RSS

የቡሄ ዕለት የደነቆረ ሆያሆዬ ሲል ያረጃል 2

31 Jan

ጥር 31 2014

እድገትን፣ መልካም አስተዳደርን፣ ነጻ ሚዲያን፣ ዴሞክራሲን፣ የሕዝብን ነጻነትና የመሳሰሉትን በአንዲት ሀገር የሚከወኑ ለውጦችን ነቅሰው በማውጣት ዓመታዊ ሪፖርት የሚያቀርቡ ዓለማቀፍ ተቋማት በተደጋጋሚ የወያኔን ውሸት እያጋለጡና አገዛዙ የደረሰበትን የዝቅጠት ደረጃ በማስረጃ እያመሳከሩ ቢያስረዱም የአዲስ አበባው ወያኔ ዜና አገልግሎትና በረከት ስምኦን ግን ሀገራችን በፋሽስት ወያኔ አገዛዝ እያሳየች ያለችው እድገት ከውድድር በላይ ሆነ እያሉን ይገኛሉ።

ባንዲት ረፋድ አርሶ የሚጨርሳትን ቁራጭ መሬት ይዞ ለዚያውም ባናቱ የፓርቲ አባልነት ካርድ ካልያዘ ይችኑ እንደሚያጣ ጧት ማታ የሚዛትበት ገበሬ በሕወሃትና በነበረከት ዓይን ዓመታዊ ተቀማጩ የሀገሪቱን ባንኮች አንዳጣበበ ሳይታከት ይነገርለታል። ሀብቱ ጣራ ነካ እየተባለ የሚነገርለት ገበሬ ግን ይልሰው ይቀምሰው አጥቶ በሀገር ውስጥ ስደት ከተሞችን እንዳጣበበ የሀገራችን ነባራዊ ሀቅ ነው። የቀረውም ቤት የሌለው ሃብት የሌለው የመንገድ ላይ ተንጠራዋዥ ከሆነ ቆይቷል። ከስደት የተረፈውም ከልክ በላይ በጠበበው የእርሻ መሬት ከልክ በላይ ተጣቦ ለከብቶቹ የግጦሽ ሳር ለማስቀረት ተስኖት በግል ከብቶቹ የሚቆጠር አጥንት ሂዎቱን ሊያቆም ላይሞላለት ይታትራል። ከዚህ ሁሉ ድካሙ በሗላ የሚገኝና ለገበያ የሚቀርብ ነግር ካለ እንኳ እሱ ሀገሪቱን የተቆጣጠረው የቢዝነስ ኢምፓየር ኤፈርት ሲሳይ እንጂ የድካሙን ፍሬ የሚያገኘው ያገሬ የተገፋ ገበሬ አይደለም።

የፋሽሰት ወያኔ ራዲዮኖችና ጋዜጦች የሚያወሩት፤ እንደነበረከት ያሉ የአገዛዙ ቁንጮዎች ትላንትም ዛሬም ያለድካም የሚለፈልፉት የሀገራችን አጠቃላይ እድገትና በተለይም የገበሬው ተመችቶት የመኖር ዜና ምናልባትም በዘመነ ወያኔ ያልታየና ከዚያ በፊት የነበረ እንጅ በሕወሃት ዘመንማ ያተረፍነው ርሃብ ነው፣ ውርደት ነው፣ ሰደት ነው፣ ከዚያም ሲያልፍ በሀገራችን እንደምንም መታየትን ነው። ምንም ጥቅም እንደማይሰጥ፣ እንዳልተፈጠረ፣ ፈጽሞ እንዳልነበርን መቆጠር ነው የተረፈን፤ ሁላችንም።

“የቡሄ እለት የደነቆረ ሆያ ሆየ ሲል አረጃል” እንደሚባለው ሕወሃት በራሱ ዓለም በምናቡ አንድ ለራሱ ደስ የሚል ትእይንት ፈጥሮ ሁሌም ስለዚያ ያወራል። በዚያ የሕወሃት ምናባዊ ትእይንት መሰረትም የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሶስቴ ይበላል ተብሎ እኛም ጠብቀን ነበር። የሆነውና እየሆነ ያለው ሃቅ ግን ሕዝባችን አንዴም እንኳ በቅጡ ቀርቶ እንደነገሩ መቅመስ እንዳቃተው ነው። ይሁን እንጅ አሁንም በረከትና ሕወሃት ባለፈው ዘመን ባዩት ቅዠት ላይ እንደተተከሉ ቅዠታቸውን እውነት ነው ለማለት እየተውተረተሩ ይገኛሉ።

በፋሽስት ወያኔ ስልታዊ ተንኮል የተሞላበት አካሄድ መከራ ፍዳውን እየቆጠረ ያለው ገበሬ፣ ነጋዴውና ሰራተኘው ባጠቃላይ የሀገራችን ሕዝብ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ትሰለፋለህ ተብሎ በሕወሃትና በነበረከት ተነግሮት ገበሬው ሎተሪ ሲያዞር፣ ምሁሩ ድንጋይ ሲፈልጥ፣ ነጋዴው የኤፈርት ተላላኪ ሆኖ ስንት ዓመቱ እየጠበቀ አለ። መካከለኛ ገቢ የተባለው ግን በስምና በወያኔ ሚዲያዎች በቀር አሁንም ድረስ አልታየም። በረከትና ሕወሃት ግን  ባፍ መፍቻ ንግግራቸው የሕዝባችን የኑሮ ደረጃ ተሻሽሏል ሀገራችንም መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለትሰለፍ ጥቂት ቀራት እያሉ ዛሬም እንዳወሩ አሉ።

ሽብርተኝነት የዓለም ቋንቋ እየሆነ ነው ብሎ ያመነው ሕወሃት ሽብርተኝነትን ለራሱ የጥቃት በትርነት ለመጠቀም ዛሬ ነገ አላለም። ባለ በሌለ ሃይሉ በመፍጨርጨር አሉ የተባሉ ጋዜጠኞችን የሰባዊ መብት ተከራካሪዎችንና ለወገን ተቆርቋሪ ፖለቲከኞችን ባመለካከታቸው ልዩነት እና ስለጻፉና ስለተናገሩ ብቻ በሽብርተኝነት ስም ዘብጥያ ሲያወርድ፤ ሰላም ሲያደፈርስ፣ የሕዝብ ሃብት ሲያወድምና ምትክ የሌለውን ሕዝባችንን ሂዎት እየቀጠፈ ቀጥሏል። በዚህ በኩልም ምንም እንኳ ታላላቅ ዓለማቀፍ ሚዲያዎችና ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሽብር እየሰራ ያለው ራሱ ወያኔ መሆኑን ቢያጋልጡም፤ ፋሽስት ወያኔ ግን ሽብርተኛ መባሉ ሳይበግረው ዛሬም ሕወሃትና በረከት ሽብርተኞች እያሉ ወገናችንን በማንገላታቱ ገፍተውበታል። “የቡሄ እለት የደነቆረ…ን እያዜሙ ያልተደረገን ነገር በመደጋገም የተፈጸመ ለማስመሰል ሕዝብን ከማደንቆር አልታቀቡም።

ባሳለፍናቸው የፋሽስት ወያኔ የአገዛዝ ዘመናት ብዙ ነገሮች ተነግረውን ሁሉም ግን አልተሳኩም ህወሃትና በረከት ግን አሁንም ከማውራት አላባሩም። ራሱን ልማታዊ እያለ ለዘመናት እያወራ ያለው ወያኔ ልማት የሚለው በእርዳታና በልመና የተሰሩትን ጥቂት መንገዶች እንጅ የማሕበረሰባችን ነጻነት ልማት አያስፈልገውም። በበረከትና በሕወሃት እምነት በነጻነት መናገርና መጻፍ ልማት አያስፈልጋቸውም። በሀገራችን በየትኛውም ቦታ በመረጥነው ህጋዊ የስራ መስክ ተሰማርቶ ራስን ወገንንንና ሀገርን ማገዝ ልማት አያስፈልገውም። ሕዝባችን በትምህርት እንዲታነጽ በእውቀት እንዲበለጽግና የአመለካከት ጥራትና ለውጥ እንዲያሳይ ልማት አያስፈልገውም። በሕወሃትና በበረከት እምነት የሀገራችን ሕዝብ በነጻነት የሚያስተዳደርውን ራሱ እንዲመርጥ ሳይፈልግ ደግሞ መሻር እንዲችል ብቃት እንዲኖረው ለማድረግ ልማታዊ መሆን አያስፈልግም። በተቃራኒው ግን አሁንም ፋሽስት ወያኔና በረከት ልማታዊ መንግስት እያሉ ከማደንቆር አልቦዘኑም።

ልማታዊ መንግስት ነኝ ባዩ ሕወሃትና ስለተናገረ ያወቀ የሚመስለው በረከት ዛሬም ከመናገር አልቦዘኑም። ገበሬው በነሱ አመራር ሰላም እንዳገኘ በሰፊው እያወሩ ነው። ከዚህም እጅግ ዘለል ብለው “የኢትዮጵያ አርሶ አደር ወያኔ እስካሁን ባደረገለት በሚገባ የረካ ስለሆነ ‘ሰልፍ ውጣ በንለው ይወጣል። ተኛ ብንለው ይተኛል። ግፍ ብንፈጽም እንኳ ይሸከመናል እንጅ ምንም አይለንም” እያሉን ነው እነበረከት።

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት እኮ ሁሉም ነገር በመጠኑም ቢሆን ዛሬ በሀገራችን ከሚታየው ይልቅ  የተሻለ ነበር። በ1997 ዓ/ም የነበረው ገበሬ እኮ  ዛሬ ካለው በእጅጉ የተሻለ ነበር። በ1997 ዓ/ም የነበረው ገበሬ የነበረው ነጻነት እኮ ዛሬ የለም። ይሁን እንጅ ከዛሬው ይልቅ በ1997 ዓ/ም በመጠኑም ቢሆን በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኝ የነበረው ገበሬ ነው እንግዲህ በጊዜው በነበረው ምርጫ እነ በረከትን እንቅልፍ አሳጥቶ  አንቆራጦ በዝረራ የጣላቸው።

የዛሬው ገበሬማ የእለት ከእለት ስራው ለስደት መዘጋጀት ነው። ክልልህ አይደለም ውጣ እተባለ ጓዝ የሚጠቀልል ነው። አካባቢህ ለልማት ይፈለጋል እየተባለ ያለምንም ካሳ የሚገፋና የሚባረር ነው። የዛሬው ገበሬማ እኛን አልደገፍክም ተብሎ የሚገረፍ፣ ከማንፈልጋቸው ጋር ወግነሃል በሚል ሰበብ ዘብጥያ የሚወርድ፣ ብድር አልከፈልክም በሚል ልጆቹ እያዩ የቤቱ ጣራ የሚነቀልና አቅም እስከቻለ በዱላ የሚቀተቀጥ ነው። የዛሬዎቹ የሀገራችን ገበሬዎች በሉ የሚባሉትን ብቻ እንዲሉና እንዲያደርጉ ተደርገዋል። በራስ መተማመናቸው አብሯቸው አይደለም። ካነስ አነስ በረከት ስምኦን ለደረሰው የጎጠኛው መለስ ዜናዊ የለቅሶ ትእይንት በሚፈለገው መልኩ አልተወንክም በሚል እንኳ ስንቱ ገበሬ ነው ፍዳ መከራውን ያየው። ስንቱ ገበሬ ነው በዚህ ሰበብ የበሬ ግንባር ታክል የእርሻ ማሳውን የተነጠቀው። ይህ ገበሬ ነው እንግዲህ በሕወሃትና በነበረከት ድርጊት በሚገባ በመርካቱ ተኛ ሲሉት የሚተኛ ሰልፍ ውጣ ቢባል የሚወጣ እየተባለ የሚሾፍበት።

በረከት በዚህ ንግግሩ ሳያስበው የተናገረው አንድ እውነት አለ። የኢትዮጵያ ገበሬ ዛሬ ተኛ ሲሉት የሚተኛ፤ ውጣ ሲሉት የሚወጣ፤ አልቅስ ሲሉት የሚያለቅስ፤ የሚያደርገው አጥቶ ሕወሃትና በረከት በነዙበት የሽብርና ፍርሃት ቆፈን ተይዞ ሕወሃትን በመሸከም ትክሻው ጎብጦ ለመገላገል አጋዥ እየፈለገ መሆኑን ነው። ዛሬ ሕወሃትና በረከት አንድ ላምስት በሚሉት የስለላ መዋቅር ገበሬውን ጨምሮ መላውን የሀገራችንን ሕዝብ ወጥረው ይዘው ተኛ ሲሉት እንዲተኛ ውጣ ሲሉት እንዲወጣ ለማድረግ እየሞከሩ ይገኛሉ።

ባሁኑ ሰአት ፋሽስት ወያኔና የስለላ መዋቅሩ የኢትዮጵያን ሕዝብ አድርግ ሲሉት ለምን ብሎ ሳይጠይቅ እንዲያደርግ ከሚገደድበት ደረጃ ላይ አድርሰነዋል ብለው ያምናሉ። ስለሆነም በፍርሃት የሚደረገውን ሁሉ እየገለበጡ ገበሬው ባደረግንለት ረክቷልና የጠየቅነውን ያደርጋል እያሉ ደጋግመው በመጮህ ምኞታቸውን ያዛጋሉ ሕወሃትና በረከት። ከሕወሃት መቋጫ የሌለው ባዶ ምኞትና ከበረከት ረብ የለሽ ንግግር ጀርባ ያገጠጠው እውነት ግን የኢትዮጵያ ገበሬ አስራ አራት ዓመት አንገቱን ደፍቶ በ1997 ዓ/ም ምድር አንቀጥቅጥ በነበረው ምርጫ ወያኔን አንዘፍዝፎ እንደዘረረ ሁሉ፤ ያሁኑ በፍርሃት የተሸፈነው ማለቂያ የሌለው የሚመስለው ያገሬ ገበሬ ዝምታም እንደ እሳተ ገሞራ ፈንድቶ ሕወሃትን ከነወሬ አነፍናፊዎቹ ድባቅ የሚመታበት ወቅት ሩቅ አለመሆኑን ነው።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on January 31, 2014 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: