RSS

ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዳ አይቀበለውም

05 Dec

ከይኸነው አንተሁነኝ

ህዳር 5 2013

ሁሉም ሰው ሰው በመሆኑ ባቻ የሚያገኛቸው ሰብአዊ መብቶች እንዳሉት ሁሉ፤ በዜግነቱ ደግሞ ከሀገሩ የሚጠብቃቸው መንግስታዊ እገዛዎችና ከለላዎች እንደሚኖሩ እሙን ነው። በሕዝብ የተመረጠው ወይም ተመርጫለሁ የሚለው መንግስትም መርጦኛል የሚለውን ማሕበረሰብ ፍላጎት ለማሟላት መጣሩ የሚጠበቅ ከመሆኑም በላይ ከዜጎቹ አንዱ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ አደጋ ቢያጋጥመው አግባብነት ያለው ፍትህ እንዲያገኝ መሟገቱና ፍትህ እንዲያገኝ መጣሩ ከመንግስታዊ ግዴታዎቹ ውስጥ እንዱና ዋነኛው ነው። ይህ እንግዲህ እንደመንግስት መንግስታዊ ግዴታዎችን ለሚያስተዳድረው ማሕበረሰብ እያበረከተ ላለ መንግስታዊ አካል የሚሰጥ ሃላፊነት ነው። መንግስትነትን መስም ብቻ ተጎናጽፈው እንደሚገኙት ፋሽስት ወያኔ አይነቶቹ ግን ሁሉም ነገር ነግድ ነው። የዜጎች ሰላምና ጤንነት እንዲሁም የሀገር ድንበር መከበርና ሉአላዊነትም እንኳ ቢሆን ከወያኔ ባለስልጣናት ጥቅም አኳያ የተቃኘ ነው። በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው የዜጎች ሁለንተናዊ ሰላም ከወያኔ ፖለቲካና የስልጣን ዘለቂነት አንጻር የተለካ ነው።

በፋሽስት ወያኔ አሰራር የሀገር ድንበር ማስከበርና የሕዝብን ሰላም ማስጠበቅ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ የሚታይ ከወያኔ የአገዛዝ ስልጣንና ግለሰባዊና ቡድናዊ ጥቅም በሗላ የሚመጣ ነገር ነው። ስለሆነም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን በደል ደረሰብን እያሉ ያሻቸውን ያህል ቢጮሁና ቢያለቅሱ ፋሽስት ወያኔ ለስሜ ጥሩ አይደለም ብሎ እስካመነ ድረስ አይደመጡም። በፋሽስት ወያኔ የአገዛዝ ዘመን ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸውም እንኳ ሳይቀር እንደሁለተኛ ዜጋ ሲታዩ መቆየታቸው የሚዘነጋ አይደለም። ከዜጋዎች በተሻለ የሚደመጡ ከኢትዮጵያዊያን በበለጠም መብት የነበራቸው የውጭ ዜጎች በሀገራችን ነበሩና ነው። አሁንም አሉ።

የፋሽስት ወያኔ ለዜጎች ክብር አለመስጠት፣ በሌሎችሀገሮች ይቅርና በሀገራችንም ቢሆን በሌሎች ሀገሮች ሕዝቦች ክብር እንድናጣ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አበርክቷል። በሀገራቸው የራሳቸውን መሬት ተነጥቀው ከባለቤትነት ወደ ሎሌነት የወረዱ ክቡር ዜጎቻችን ”ቻይናዊያን አሰሪዎቻችን በደሉን” ብለው ስለከሰሱ እንኳ፤ ”ቻይናዊያንን መክሰስ አይቻልም” የሚል መልስ ከወያኔ መሰጠቱ በሀገራችን እንኳ ምን ያህል እንደቀለልንና ፋሽስት ወያኔ ምን ያህል እንዳስደፈረን ያሳያል።

ሰሞኑን በሳውዲ አረቢያ እየሆነ ያለውም ቢሆን ፋሽስት ዉያኔ ዜጎችን በሰው ሀገር ከሚያዋርድባቸው መንገዶች አንዱ ማሳያ ነው። የደረሰውን ከፍተኛ ውርደትና ጉዳት በመቃወም ፋንታ ወያኔ ግን ዝምታን መርጧል። ተጎጂ ዜጎቻችን የሚያስፈልጋቸውን ርዳታ በተገቢው መንገድ ማግኘት አልቻሉም። ለነገሩ፤ ወያኔ በሀገራችን ክብር አሳጥቶ እንዳሳደደን የሚያውቁ አረቦች እንዴትስ ክብር ሊሰጡን ይችላሉ? ፋሽስት ወያኔ በሀገራችን ሳይቀር እንደፈለገ እንደሚያደርገን የሚያውቁ አረቦች እንዴት ለኛ ክብር ሊሰጡ ይችላሉ? እኛ እኮ የቀለልነው፣ እኛኮ የተዋረድነው ያለገደብ በንቀት እየገዛን ባለው ፋሽስት ወያኔ ነው።

ለመሆኑ ሰሞኑን በአረብ ሀገር የሆነውን ይህን ሁሉ ውርደትና ግድያ ስናይስ ምን አልን? ምን አሰብን? ምን ወሰንን? የችግሩ ማጠንጠኛ ያለው በሀገራችን እንደሆነስ አላወቅን ይሆን? ”ባለቤት ያቀለለውን አሞሌ ባለዳ አይቀበለውም” እንሚባለው ውርደትን እየገዛልን ያለው፣ በመጀመሪያ እንደዜጋ የማያየንና አዋርዶ በንቀት የሚገዛን ፋሽስት ወያኔ እንደሆነስ ዘንግተን ይሆን? ግን ግን ይህን ሁሉ ችግር ካየን በሗላ የአቋም ለውጥ ለማድረግ ዝግጁ ካልሆንን ችግሩ ያለው ከወያኔ ሳይሆን ከራሳችን መሆኑን ልናውቅ ይገባል። የሰሞኑን የወገናችንን ችግር ያየ የዚህ ሁሉ ችግር ፈጣሪ በሆነው ወያኔ ላይ ለመነሳት ዓይኑን ማሸት ያለበትምና።

 

ወገኔን አያችሁ?!

ከአስራ-ሶስት ወራት የብርሃን ጸጋ፣

ከአዝርዕት እናት ከለምለሟ ምድር..፣

ተፈጥሮ ሲቸገር!

ወገኔን አያችሁ?!

አባይ፣ አዋሽ፣ ኦሞ – አንገረብ፣ ተከዜ፣

ጊቤ፣ ዋቤ፣ ባሮ – አትባራ፣ ገናሌ…፣

ጀማ፣ ሮቤ፣ ሙገር – ደዴሳ፣ ቀበና…፣

ጎጀብ፣ ሚሌ፣ ጉደር፣ – በለስ፣ መረብ፣ ዳዋ…፣

ጨፌ የሕይወት ምንጭ አቋርጦ ተሻግሮ፣

በምድረ-በረሃ በውሃ ጥም አሮ፣

በረሃብ በጠኔ አንጀቱ ተቋጥሮ?!

ወገኔን አያችሁ?!

ባረመኔ ጥይት ልቡ ላይ ተመቶ፣

በጨካኞች በትር አናቱ ተፈልጦ፤

በስጋት በጭንቀት ሰርክ ተወጥራ፣

በውራጅ ቦዘኔ ንጹኋ ተደፍራ፤

በበረሃ በረት እንደ ከብት ታጉረው፣

በቀቢጸ-ተስፋ ፍጡራን ተሞልተው…፣

ወገኔን አያችሁ?!

…እናስ ምናላችሁ?

እናንት ደላሎች የሰው ፍጡር ሻጮች፣

በነሱ ላብና ደም “ሚሊዮን” ቆጣሪዎች፣

እብነ-በረድ ሕንፃ ፎቅ ቤት አሰሪዎች፣

ጮማ ሰልችቷችሁ “ቃተኛ” በሊቶች፣

ቬርሙጥ፣ ኮኛክ፣ ውስኪ፣ እንደ ወሃ ቀጂዎች…፣

እናስ ምናላችሁ?

ሲራብ፣ ሲጠማ.. ምስኪን ወገናችሁ፤

የገንዘብ ምንጫችሁ!

እናንተስ “ክቡራን” የተኮፈሳችሁ፣

በንቀት ጥላቻ የተበከላችሁ፣

በዘር በሃይማኖት …ሕዝብ እያመሳችሁ፣

በጉልበት በብረት አፈና የገዛችሁ፤

ከንቱ ጸረ-ዜጋ “ልማታዊ መንግሥት” እኛን ወደ “አሸዋ” – “ለነሱ” ለም- መሬት…፤

ምንድን ተሰማችሁ?

ሲናድ ሰብዕናችን—ሲነካ “ክብራችሁ”?

እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድም…ዘመዳሞች፣

አልቅሶ ተቀባይ… አልቅሶ ሸኚዎች፣

በጣርና ስቃይ ከሚያገኟት ጥሪት እሚያካፍሏችሁ፣

ሲራቡ፣ ሲጠሙ፣ በግፍ ሲሰቃዩ.. እስኪ ምን አላችሁ?

በሃዘን መኮራመት— ሁለተኛ ጉዳት?

 ወይስ ተጠያቂን አፋጦ መሟገት?!

ስንት ዓመት ይቆጠር ስንት ዘመን ይለፍ፣

በግፍ በሰቆቃ ስንት ወጣት ይቀጠፍ፣

እንደ አገር ኢትዮጵያ— እንደ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ተከብሮ ለመኖር፣

ስንት ጊዜ ይክነፍ? — ስንት ሽበት ይብቀል?

ግፈኛውን ቡድን፣ ዘረኛውን ሥረዓት ከስሩ ለመንቀል?!

ከዚያም የሆናችሁ — ከዚህም ያላችሁ

ሁላችን! ሁላችሁ!

ወገኔን አያችሁ?!

አናስ ምን አላችሁ?!

 

ስለግጥሙ

ጌታቸው አበራ

ሕዳር ፳፻፮ ዓ/ም

(ኖቬምበር 2013)

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on December 5, 2013 in AMHARIC, ARTICLE, POEM

 

Tags: , , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: