RSS

ትላንትን ለመማሪያነት እንጅ ለበቀል አናስታውስ

23 Jan

ጥር 23 2014

ትላንት የዛሬ የጥሩም ሆነ የመጥፎ ትዝታችን መሰረት ነው። ትላንት የዛሬ ማንነታችን የተቦካበት እርሾ ነው። ያለትላንት ዛሬ የለም። ትላንት ከሌለ ልክ እንደ ሕጻን አልያም እንደ አዲስ ሰራጠኛ መደነጋገርና ግራ መጋባት ይነግሳል ምክንያቱም ትላንት የተሞክሯችን ማጠንጠኛ ነውና። ስለሆነም ትላንት መረጃ ነው። ትላንት ለዛሬ ግብአት አድርገን ልንጠቀምበት የሚገባ እውቀት ነው።

የትላንት ባለቤቶችና የዛሬ ማንነታችን መሰረት የሆኑት ቅድም ወላጆቻችንና እነሱ የኖሩበት ትላንት ለልጆቻቸው ለእኛና ለምንኖርበት ዛሬ ያስተላለፉልን ብዙ ማንነቶች አሉ። ጥንካሬያቸውና የትብብር ውበታቸው የሚጠቀሰውን ያህል አልፎ አልፎ ለምን የሚያስብሉ ድክመቶችና ያፍታ መለያየቶችንም አስመዝግበዋል። አንቱ የሚያሰኙዋቸውን የተለያዩ እድገቶችን እንደተውልን ሁሉ በዛሬው እይታ ሲመዘኑ ጥፋት የሚባሉ ውርሶችንም ትተውልን አልፈዋል። ይሁን እንጅ ይህ ሁሉ ለኛ የተላለፈ  የወላጆቻችን ውርስ ቢሆንም ያለፈና የተጠናቀቀ ታሪካችን በመሆኑ ለመረጃና እውቀት መሰረት ይሆን እንደሁ እንጅ ዛሬ ለመለያየት ወይም ለመጣላት በምንም አይነት መንገድ እንደምክንያት ሊጠቀስ አይችልም። ወይም ደግሞ ሆድ ያባውን ለመተግበር ለበቀል መረጃነት ሊጠቅም አይችልም። የትላንት የጋራ ወላጆቻችን አንደኛው በሌላኛው ላይ ጥፋት ሰርቶ ነበር ቢባል እንኳ በዚህ የተነሳ ጥፋት የተፈጸመበት ግለሰብ ልጆች ጥፋት በፈጸመው ግለሰብ ልጆች ላይ ዛሬ በቀል ለመፈጸም ቢፈልጉ መክንያታዊ አይሆኑም።

ትላንት ጥፋት ተሰርቶ ነበር ቢባል እንኳ ያን ጥፋት የሰሩት በነበረው የአስተዳደር ስርአት የታቀፉት የጋራ ወላጆቻችን ናቸው። ጥፋትም ይሁን ደስታ ትላንት ወላጆቻችን በጋራ ከውነውት በነሱው አልፏል። ነገር ግን ከነበረው ስርአት ጋር የተፈጸሙትን ስህተቶች ወይም ጥፋቶች ወደ አንደኛው ማህበረሰብ ክፍል በማንሸራተትና ጥፋተኛ በማለት የዚያን ማህበረሰብ ልጆች ዛሬ ለመቅጣት መነሳት ወይም አምርሮ ማውገዝ ስነ አመክኖዋዊ አይደለም። ትላንት አባቱ አጠፋ በሚባለው ጥፋት ምክንያት ዛሬ ልጁ ሊቀጣ አይችልም። ትላንት አባቴ ባባቱ ተበድሏል የሚል እንደ ወያኔ አይነት የዛሬ ባለጊዜ ዛሬ እኔ ልጁን እቀጣለሁ ቢል እንስሳነት እንጅ ምክንያታዊ ሊያደርገው አይችልም።

ፋሽስት ወያኔ ለራሱ የአገዛዝ ስርአት መራዘም ይጠቅመው ዘንድ ባለፈው ዘመን የተፈጸሙ ስህተቶችን በማጋነን ያልተፈጸሙ አፈ ታሪኮችንም በመቀባባት ጥፋት አድርጎ በማሳየትና አንደኛው የማህበረሰብ ክፍል ብቻውን እንደፈጸማቸው አድርጎ ከማቅረበም በላይ ለራሱ የዘር ፖለቲካ ይመቸው ዘንድ ሆን ተብለው የተፈጸሙ አስመስሎ በማቅረቡ ሌሎች ተጎጅ ነን ባይ ወንድሞቻችን ይህንኑ እንዲያቀነቅኑት ማድረግ ችሏል።

በዘረኝነት የታጠነው ፋሽስት ወያኔ ትላንትን እያጮኸ ሌሎችን በማጋጨት ዛሬን በሚፈልገው መልኩ እየኖረ ነው። ትላንትን በትልቁ እየሳለ ዛሬ እኛ እንዳንተባበርና አቅማችን ጎልቶ እንዳይታይ እያደረገ ነው። ይህ በመሆኑም ዛሬ እየወደቁ ያሉ ዛሬ እየሞቱ ያሉ እልፍ አእላፍ ዜጎቻችን ያላሳዘኑዋቸው አንዳንድ ወገኖች በትላንት ማንነታችን ላይ ታንቀው ተይዘው ትላንትን እያስነተሱ ይገኛሉ። ወያኔ በወገኖቻቸው ላይ ዛሬ የሚፈጽመውን ጉድ ማየት ተስኗቸው ትላንትን እያስታወሱ ዛሬ የበቀል ቢላ ሲስሉ ይደመጣሉ።

ትላንት ተሰርተዋል ብለው በሚጠቅሷቸው ስህተቶች ወይም ጥፋቶች ዘራፍ እያሉ ያሉት ፋሽስት ወያኔ እና አንዳንድ ወገኖች እያወቁም ሆነ ባለማወቅ ተፈጽመዋል እያሉ የሚጠቅሷቸውን ድርጊቶች ከዘመኑ ርቀት አንጻር የማስተዳደር አቅሙም ደካማ ሊሆን ስለሚችል ሊፈጸሙ ይችላሉ ብለው ለመገመት አለመቻላቸው፣ በዘመኑ ይኖር ከነበረው ማህበረሰብ ንቃተ ህሊና ዝቅተኛነትና በሗላ ቀር ባህሎችና ልማዶች ተጽእኖ  ስር የነበሩ ከመሆናቸው አንጻር አንዳንድ ስህተቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ከግምት ባለማስገባት ከዛሬው ከኛ ዘመኑ የአስተዳደር ስርአት ጋር በማወዳደር፤ ሀገራችን አንድነቷን ጠብቃ ድንበሯን አስከብራ እንድትኖር ያደረጉትን አባቶቻችንን አምርረው ሲያወግዙና የጀግንነት ስራቸውንም ለማጣጣል ሲሞክሩ ያታያሉ።

ሀገር በመምራትና ሕዝብ በማስተዳደር ሂደት ስህተቶች ሊፈጸሙ ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉ ስህተቶች ታዲያ በጊዜው በይቅርታ ሊታለፉ የሚችሉ እንጅ ዘመን ተሻግረው ጦር የሚያማዝዙ መሆን የለባቸውም። ይህ ማለት ግን ተፈጽመው የነበሩ ስህተቶች ካሉ እንኳ ይረሱ ለማለት አይደለም። ምክንያቱም ጠባሳን መርሳት አይቻልማ። ነገር ግን እነሱን በማስታወስና ለበቀል በመዘጋጀት ለዛሬ ጠላታችን ወያኔ ጊዜ ከመስጠት ይልቅ ያለፈውን ዘመን ችግር እንደትምህርት ወስደን ስህተቶቹ በድጋሚ እንዳይከሰቱ ለማድረግ ትብብራችንን አጠንክረን በጋራ ተላታችን ፋሽስት ወያኔ ላይ እንነሳ ለማለት እንጅ።

ፋሽስት ወያኔ ባለፈው ዘመን ተፈጽመዋል እየተባሉ ከሚጠቀሱት ይልቅ እጅግ የከፉ፣ ቅስም የሚሰብሩና ዘርን መሰረት አድርገው በእቅድ የተከወኑ በደሎችን በሁላችንም ላይ ፈጽሟል። እየፈመም ይገኛል። ገና በእቅድ ላይ ያሉና ሕዝብን የበለጠ የሚያለያዩና ሀገር የሚበትኑ ስራወቹንም ለመተግበር በማስፈራራት ላይ ይገኛል። በዚህ ስራው በመቀጠልም ባንዲት ሀገር ኢትዮጵያ የምንኖር ሁላችንም ሀገር በቀል የሆነ አንድ የጋራ ቋንቋ ከመጠቀም ይልቅ እንግሊዝኛን እንድንዋስ ለማድረግ ታግሏል። ለሁላችንም የጋራ ሀገር ተመሳሳይ ሀላፊነት እንዳይሰማን ለማድረግ ጥሯል። በጥቅሉ ሀገራችንንና ሕዝባችንን በተመለከተ እኔና አንተ እኛና እናንተ የሚሉ ከፋፋይ አስተሳሰቦችን ባአእምሯችን ለማስተጽ ሞክሯል። ይህንን በማድረጉ ሂደትም አጃቢዎችን ለማበራከት የጋራ ታሪካችንን በማጣመምና ያንደኛው ወገን ስራ አስመስሎ በማቅረብ ቲፎዞ ሰብስቧል። እነዚህ ቲፎዞዎች ናቸው እንግዲህ አሁን የወያኔን ህልም ለማስፈጸም ታሪክን በማስታወስ መማሪያ ከማድረግ ይልቅ ለበቀል ማስፈጸሚያነት እየጠቀሱ ያሉት።

በመለያየት ለበቀል መዘጋጀት ደግሞ አንድነትን በማዳከም ለዘላለም የወያኔ ባሪያነት ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። የቂም ሰንሰለት እየወፈረና እየጠነከረ ወደ ልጅ ልጆቻችን እንዲተላለፍ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ፋሽስት ወያኔ ያለተቀናቃኝ ሀገራችንንና ሕዝባችንን እንዳሻው እንዲያደርግ ምቹ ጊዜ ይሰጠዋል። በጥቅሉ የጋራ ታሪካችንን ከመማሪያነት ይልቅ ለበቀል ማስታወስና መለያየት ፋሽስት ወያኔ ላሰፈነው ዘረኛ አገዛዝና ማለቂያ ለሌለው ተንኮሉ እንደመተባበር ከመቆጠሩም በላይ ይህ አገዛዙ እንዲቀጥል መፍቀድ ይሆናል። ስለሆነም ትክክለኛውን ታሪካችንን ለልጆቻችን እንዳለ ለማስተማር እንጅ ለበቀል እንዲዘጋጁ ላለማድረግ ለራሳችን ቃል እንግባ። ታሪክ ጠቅሰን በመለያየትና በመወቃቀስ ጠላትን እናጠነክራለን እኛም እንጠፋፋለንና ጊዜው ሳይመሽ ከትላንቱ ተምረን ዛሬን በጋራ ጠላታችን ፋሽስት ወያኔ ላይ በመነሳት ለነገይቱ ኢትዮጵያ ጠንክረን እንስራ።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on January 23, 2014 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: