RSS

ኢትዮጵያ ትላንትናና ዛሬ

15 Dec

ይኸነው አንተሁነኝ

ታህሳስ 15 2013

ይህ ጊዜ የመበታተንና የመለያየት ጠላት፣ የፋሽዝም ቅስም ሰባሪ፣ የዘመኑ ፋሽስቶች የሌት ቅዠት፣ የመቻቻልና የዲፕሎማሲ አባት፣ የአዱዋ አናብስቶች መሪ የነበሩት እምዬ ዳግመዊ አፄ ሚኒሊክ መቶኛ ሙት ዓመት የሚከበርበት ሳምንት ነው። እምዬ አፄ ሚኒሊክ፤ ከነበረው የቀደምት አባቶቻችን የአስተዳደር ስርአት ውጭ ከሰባ ዓመታት በላይ በባላባቶችና መሳፍንቶች ተከፋፍላና ተቦጫጭቃ ስትበላ የነበረችውን ኢትዮጵያ እንደገና ወደ ቀደመው ክብሯና አንድነቷ ለመመለስ አቅደውና ጀምረው ሳይቋጩት ያለፉትን የአፄ ቴዎድሮስን ራእይ የተገበሩ፤ ሀገራችን ከውጭው ዓለም ጋር ሊኖራት የሚገባውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተገቢው መንገድ ለማስኬድ የታተሩ፣ የዘመኑ የዓለም ቴክኖሎጂ ወደ ሀገራችን እንዲገባና እንዲስፋፋ በእጅጉ የጣሩ ከመሆናቸውም በላይ ሀገራችንን ወደ ቀደመው ቅርጿ በመመለሱ በኩል በዋናነት የሚጠቀሱ የትላንትም ሆነ የዛሬ ኩራት ናቸው- እምዬ አጼ ሚኒሊክና የዚያ ዘመኑ አስተዳደራቸው።

በሌላ መልኩ ፋሽስት ወያኔ ከቀደመው የአባቶቻችን የአስተዳደር ስርአት ፍጹም በተለየና ባፈነገጠ መልኩ ጥላቻንና መለያየትን የሰበከና በመስበክ ላይ ያለ፤ በአንድነት ስም መገነጣጠልን እያስተማረ ያለና ለዚህም ሽንጡን ገትሮ ያለ ሀፍረት የሚከራከር፤ ሰለ ፍቅር በሚል በቂምና በጥላቻ በተመረዘ አስተሳሰብ ድንበርን አሳልፎ በመስጠት ወይም በመሸጥ የሀገራችንን ክብር ያስደፈረ፤ በተዛባና የሀገርን ጥቅም ባላስቀደመ መልኩ በተቃኘ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተለከፈ፤ በፋሽስት አመለካከት የሚመራ አገዛዝና በዚሁ ሳቢያም ዜጎችን ለርሃብና ለስደት የዳረገ እጅግ ጠባብና ጎጠኛ አገዛዝ በመሆኑ ዛሬም ሆነ ወደፊት ስናፍርበት የምንኖር ነው ፋሽስት ወያኔና አገዛዙ።

በመሆኑም የእምየ ሚኒልክ መቶኛ ሙት ዓመት ሲታወስ በደማቸው ያስከበሯት ሀገራችን፣ ከፍ የደረጉት ባንዲራችን፣ ሀገርና ሕዝብ ወዳጂነታቸው በኩራት እንደሚታወስ ሁሉ ዛሬ እሳቸውና ስርአታቸው ያቀኗትን ሀገር የራሳቸው አቋም በሌላቸው ባዶ ባለ ራእይ ነን በይ ፈስስቶች ለመበታተን ጫፍ የደረሰች ሀገራችን፣ የተዋረደ ባንዲራችን፣ የተደፈረው ማንነታችንና ፋሽስታዊ አገዛዙን በሀዘንና በሃፍረት አብረን የምናስታውሰው ይሆናል።

ከብርና ኩራትን፣ ሃያልነትንና አይደፈሬነትን፣ ሀገራችንን የአፍሪካና የጠቅላላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት ያደረጉ፣ ለሀገርና ለሕዝብ ቅንአትን ያስተማሩና የተገበሩ አባቶቻችንን ገድላቸውን እያወሳን በደስታ የማስታወሳችንን ያህል፤ እንደ ፋሽስት ወያኔ አይነት ዘረኛ አገዛዞችንና የዳቦ ቅርጫት ስትባል የነበረች ሀገራችንን ወደ ቁጥር አንድ የሁል ጊዜ ርሃብተኛነት የቀየሩ፣ ሕዝባችንን ያለልዩነት ስደትን እንደ አማራጭ እንዲመለከት ያደረጉ፣ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል ተዘዋውረን እንዳንሰራ ገደብ የጣሉ፣ በየዓመቱ በዚህ ወቅት በብሔር ብሔረሰብ ስም ባዶ ከበሮ በመደለቅ አንደኛው ብሔረሰብ ሌላኛውን እንዳያምንና በጠላትነት እንዲመለከት መንገድ የተረጉና የተገበሩ፣ ስለራሳቸው እና ስለ ሆዳም ተላላኪወቻቸው በቀር ስለሀገርም ሆነ ስለሕዝብ የማያስቡትን ከንቱዎችን ደግሞ በሀዘን ማስታወሳችን ግድ ይሆናል።

ስለሀገራቸውና ሕዝበቸው ሲሉ በሞቱት ንዑድ ክቡር አባቶቻችን እግር የመጡብን ባለ ራዕዩ እና የፋሽስተ ወያኔ አገዛዝ የኢትዮጵያን ተሰሚነትና ክብር ለማዋረድ፣ ሉአላዊነቷን ለማስደፈርና ሕዝቦቿን ከቀደመው ክብራቸው ዝቅ ለማድረግ የተጉ፤ ባንድ ወቅት ለአፍሪካዊያን ሀገሮች ነጻ መውጣት እገዛ ስናደርግ የነበርን ኩሩ ሕዝቦች እንዳልነበርን አሁን በነሱ እንኳ እንድንናቅ እገዛ የሚያደርጉ፤ አለን ወይም አመረትን እያሉ የሚሞካሹበትን የኤሌክትሪክ ሃይል ለኛ በቅጡ ሳይሞቀንና ሳንገለገልበት ከራሳችን ይልቅ የሌላው ሀገር ሕዝብ የተሻለ ይገባዋል በሚል መንፈስ አሳልፈው የሚሸልሙ እኛን ግን በጨለማ የሚተው፤  እኩልነትን፣ መቻቻልንና አብሮ መኖርን፣ ሰብአዊ መብትንና ዴሞክራሲን በወረቀት ላይና በአፋዊ ቃል በስተቀር በተግባር የማያውቅ እጅግ ጠባብ አገዛዝ በመሆኑ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን አይመጥንም አይገባንምም  ሊወገድም ይገባዋል።

ፋሽስት ወያኔን በትላንትናው መነጽር ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው እንግዲህ የሀገራችንን ድንበር ማስከበር ያልቻለ እንዲያውም በተቀነባበረ መንገድ ለሌሎች አሳልፎ መርቆ የሚሰጥ፣ ሉኣላዊነታችንንና ባንዲራችንን ያዋረደና ያጣጣለ እንዲሁም ሕዝባችንን በሀገር ውስጥም ሆነ ውጭ ከሰው በታች ሆኖ እንዲገዛ ያደረገና በዝምታ የፈቀደ ጉጅሌ ነው። ስለሆነም እኛ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ሳምንት  የኩራታችን መሰረት፣ የቅኝ ግዛት በትር፣ የአንድነት አባት የሆኑትን እምዬ ሚኒልክን መቶኛ ሙት ዓመት ስንዘክር፤ እነሱ ወዳስረከቡን አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያ ለመመለስ በዘፈንና በከበሮ ድለቃ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት እያከበርኩ ነው እያለ የሚቀልደውን ፋሽስት ወያኔን በተባበረ ክንዳችን ደቁሰን ለማስወገድ አንድነታችንን የምናጸናበትና የተጀመሩ ትግሎችን አጠናክረን ለመቀጠል ወገባችንን ጠበቅ፣ እይታችንን ሰብሰብ በማድረግ ሃይላችንን በሙሉ ፋሽስት ወያኔን ለማስወገድ የምናስተባብርበት ሳምንት እንደሆነም ልናስታውስ  ይገባል እንላለን።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on December 15, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: