ዘርን፣ ቋንቋንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ አድሎዎች መኖራቸውን፤ በሀገራችን የህዝባችን መሰረታዊም ሆነ ፖለቲካዊ መብቶች እየተከበሩ አለመሆናቸውን፤ መልካም አስተዳደር ጠፍቶ ሙስና እየነገሰ መምጣቱን፤ ሰዎች ባመለካከታቸው ብቻ ወህኒ እየተወረወሩ መሆናቸውን፤ ሕዝባችን መብቱን ስለጠየቀ ብቻ ማሳደድ፣ ግርፋትና ግድያን ጨምሮ የበዛ ስቃያ እንደሚያጋጥመው በማስመልከት ብዛት ያላቸው ሪፖርቶች ያወጡ ቢሆንም ፋሽስት ወያኔ ግን የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሎ በወፍራሙ እንደተኛ ነው።

ባጠቃላይ ሰሞኑን አሜሪካ ያወጣውችውን የሀገሮች የሰብአዊ መብት አያያዝ ሰፋ ያለ ሪፖርት ጨምሮ ሂውማን ራይትስ ወችና አመንስቲ ኢንተርናሽናል ስለ ወያኔ ሕወሃት እና አገዛዙ እየወሰደው ስላለው እጅግ የተዛባ አገዛዝ ብዙ ብዙ ብለው ነበር። በሀገሪቱ ስላለው የዜጎች ሰብአዊ መብቶች አለመከበር፤ በዘርና በዝምድና የተተበተበውን አገዛዙንና የነገሰውን የመልካም አስተዳደር መጥፋት፤  ቀስ በቀስ እየነገሰ በመጣው ሙስና ምክንያት በሀገሪቱ አንደኛው የወያኔ ቁንጮ ሌላኛውን መጠየቅ ወደማይችልበት መንግስታዊ ሙሰኝነት እያመራች መሆኑን፤ ዜጎች አሳማኝ ባልሆኑ ምክንአቶች ከባድ ስቃይ እንደሚያጋጥማቸውና ሞትና እስርን ጨምሮ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ዜጎች የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ እና ሌሎችንም የወያኔ ሕወሃት አይነተኛ መገለጫዎች በማጋለጥ እያደረገ ካለው መሰል ኢዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲታረም ማሳሰቢያዎችንና የተማጽኖ ጥሪዎችን ቢያቀርቡም ፋሽስት ወያኔ ግን በታጠቀው መሳሪያ ተማምኗልና ለእንዲህ ያለው ሪፖርትም ሆነ ጥሪ ጆሮ ያለው አልመሰለም።

ስለሆነም ጠይቆ ጠይቆ መልስ ያጣ ሕዝብ ደግሞ ራሱ የሚመስለውን እርምጃ መውሰዱ የማይቀር ተፈጠራዊ ነውና ርምጃውን ጀምሯል። ለዚህም ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ እና በተለያዩ የትግራይ ከተሞች እንዲሁም በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች የታዩት ሕዝባዊ እንቢተኝነቶችና በየከተሞች እየተበተኑ ያሉት የእንታገል መልእክት የያዙ  በራሪ ወረቀቶች እንዲሁም በየግድግዳው ላይ የሚጻፉት መፈክሮች አይነተኛ መገለጫዎች ናቸው። ከተለያዩ ሀገር በቀልና ዓለማቀፋዊ ተቋማት ማሳሰቢያዎችና ማስጠንቀቂያዎች ያልተማረው ወያኔ ሕወሃትም ምሬት ባስተባበረውና በግልጽ እየታየ በመጣው የሕዝብ ክንድ ተደቁሶ ከመድረኩ ዞር የሚልበት ቀን ሩቅ አይሆንም። ሁሌም አሸናፊው ሕዝብ ነውና።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on March 9, 2014 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: