RSS

መብት ረገጣውና ግድያው መልኩን ቀይሮ ቀጠለ እንጂ አላባራም

18 Dec

ይኸነው አንተሁነኝ

ታህሳስ 18 2013

በከተማው መሃል ስብሰባ ሊያስብል የሚችል ያህል ሕዝብ ተከማችቷል። ሁሉም በስሜትና በንዴት ይናገራል፣ ይጮሃል አንዳንዴም ይባርቃል። ራቅ ብሎ ለሚመለከታቸው እርስ በርሳቸው የሚደማመጡ እንኳን አይመሰሉም፤ ሁሉም ራሱን እያዳመጠ መናገር መናገር መናገር ብቻ። በመሃሉ የፋሽስት ወያኔ ታጣቂዎችና ወታደሮች በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎችና ወደ ተሰበሰበው ሕዝብ አካባቢ መታየት ጀመሩ። አለፍ ብሎም በትልቅ ካሚዮን ሙሉ የተጠቀጠቀ የወያኔ ጦር ተስተዋለ። ነገሮች ባልተጠበቀ ሁኔታና ፍጥነት መለዋወጥ ጀመሩ። ይህ በእንዲህ እንዳለ በማን እንደተገደሉ የማይታወቁ ስምንት አስከሬኖችን የወያኔ ጦር ከሌላ መኪና ላይ ሲያወርድ ታየ። ሁሉም አስከሬኖች በከተማው መሃል ተሰብስበው ሲነጋገሩ የነበሩት ማሕበረሰብ አባላት የሆኑ የደገኞች ነበሩ። ይህ የሗለኛው የወያኔ ጦር አስከሬን የማውረድ እንቅስቃሴ በግልጽና በሕዝብ መሃል መደረጉ ሆን ተብሎ የተከወነና በከተማው መሃል የተሰበሰበውን ደገኛ ሕዝብ ስሜት የበለጠ ለማናር እንደነበር በሗላ ላይ ታውቋል። ይህ ከሆነ በሗላ ተሰብሳቢው ሕዝብ  ቆንጨራ፣ መጥረቢያና የመሳሰሉትን አይነት ቤት ሰራሽ ጥቃት መሰንዘሪያ መሳሪያ ለማምጣት እንዳበደ በየቤቱ ተበተነ። በካሚዮኑ ውስጥ ሲታዩ የነበሩ ወታደሮች ከመኪናቸው በመውረድ የተፈጠረውን አደገኛ ሁኔታ ሊያበርዱት ነው ተብሎ ሲታሰብ በደገኞቹ እየተመሩ ቁጥር እንድ ጥቃት ዘንዛሪዎች እነሱ ራሳቸው ሆኑ። ያለ ርህራሄ የከተማውን ኗሪ ሕዝብ በጥይት ይቆሉት ጀመር። መኖሪያ ቀያቸውን ማደሪያ ጎጇቸውን በእሳት በመለኮስ መሮጫ መንገድ መደበቂያ ፉካ አሳጥተው ያርበደብዳቸው ገቡ።

በሌላው የከተማዋ ገጽ ደግሞ ሁኔታው እጅግ የተለየና አስከፊ ነበር። ጋምቤላ ከተማ በደም ታጠበች ሊያስብል በሚችል መልኩ አካባቢው በደም ርሷል። በቤታቸው ውስጥ አልያም በበራቸው ደጃፍ ወይም ደግሞ ነፍስ ይዟቸው ነፍስ ለማትረፍ በመሮጥ ላይ እንዳሉ በፋሽስት ወያኔ ጥይት ተመተው የወደቁና በደም የራሱ አስከሬኖች፤  ምን እንደተፈጠረ የማያውቁና ጓደኛቸው ወደ ሮጠበት አቅጣጫ ዝም ብለው የሚሮጡ ግራ የገባቸው ኗሪዎች፤ ማን እንዴትና በምን ሁኔታ እንደተፈለገ ያልገባቸውና ሁኔታውን አንዳመጣጡ ለመቀበል የወሰኑ ነገር ግን ይህችን የጭንቅ ቀን በሰላም እንዲያሳልፋቸው አምላካቸውን የሚማጸኑ እናቶችና ሕጻናት ቅልቅል ዋይታ፣ የውሾች ጩኸትና የእንስሳት ማንቋረር ከወያኔ ወታደሮች ጥይት ድምጽ ጋር ተቀላቅሎ እለተ ምጽአት የደረሰች ያክል ጋምቤላ አስፈርታ ታየች። ልክ የዛሬ አስር ዓመት በታህሳስ የመጀመሪያ ሳምንት 1996 ዓ/ም።

ዛሬ ሁሉም ነገር አልፎ ሲታይ ቀላል ቢመስልም በጊዜው የፋሽስት ወያኔ ወታደሮች  ያደረሱት ጥፋትና ጥፋቱን የፈጸሙበት መንገድ ልክ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሂትለር ወታደሮች እስራኤላዊያኑን ያጠቁበትን አይነት ነበር /ምንም እንኳ በሗላ ለይ ያን ሁሉ ግድያና የዘር ማጽዳት ወንጀል ወደ ጎሳዎች ግጭት ዝቅ በማድረግና በማመካኘት እኛ ገላጋይ ነበርን በማለት ከደሙ ንጹህ ነን ለማለት ቢሞክሩም/። በዚያ አሰቃቂ ጭፍጨፋም ሁሉም ከአኙዋክ ወገን ብቻ የሆኑ 424 ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑና ወጣት ወንዶች በግፍ ተጨፈጨፉ። ሌሎች ብዙዎችም የአካል ጉዳተኛ ሆኑ። በሽዎች የሚቆጠሩ አኙዋኮች ተሰደዱ። የአኙዋክ ሴቶችና ልጃገረዶች በፋሽስት ወያኔ ወታደሮች ተደፈሩ። ከ400 በላይ የአኙዋክ ቤቶች ከነ ሙሉ ንብረታቸው እንዲቃጠሉ ሆነ።

በወያኔ ሃይሎች የተመራውና ይህን ሁሉ ጥፋት በአኙዋኮች ላይ በግፍ በመፈጸም የአኙዋክን ዘር የማጽዳት አሰቃቂ ዘመቻ ካጠናቀቀ በሗላ፤ ጉዳዩን ለማጣራት የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ የደረሰበትን መደምደሚያ በመሻርና በሚፈልገው መልኩ በማስገልበጥ ፋሽስት ወያኔ በአኙዋክ ወገኖቻችን ላይ ታሪክ የማይረሳው ሸፍጥ በመፈጸም እንደፈለገ የሚያዛቸውን ወታደሮች ተከላከለ። እናም የንጹህ አኙዋክ ወገኖቻችን ደማቸው እስካሁንም ደመ ከልብ እንደሆነ ፍትህ አጥቶ የፍትህ ያለህ እንዳለ አለ። በግፍ የወደቁት የአኙዋክ ወገኖቻችን ደም ዛሬም አፍ አውጥቶ እየጮኸ ነው። የፍትህ ያለህ የእውነት ያለህ እያለ ነው። ልክ ያዛሬ አስር አመት በዚህ ወቅት በግፍ በጋምቤላ መንደሮች፣ በጋምቤላ ጫካዎች ወድቀው ያየናቸው እነዚያ ረዣዥም ጥቃቁር ክንዶች ዛሬ የኛን ርዳታ ይሻሉ። እነዚያ ያለ ደጋፊ ያለ ተከላካይ  በየሳሩ እጥፍጥፍ ብለው ተደፍተው ያስተዋልናቸው ግማሽ ራቁት ጥቁር እንቁ አስከሬኖች ፍትህን ከኛ ይሻሉ። ዛሬ ኢትዮጵያዊያን ሁላችን ለጣያቄያቸው መልስ ልንሰጥ የግድ ይለናል። ፋሽስት ወያኔ ጉዳዩን “ዴድ ፋይል” ብሎ ከወረወረው ቆይቷልና።

ይሁን እንጅ በዘር ልክፍት የተነካው ፋሽስት ወያኔ ግን ዛሬም ካስር ዓመት በሗላ እንኳ በዘር ሰበብ የሚያፈናቅላቸው በዘር ሰበብ የሚገድላቸው በዘር ሰበብ የሚያሳድዳቸው ገምቤላዎች ቁጥር እንደጨመረ ነው። ዛሬም እንደ ያኔዎቹ አኙዋኮች ለምን እንደሚፈጸም ምክንያት የታጣላቸው ወያኔያዊ ግፎች ፋሽስታዊ ግድያዎች በጋምቤላ መንደሮችና ፈፋዎች ቀጥለዋል፡፡ልክ በጋምቤላ እንደታየውም አንድን ዘር ከሌላኛው ዘር ጋር ለማገጨት በማሰብና በዘረኝነት በተሞላ ርኩስ መንፈስ በመመራት ይህ የናንተ ክልል አይደለም ውጡ እየተባለ ለዘመናት ያፈሩት ሙሉ ሃብታቸው እየተዘረፈ ከሚኖሩበት ሀገራቸው የተባረሩ የተገረፉ የተገደሉ አማሮች ጉራጌዎችና ኦሮሞዎች ቁጥር ጨመረ እንጅ ቀንሶ አልታየም።

ይህን የመሰለውን በዘረኝነት የተጠመቀ ዘረኛ አገዛዝ፣ በጎጠኝነት የታጠረ ቡድን የግፍ ስራዎችን በማጋለጥ ላይ የሚገኙ የዴሞክራሲ ጠበቃዎችን፣ የፍትህ ተሟጋቾችንና ጋዜጠኞችን ፋሽስት ወያኔ ከማሳደድ ከማሰርና ከመግደል አልተመለሰም። ዛሬም እንደትላንቱ ግፍና በደሉ ቀጥሏል። ማለያየቱና ማበጣበጡ አይሏል። ግድያውም ሳይቋረጥ እንዳለ ነው። ዛሬም የተለያዩ ማሕበረሰብ ወገኖቻችን በቋንቋቸው በመሳሳብ እንዲደራጁና እንዲቧቀሱ ፈሽስት ወያኔ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ነው። ዛሬም ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ይዘመራል። በመቻቻል አብሮ ከመኖር ይልቅ በመናናቅ መበታተንን የሚያነግስ ድንበርተኝነት ይሰበካል። እናም ታዲያ ዛሬም ፋሽስት ወያኔ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በብሔረሰብ ስም ሕዝብን የሚያጠፋፋ ሀገርን የሚያዋርድ ስራ ከመስራት አላባራም። የእለት ከለት ስራዬ ብሎም እየተገበረው ይገኛል።

የዴሞክረሲ ታጋዩ፣ ለአንድነት ለእኩልነትና ለሰላም የቆመው ሃይል፣ ለፍትህ እየታገለ የለው ክፍል እንዲሁም ሰፊው ገፈት ቀማሽ ኢትዮጵያዊስ ይህን አድርግ ወይም ያን ያድርግ ተብሎ የሚመከርበት ወይም የሚታዘዝበት ወቅት ነውን? አይደለም። ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የረዘመው የወያኔ አገዛዝ ምን መቼና እንዴት  ማድረግ እንዳለብን ከማስተማር በላይ አሳውቆናልና። ስለሆነም አሁንም በጋምቤላና በሌሎችም የሀገራችን ክፍሎች እየሞተ ያለው ወገናችን በሲቃ ድምጽ እየጠራን ነውና ወገንተነነታችንን እናሳየው። ትብብራችን ከቃል በላይ ገዝፎ እንዲታይና ትርጉም ያለው የሚታይ እንቅስቃሴ እንዲሆን ያለ ምንም የጊዜ ቀጠሮ ዛሬውኑ ከግንቦት 7 እና ከሌሎችም የተቃውሞ ንቅናቄዎችና ሃይሎች ጋር ትብብር በመፍጠር ወያኔን የማስወገድ የተግባር እንቅስቃሴ ውስጥ እንግባ።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on December 18, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: