RSS

ወያኔዎችና ጨፍን ደጋፊዎች የንስሃ ቀናችሁ ገና አልመሸም

29 Dec

ሀገራችን ብዙ ጀግኖች የሀገር ኩራት የሆኑ የቁርጥ ቀን ልጆች የማፍራቷን አክል ስራቸው ሲታወስ ”ውሾን ያነሳ ውሾ” ተብለው የሚዘለሉ ብዙ ወራዶች አሳፋሪዎች ልጆችም ነበሯት። አሁንም አሏት። የሀገራችን የታሪክ ድርሳናት ወደ ሗላ ሲተረተሩ ሁለት ሶስቴ ቢወለዱ የሚባሉ ወገኖች እንዳሉን ሁሉ ምነው ባልተወለዱ የሚባሉም ሞልተዋል። በተለይ ሳያውቁ በስህተት ከተሰሩት ግድፈቶች ይልቅ እያወቁ በድፍረት፣ በማንአለብኝነትና በንቀት የተሰሩት ህሊናን እንዳደሙ ዘልቀዋል። የቁጭት እሳት በውስጣችን እንደጫሩ አሉ። የሀገራችንን የቅርብ ታሪክ የወያኔን ዘመን ብንመለከት እንኳ፤ በሀገርና በሕዝብ ላይ የተሰሩት በደሎችና የተፈጠሩት ችግሮች መቼ ሊፈቱ እነደሚችሉ ስናስብ ለምን ይህን አደረጉ? ከሚለው ጀምሮ የአመራር እርካታስ እስከምን ድረስ ነው? ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን።

እጅግ በሚገርም ሁኔታ ደግሞ ሀገር በመበተኑ ሂደት የተሳተፉ፣ ሃይማኖቶችንና ብሔረሰቦችን በማጋጨቱ ተግባር ግንባር ቀደም የነበሩ፣ ባንዲራን በማዋረዱና ድንበርን ቆርሶ በማስረከቡ ስራ ላይ የፊት መስመር ተዋናይ የነበሩ ቱባ ቱባ ወያኔዎች ባንዱ ወይም በሌላ ምክንያት ከዚህ በሗላ አንፈልጋችሁም ዞር በሉ ተብለው ሲባረሩ ስናይ፤ እነዚህ ተባራሪዎች ፋሽስት ወያኔ ለሚከውነው ሀገር የማውደም እንቅስቃሴ ለጊዜው ተቀዳሚ አገልጋይ እንዳልሆኑ፣ የእነሱ ወርቃማ ሀገር የመግደል ሕዝብ የማድማት ዘመንም ላይመለስ እንዳለፈና ፈጣኖች እየተኳቸው እንደሆነ እንረዳ እንደሁ እንጅ ሀገር የመግደል ሂደቱማ ሳይቋረጥ እንደቀጠለ ባይናችን እያየን ነው። ከዚህ በሗላ የእነዚህ ሰዎች እጣ ፋንታ እንግዲህ ቁጭት ይሆናል ማለት ነው። ወጥተውም ገብተውም ራሳቸውን መነቅነቅና መበሳጨት፣ ጸጉር ማሻሸትና መንጨት፣ ከዚያም ሲያልፍ ሱሰኛ በመሆን ራስን ቀስ በቀስ ለመግደል ትኬት በመቁረጥ ይጠናቀቃል። በዚህ መንገድ በፋሽስት ወያኔ የፕሮፓጋንዳ ማሽን ተታለው ወይም ጥቅም ገዝቷቸው ሕዝብ ያስቀየሙና አገልግሎታቸውን ጨርሰው የተጣሉ የትየለሌ ናቸው።

በጣም የሚደንቀው ግን የበለጠ ሀገራቸውን ለማድማት አሁንም ከፋሽሰት ወያኔ ጋር በመተባበር ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያን  ከጓዶቻቸው ስህተትና ተከትሎ ከመጣው መጥፎና አሳፋሪ ውጤቱ ለመማር አለመሞከራቸው ነው። ጉዳዩ አሳስቧቸው ከዚህ የጥፋት ቡድን ለመውጣት የሞከሩ ቢኖሩ እንኳ ቁጥራቸው በጣም ጥቂት መሆኑ ነው ክፋቱ። ወጣም ወረደ እህት እየተባሉ ሲወደሱ ከነበሩት የወያኔ ፍልፍል ድርጅቶች ብአዴን፣ ኦህዴድና ደህዴንም ሆነ አጋር ተብለው ከሚጠሩት ቁና ሙሉ ቡድኖች በአመራር ደረጃ ያገለገሉና ባሁኑ ሰአት ግን ተተፍተው የተጣሉ ቁጥራቸው ጥቂት አይደሉም። እነዚህ ድንበርተኛ ቡድኖች ከዋናው ቡድን ህወሃት ጋር ለስም ይሰለፉ እንጅ እንደ ቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ይዘውት በነበረው ሃላፊነታቸው ከህወሃት እውቅና ውጭ ምንም አይነት የውሳኔ ሰጭነት ሚና ለመጫወት የማይችሉ እንደነበሩ ይታወቃል። ከዚህ የምንረዳው እንግዲህ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴን እንዲሁም አጋር የሚባሉት ቡድኖችም ሆኑ ቁንጮዎቻቸው ከራሳቸው አመንጭተው በራሳቸው መንገድ ለመተግበር የማይችሉ ባለ ሙሉ አካል ድኩማን እንደነበሩና እና ከመጀመሪያውም ህወሃት የሚለውን ለማስፈጸም የተደራጁ እንጅ በራሳቸው ስልብ የነበሩ መሆናቸውን ነው።

በሕወሃት መሰሪ አካሄድ ሆን ተብሎ ስማቸው እየገዘፈ ሃላፊነታቸውና ውሳኔ ሰጭነታቸው ግን እየጫጨና እየሟሟ ከሚገኙት ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴንና አጋር ከሚባሉት ቡድኖች የሀላፊነት ቦታ የህወሃት አካሄድ አስአስቧቸው ከፍተኛ ጥፋት ከማድረሳቸው በፊት ከነሙሉ ክብራቸው ቀድመው የለቀቁ ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ነበሩ። በሀገራችንና በወገናችን ላይ እየደረሰ ያለው ውርደትና መደፈር፣ ግፍና በደል፣ ጉስቁልናና የበታችነት፣ መድሎና ፍርደ ገምድል ዳኝነት አሳስቧቸው ፊት ለፊት በመጋፈጥ ”አሁንስ ስራህ እና አሰራርህ ሳጥናኤልንና የሳጥናኤንል መሰለኝ” እያሉ ”የመጣው ይምጣ ገደል ግባ ብለው” በሚያኮራ ጀግንነት ህወሃትን የሗሊት ጥለው ወደፊት የተራመዱ አይብዙ እንጅ ነበሩ። የህወሃትን ግንፍልተኘነት በማቀዝቀዝ የተመዘነ ስራ እንዲሰራ ለማገዝ ምለው፣ ሀገርና ሕዝባቸውን ባለ በሌለ አቅማቸው እስከ መጨረሻው ለማገልገል ተስለው ቢሰለፉም በህወሃት አጉራ ዘለልተኝነት ሳይሳካላቸው በመቅረቱ የተነሳ ተገደው ይህን አገዛዝ ሳያስወግዱ ክንዳቸውን እንደማይንተራሱ ለራሳቸው ቃል ገብተው ጥለው የወጡና ራሳቸውን ለትግል እያዘጋጁ ያሉ የቁርጥ ቀን አናብስቶች አይብዙ እንጅ ዛሬም አሉን።

በተቃራኒው ግን ከዚህ የተሻለ ለውጥ ከእንግዲህ ሊመጣ አይችልም በሚል የጨለምተኝነት መንፈስ ታጥረው ሕወሃት ሽህ ዓመት ንገስ እያሉ የህልም ኬካቸውን ሲገምጡ የነበሩ የብአዴን፣ የኦህዴድ፣ የደህዴንና አጋር የሚባሉት ቡድኖች ሃላፊዎች ድንገት በራሱ በሕወሃት ሰዎች መካከል በተነሳ የጥቅም ፍትጊያ በተነሳ ማእበል በሀፍረት ወደ ጥልቁ የወረዱ ብዙዎች ናቸው። ”እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው” በሚለው ብሂል ተስበው በፍጹም ልባቸውና መንፈሳቸው ለህወሃት ሲገዙ የነበሩ የነዚህ ቡድኖች ሃላፊዎችና ደጋፊዎች ድንገት የአገልግሎት ዘመናቸው አልቆ ተላምጠው ተላምጠው አታስፈልጉም ተብለው በውርደት የተተፉ ብዙዎች ናቸው። ትልልቆቹ ገዥዎች በጉልህ ይታወቁ እንጅ ዛሬም እነዚህ በውርደትና በሃፍረት ከህወሃት የሚተፉ የስም ኢትዮጵያዊያን የትየለሌ ናቸው። ይዘውት በነበረው የሃላፊነት ቦታ ራሳቸውን እንጅ ወገናቸውን ለማገልገል ተነሳሽነት ያልነበራቸው እነዚህ ቡድኖችና ግለሰቦች እንኳንስ በህወሃት ሲባረሩ ይቅርና ባይባረሩ እንኳ በሰፊው ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ዘንድ መጥፎ ስራቸው ታውቆ ባንዳ ተብለው የሚጠሩና ክብረ ቢስ ናቸው። ስለሆነም ማንኛችንም ባሁኑ ሰአት ከወያኔ ጋር ተባብረን እየሰራን ያለን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በሕዝብ ዓይን እይታ ስር መሆናችንን ላፍታ እንኳ ልንዘነጋው አይገባም።

ዛሬ በተቀመጥንበት የስልጣንና የአመራር ቦታ ሆነን እንደግለሰብም ሆነ እንደ ፓርቲ እያገለገልነው ነው የምንለውን ሕዝብም ሆነ ሀገራችንን እያገዝን ካልሆንን በፍትህ አደባባይም ሆነ በታሪክ ተጠያቂ ከመሆን አናመልትም። ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሳይቀር የምናመሰግናቸውና የምንወቅሳቸው የያኔዎቹ ሀገር መሪዎችና ሕዝብ አስተዳዳሪዎች በዘመናቸው ከውነውት ባለፉት ስራቸው መልካምነትና ደካማነት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል። መልካም ስራ ራስን ቤተሰብን አካባቢንና ሀገርን የማኩራቱን ያህል መጥፎና ተቀባይነት የሌለው ስራ ደግሞ ቤተሰብንም ሆነ ወገንን አንገት ያስደፋል። በጣሊያን ወረራ ወቅት ሀገራቸውን ክደው በባንዳነት ሲያገለግሉ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ልጆች የሆኑት እንደ ጎጠኛው መለስ ዜናዊ አይነቶቹ በሗለኛው ዘመን ላቀነቀኑት ጠባብነትና አንድነትን ጥላቻ የበቁት፤ ወላጆቻቸው በፈጸሙት የሀገር ክህደት ምክንያት ክብር አጥተው ተንቀው በማደጋቸው በደረሰባቸው ሀፍረትና መሸማቀቅ የተነሳ በተፈጠረ የመንፈስ ስብራትና በዚሁ ሳቢያ እያደገ በመጣ የበቀል ስሜት የተነሳ እንደሆነ ይታመናል። ስለሆነም ወያኔዎችና የወያኔ ጭፍን ደጋፊዎች ሆይ በሀገራችሁና በሕዝባችሁ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሳችሁ በፊት ወይም ደግሞ በፋሽስት ወያኔ አገልግሎታችሁን ጨርሳችሗል ተብላችሁ ተመጣችሁ ተመጣችሁ ቱፍ ከመባላችሁ በፊት እና ራስንም ከህሊና ወቀሳ ከፍርድ ወንበርም ሆነ ከታሪክ ተወቃሽነት ለማዳን፣ ልጆቻችሁንና ወገናችሁንም ዘመን ከማይሽረው ሃፍረትና መሸማቀቅ ለማውጣት ዛሬ እየሰራችሁት ካለው የሀገርን ክብር አስደፋሪ፣ ታሪክ አጥፊ፣ ወገንና ሕዝብ አሳፋሪ ስራችሁ በቃን ብላችሁ በይቅርታ ወደ ሕዝባችን ተመለሱ። ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን፤ ባሁኑ ሰአት ከምንጊዜውም በላይ በፍጥነት ለድል እየገሰገሰ ያለው የኢትዮጵያዊያን ትግል አሸንፎ አመራሩን በሚጨብጥበት ወቅት ለፍርድ የምትቀርቡ መሆናችሁን ከወዲሁ ልናሳውቃችሁ እንወዳለን።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on December 29, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: