RSS

ለኢትዮጵያዊ ወገኑ ማነው?

27 Jan

 

ጥር 27 2014

ጥቂት በማይባሉ የአፍሪካ አገሮችና በመካከለኛው ምስራቅ ባጠቃላይ ደግሞ በዓለም ደረጃ የኢትዮጵያዊ ማንነቱ በእንግዳ ተቀባይነቱ እና በጀግንነቱ ሲለካ እንደኖረ አሌ የማይባል ሀቅ ነው። በሃይማኖት መጽሐፍትና ሌሎች ቀደምት ድርሳናት በጥልቀት ሲወሳለት የኖረው እንግዳ አስተናጋጅነቱ እና ጥሩ ጉርብትናው ዛሬ እንዳልነበር ሆኖ ለመስማት በሚዘገንን ርሃብ፣ ስደትና የነጻነት እጦት ሲተካ፤ ኢትዮጵያዊ በየሄደበት ከልክ በላይ ሲናቅና ሲገፋ፤ በሀገር ውስጥ እንኳ ከሰው በታች ተደርጎ ተቆጥሮ አንገቱን ቀና ለማድረግ እንኳ የመንፈስ ጥንካሬ አጥቶ ቁልቁል ሲሽቀነጠር አይዞህ ብሎ ከጎኑ የቆመ ማነው? ሲሆን ሲሆን የወገኖቹን የቀደመ በጎ ስራ አስታውሶ ካልሆነም በሰብአዊነት ለኢትዮጵያዊው እኔ አለውህ ያለው ማን ነው?

ከሩቅ ምስራቋ ጃፓን እስከ ላቲን አሜሪካዋ ሜክሲኮ፣ ከአውስትራሊያ እስከ ካናዳ፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ምራብ አውሮፓ ኖርዌ፣ ከአረቡ ዓለም መካከለኛው ምስራቅ አስከ ሙሉ እስያ በሁሉም ቦታ በሚባል መልኩ ይዘቱና ምክንያቱ ይለያይ እንጅ ኢጥዮጵያዊ ይሰቃያል፣ ይታሰራል፣ መብቱ ይረገጣል የሰቀቀን ኑሮን እንዲገፋ ይደረጋል። ከዚህ እጅግ በከፋ መልኩ ደግሞ በሀገር ውስጥ በህዝባችን ላይ የሚደረገውን ግርፋትና ሰቆቃ እስርና መጉላላት መፈናቀልና ሞት ስናስታውስ በእርግጥ ለኢትዮጵያዊ ወገኑ ማነው? እንድንል ያደርገናል።

ሀገር ውስጥ ከምትከወን በጣም ከትንሿ ኢፍትሃዊ ስራ ብንጀምር አስፋልት ዳር ቁጭ ብሎ በፀሓይ ሃሩር እየተቃጠሉ በነፋስ እየተገረፉ የአካባቢው አየር ያመጣውን ማንኛውንም አይነት ጠረንና አቧራ እየማጉ ጥቂት የድንች፣ የቃሪያ የቲማቲምና የመሳሰሉትን የአትክልት ውጤቶችን ለመቸርቸር ቢፈልጉ ወያኔ መሆን የግድ ይልዎታል። ጥራታቸው እየሞተ ካሉት የወያኔ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ስራ ለመቀጠር ቢፈልጉ፤ ይህም ወያኔያዊ መስፈርቶች አሉት። ለአንድ ክፍት የስራ ቦታ የሚጠይቀውን አሟልቶ እራስን ለገበያው እንደሚመች አድርጎ ማቅረብና በነፃ ገበያ ተወዳድሮ የገባያውን ውሳኔ መቀበል የሚለው ዓለማቀፋዊ ተቀባይነት ያገኘው ሂደት፤ በኢትዮጵያ በወረቀት ላይ ብቻ ያለ ለእርዳታ ሰጭ የውጭ ሀገራት ፎጆታ ብቻ የተቀመጠ እንጂ በመንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሚተገበር ነገር አይደለም እጅግ በጣም ቢያንስ አሁን ባለው የሀገራችን አሰራር።

ፋሽስት ወያኔ ልክ እንደ ዱር እንሰሳት የራሱን ወገኖችና እሱ እንደሚፈልገው የሚሰሩ የሚታዘዙና የሚተገብሩትን ብቻ በዙሪያው አሰባስቧል። ከወያኔ የዘር ሀረግ ውጭ የሆኑና የወያኔን የዘረኝነት አከሄድ ያልተቀበሉ የሚፈልጉትን አያገኙም። ያገኙም ካሉ የተለያየ ምክንያት ተለጥፎባቸው ይባረራሉ፤ እድለኛ ከሆኑ ማለቴ ነው አለዚያ ግን መጨረሻቸው ወህኒም ሊሆን ይችላል። ወያኔ የኔ ከሚለው የዘር ሀረግም ቢሆኑ ወያኔያዊ አሰራርን ማመንና መተግበር ይጠበቅበዋታል። ሰላማዊ እየተባለ የሚጠራውና በሀገር ውስጥ ያለው እንቅስቃሴም ቢሆን ይህን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር ይቅርና ሕዝብ ሰብስቦ በበቂ ሁኔታ ሃሳቡን ለመናገር አልቻለም። ይህ እንግዲህ ባለፉት የወያኔ አገዛዝ ዘመናት የታየ ሃቅ ነው። ታዲያ ይህን የተመለከተ አንድ ሰው ለኢትዮጵያዊ ወገኑ ማነው ብሎ ቢጠይቅ የሚያስደንቅ ሊሆን ይችል ይሆን?

ባሁኑ ሰአት ከጥቂት ምርጥ የወያኔ አቀንቃኞች በስተቀር በየትኛውም መመዘኛ ነፃነት የሚሰማው ትውልድ በሀገር ውስጥ እንዲታይ አየፈለግም ። በመሆኑም በኢኮኖሚ እራሱን የቻለ ዜጋ መብቱን ለማስከበር ወደ ሗላ የሚጎትተው ነገር እንደሌለ የተገነዘበው የወያኔው ዘረኛ አገዛዝ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት አንጻር ሁሉም ዜጋ በኢኮኖሚ እራሱን ችሎ እንዳይቆምና ሁሌም የወያኔ ትርፍራፊ ለቃሚ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ  ላለፉት የወያኔ የአገዛዝ ዓመታት በትጋት ሰርቷል አሁንም እየሰራ ይገኛል።

በጋንቤላ፣ ጉራ ፈርዳ፣ ቤኒሻንጉልና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች፤ ገዳማትንና የቀብር ቦታዎችን ጨምሮ ለልማትና ክልልህ አይደለም በሚል ሰበብ የሚደረገው የቦታ መንጠቅ፣  ከመኖሪያ ቅየ ማፈናቀል፣ ያለትክ ቦታ ይትም ግባ ብሎ ማባረር፣ ማንገላታትና መብት ገፋፋ ሲታይ በእርግጥ ሀገራችንን እየመራን ነው የሚሉት ወያኔዎች ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን አጠያያቂ ያደርገዋል።

ይህ ሁሉ ስቃይና መከራ፣ የመብት ጥሰትና ጭቆና እስርና ሞት አንገፍግፎት ሀገር ጥሎ የኮበለለው ዜጋ ደግሞ በሄደበት ሁሉ ሌላ ግፍ ሌላ ሰቆቃ ይጠብቀዋል። ድሮስ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዳ አይቀበለውም አይደል የሚባለው። በሄደበት አገር ሁሉ በተለይ ደግሞ በአረቡ ዓለም እንደባሪያ እንደአገልጋይ ከመታየቱም ባሻገር ግፉ በጣም ሲከፋ ደግሞ እሱ ሞቶ ሌሎች ሃብታሞች በህይዎት እንዲኖሩ አካሉ እየተቀደደ የውስጥ ብልቱ እየተመረጠና ተበልቶ እየወጣ በጥቁር ገበያ እየተቸበቸበ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ የፋሽስት ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ አንገፍግፏቸው በስደት በሱዳን፣ በኬንያ በጅቡቲ እና በሱማሌ ላንድ የሚገኙና ፋሽስት ወያኔ በተለያየ መንገድ ይታገሉኛል ብሎ የሚያስባቸውን ኢትዮጵያዊ ስደተኞች ከሀገሮች ጋር በመስማማትና በግዳጅ ወደ ሀገር በመመለስ የፈለገውን ሲገርፍ፣ ሲያስርና እያሰቃየ እንዳለ ሲታወቅ፤ በእርግጥ ለእኛ ያለና የቆመ ማነው? ያሰኛል።

እንግዲህ ይህን ሁሉ ስንመለከት ኢትዮጵያዊው ወገናችን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ መቀመጫ መላወሻ ያጣ ሁሌ ባካኝ ሁሌ በርጋጊ ሆኗል ለማለት እንችላለን። ከትምህርት እስከ ቢሮ ስራ፣ ከንግድ እስከ ግብርና ሁሉም በወያኔ የተያዘ አልያም የተነጠቀ ሆኗል። ህዝባችን የኔ የሚለው አንዳች ነገር የለውም ዛሬ። መኖሪያ ቦታው ነብረቱ ብቻ ሳይሆን እሱ ራሱ ወያኔ እንደሚያዘው ካልኖረ ተስፋ የሌለው ብኩን መሆኑ የሚታወቅና የተረጋገጠ ጉዳይ ሆኗል። ታዲያ ዛሬ ኢትዮጵያዊ ወገኑ ማነው? ቢባል ወገን የሌለው ባካኝ ተብሎ ቢመለስ ስህተት ይሆን?

የሆነው ሆኖ አንድን ትንሽ ድመት እንኳ ሁሉንም ማምለጫ በሮችና መስኮቶችን ዘግቶ ለመግረፍ በማይቻልበት ሁኔታ እንዴት ወያኔ ሁሉንም መንገዶች ዘግቶና ተቆጣጥሮ እኛን እንደፈለገ ሊያደርገን ቻለ? ከሀገር ካባረረንም በሗላ እንኳ በያለንበት እየመጣ ለማተራመስና የፈለገውን ለማድረግ ሞከረ? ብለን ብንጠይቅ መልሱ አጭር ነው፤ ትብብር ስለሌለን ነው። በተለይ ባሁኑ ጊዜ ሁላችንም ብቸኝነታችን እንጅ አንድነታችን አይታወቅም። ስንለያይ እንጅ ስንተባበር አንስተዋልም። ስለሆነም በየሄድንበት ለጥቃት የተጋለጥን ነን። ብዙ አጋጣሚዎቻችንን ብናስተውል በክፉ ዘመን የምንጯጯህ በሀሴታችን ግን የማንጠያየቅ ብዙዎች ነን።

እስርኤሎች አሁን የደረሱበት ደረጃ የደረሱት ቢጣሉም ቢጋጩም ቢገዳደሉም ስለሀገረቻው ግን እንድ በመሆናቸው ነው። ሀገራቸውን ለድርድር አያስገቡም። ሀገራቸው ከሁሉም በላይ ናት። ከዚያ ሁሉ እልቂታቸው መከራቸውና ስደታቸው በሗላ ዞረው የሚገቡባት ሀገር አገኘን ብለዋልና ስለሀገራቸው አንድ ናቸው። እኛም ልዩነቶች ሊኖሩን ይችላሉ ልንጋጭ ልንፋጭ ልንከራከር እንችላለን ነገር ግን ሀገራችንን በተመለከተ አንድ ሆነን ተባብረን እስካልተገኘን ድረስ ገና ወደፊትም የወያኔ መቀለጃ መሆናችን አይቀርም። ከእስከአሁኑ መከራ የባሰ ካለ ማለቴ ነው። ስለዚህም ፋሽስት ወያኔ ከጫነብን የመቧደን፣ የመከፋፈልና አንድ ዓላማ ይዞ የመቆም ችግር ለመዳን እንተባበር በማንኛውም ጊዜ አንረዳዳ ለኢትዮጵያዊ ወገኑ እኛ ለእኛም ወገኖች እኛ እንጅ ወያኔ አይደለምና። 

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on January 27, 2014 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: