RSS

ትግላችን የሞተን ከመሸኘት፣ ለታሰረ ከመጮህ በላይ እና ዘላቂ ይሁን

08 Dec

ከይኸነው አንተሁነኝ

ታህሳስ 8 2013

ኢትዮጵያዊያን በዓለም ዙሪያ ካሉትም ሕዝቦች በተለየ መልኩና ላቅ ባለ መንገድ ሀገራችንን እንደምንወድ ይታወቃል። የሀገራችን ሉአላዊነት ሲደፈር ክብሯ ሲነካ አንድነቷ ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ እገሌ ከገሊት ሳይባል ሁሉም በያለበት ያቅሙን ሲያደርግ ኖሯል እያደረገም ይገኛል። የወገኖቻችን ማንነት ሲናቅ ሲዋረድም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በያለበት ጮሗል፣ አልቅሷል፣ አዝኗል። ከሰላማዊ ሰልፍ እስከ ገንዘብ ማዋጣት በመተባበርም የተፈጠረውን ችግር ለማስወገድ ከፍተኛ ርብርብ ሲያደርግ እንደነበር የሚታወቅ ነው። አሁንም በሳውዲ አረቢያና በአካባቢው እየደረሰ ላለው የወገን እንግልትና ግድያ በከፍተኛ ሁኔታ በቁጣ ገንፍሎ በመውጣት ችግሩን የዓለም ማሕበረሰብ እንዲያውቀውና ወገኖቻችን እየደረሰባቸው ካለው ስቃይ እንዲላቀቁ ለማድረግ ለወገኖቻችን አርነት ከፍተኛውን ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል።

በእርግጥ ይህን ሁሉ ትግል ማድረግ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን እጅግ በጣም ትንሹ ተግባራችን ሊባል ይችላል። ምክንያቱም እኛ ኢትየጵያዊያን ነና እኛነታችንን አዝለን ዓለም ለዓለም የምንንከራተት፤ አኗኗራችንን፣ አበላላችንን፣ አለባበሳችንን፣ ማንነታችንን ተሸክመን በሌሎች መሃል በራሳችን መንገድ የምንኖር ንዑድ ሕዝቦች፤ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን ነብርስ ዥንጉርጉርነቱን ሊቀይር ያቻለዋልንን በተግባር እየመሰከርን አረንጋዴ ቢጫና ቀይ ባንዲራችንን በአናት በልባችን  ጠምጥመን እንደ ቀስተ ደመና ደምቀን ከርቀት የምንታይ፤ ሰላምታችን፣ ሰርጋችን፣ ሀዘናችን ተለይቶ ልዩ ያደረገን፤ የወገናችን ሀዘንና መከራ ደማችንን አፍልቶ አስጓርቶ የሚያስነሳን ክቡር ቀናኢ ሕዝቦች ነን ኢትዮጵያዊያን። ለዚህም ነው ልክ እንደ ራሔል መሪር ለቅሶ የወገኖቻችን ዋይታ በዓለም ሲናኝ ተረጋግተን ለመቀመጥ ያቃተን። እልፍ ዘመናትን ተሻግሮ ስለፍትህ ሲንጠረጠር እንደነበረው በግፍ እንደፈሰሰው የአቤል ደም በደረቅ አስፋልት ላይ ያለገደብ የፈሰሰው የወገኖቻችን ንጹህ ደም ታዘበን፣ ወቀሰን፣ አፍ አውጥቶ ጠራን እናም አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል እንደሚባለው ዓለምን በሰላማዊ ሰልፍ በእሪታና በዋይታ ሞላናት።

ይህ አይነቱ ትግላችን እንግዲህ ውጤታማም ይሁን አይሁን የተፈጠረን ወቅታዊ ችግር ለሌሎች ለማሳወቅና ጊዜያዊ እገዛን ከያቅጣጫው ለማሰባሰብ አይነተኛ መንገድ ሊሆን ያችላል እንጅ ችግሩን ከመሰረቱ ሊቀርፈው አይችልም። ችግር እየፈጠረ ያለውን አካል ለማጋለጥና ለማሳጣት መልካም ዘዴ ሊሆን ይቻላል እንጅ በዘላቂ መፍትሄነት ሊወሰድ የሚችል ነገር አይለም። እንዴውም እኛ ኢትዮጵያዊያን የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ሲፈተሽ ትብብራችን ጩኸታችንና ለቅሷችን የተፈጠረውን እሳት ከማጥፋቱ ላይ እንጅ እሳቱን ማንና እንዴት ፈጠረው ብለን ስርነቀል ርምጃ በመውሰዱ በኩል ድክመት እንዳለብን ብዙ ጻህፍት ደጉሰዋል። ለሀገራችንና ለወገኖቻችን ቀናኢና ተባባሪ የመሆናችንን ያህል ዘላቂ መፍትሄ እማፈላለጉ ላይ ግን ዘገምተኞች ነን። ለዚህም ይሆናል ተመሳሳይ ችግሮች በተለያየ ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ ለሰላማዊ ሰልፍ የሚያስወጡን። ጊዜያዊ መፍትሄዎች የተፈጠሩትን ችግሮች ለጊዜው በማስታገሱ በኩል መልካም ቢሆኑም ተመልሰን በተመሳሳይ ችግሮች እናዳንገናኝ ግን ጠንካራ ተቋማትን እንደመገንባት ያሉ መሰረታዊ የሆኑ ችግር መፍቺያ መንገዶች ሊኖሩን ይገባል።

ባሁኑ ሰአት በዓለም ደረጃ ግዙፍ የሚባለው እና ዘርፈ ብዙ ስራዎችን የሚያከናውነው ቀይ መስቀል የተመሰረተው ባንድ ትንሽ አጋጣሚ ነው። እንዲህ እንደሰሞኑ ያለው በኢትዮጵየዊያን ላይ የደረሰው አጋጣሚም ተመሳሳይና ለዘላቂ መፍትሄ የሚያግዙ ተቋማትን ለማቋቋም ምክንያት ሊሆን ይችላል። የእንደነዚህ አይነት ተቋማት መኖር እጅግ በጣም ቢያንስ ችግሩ ሳይባባስ መፍትሄ ለማፈላለግ ከማገልገሉም በላይ ተመሳሳይ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት፤ ችግር እየፈጠረ ባለው አካል ላይ ሕዝብን በማስተባበርና አመራር በመስጠትም ሊያገለግሉ ይችላሉ።

በተለይ ወደ ሀገራችን ወቅታዊም ሆኑ የከረሙ ነገር ግን ያልተፈቱ ችግሮችን ስንመለስ አንድን ነገር በጉልህ እንመለከታለን አሱም የፋሽስት ወያኔ ፋሽስተዊ፣ ጎጠኛና መሰሪ አገዛዝን ነው። ርግጥ ነው የሀገራችን ድንበር ያላግባብ ለጎረቤት ሲሰጥና በሀገር ውስጥ ወያኔ ሰራሽ በሆነው ችግር የሀገራችን ሕዝብ ድንበራችን ድንበራችን እየተባባለ ሲካሰስና በዚህም ሳቢያ እስከ ግጭት መድረሳቸውን ስንሰማ አስደናቂ ሰላማዊ ሰልፎችንና ስብሰባዎችን በዓለም ዙሪያ አደረግን ችግሩ ግን እስካሁንም ቀጠለ እንጅ አልበረደም።  ርግጥ ነው ብሔርንና ቋንቋን መሰረት በማድረግ በሰፈነው የአገዛዝ ሰንሰለት ሕዝባችን አይሆኑ ሲሆን፣ አንዱ እንዳሻው ሲሆን ሌላው ሲንከራተት፣ አንዱ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመቆጣጠር ሲዳዳው ሌላኛው የሚበላው አጥቶ ጠኔ ሲደፋው ስናይና ስንሰማ አስደማሚ ሰልፎችን አደረግን እንጅ ችግሮቹ እስካሁንም ድረስ ተባብሰው ቀጥለዋል። ርግጥ ነው ገቢን በማከፋፈል ሰበብ አዲስ ስራ ተቀጣሪዎች የአንድ ዘውግ አባላት ወይም በዘመድ እንዲሁም በፓርቲ አባልነት መረዳዳትና መጠቃቀም ሲስፋፋ እኛ አሁንም በሰላማዊ ሰልፍና በስብሰባዎች ተወጥረን ፋሽስት ወያኔን እያወገዝን ቢሆንም ችግሩ ግን እስካሁንም አልተፈታም። እንዲያውም ፋሽስት ወያኔ የሌሎችን ዘውግ አባላት ከስራና ከቦታቸው በማፈናቀል የራሴ የሚላቸውን መሰግሰጉን አጠናክሮ ቀጠለ እንጅ ለሰከንድ እንኳ አልቦዘነም።

በነዚህ ሁሉ ወያኔ ሰራሽ ችግሮች ሳቢያ ስደት የወጣው ወገናችን በያለበት ሀገር ስቃይ ሲያጋጥመው ስናይም መድር አንቀጥቅጥ ሰላማዊ ሰልፎችን ማድረጋችንን አላቋረጥንም። ትግላችን ግን ወቅታዊ ችግሮችን ለዓለም ለማሳወቅ ወይም ወገናችን ካጋጠመው ወቅታዊ ችግር እንዲወጣ እንጅ ዘላቂ አይደለም።  ለዚህ ሁሉ ስቃያችን ዘላቂው መፍትሄ እንዚህን ሁሉ ችግራችንን እየፈጠረ ያለውን አካል ፋሽስት ወያኔን ከማስወገዱ ላይ ነው። የችግርም ሆነ የደስታ አጋጣሚዎቻችንን ለዘላቂ መፍትሄዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማትን ለመገንባት እንጠቀምባቸው። እነዚህ ተቋማት በዓለም ዙሪያ ከወገኖቻችን ጋር በተያያዘ ለሚፈጠሩ ችግሮች ቋሚ ተሟጋች ሆነው ሊያገለግሉን ከመቻላቸውም በላይ የችግሮችን እንዴትነት በማጥናት በመሰረታዊ ጠላታችን ፋሽስት ወያኔ ላይ የተባበረ ክንዳችንን እንድናነሳ፣ ትግላችንም ግብ ያለው፣ አቅጣጫውን ያልሳተ፣ ተከታታይና ተደጋጋፊ እንዲሆን ያግዙናልና።

ስለሆነም ሞቅ ቀዝቀዝ ከሚል የትግል ስልት እንውጣ፤ ትግላችን የሞተን ከመሸኘት ለታሰረ ከመጮህ በላይ እና ዘላቂ ይሁን፤ ወቅታዊ ችግሮችን ማስወገዳችንን እንደጀግንነት በማየት ከመኮፈስ ይልቅ ጠላታችን ወያኔ እንዴት ባለ አቅምና ሃይል እየሰራ እንደሆነና አካሄዱንም እንመልከት፤ ሰው ወይም መሪ አምላኪ ከመሆን ይልቅ ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት ለተቋማቱ እቅድ ተፈጻሚነትና ዓላማ መሳካት እንትጋ። ይህን ስናደርግ ትግላችን ዘላቂ ይሆናል። የችግሮቻችን ምንጭ የሆነውን ፋሽስት ወያኔንም ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እናስወግዳለን።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on December 8, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: