RSS

የረጋ ውሃ ትርፍ መሻገት ነው

09 Nov

ይኸነው አንተሁነኝ

ህዳር 09 2013

ማንኛውም ማሕበረሰብ በጋራ እንዲንቀሳቀስ እንዲተሳሰብና እንዲረዳዳ የሚያግዙትን ማሕበራዊ እሴቶች በዘገምተኛ የለውጥ ሂደት ይገነባል። እነዚህ የገነባቸው ማሕበራዊ እሴቶችም የማህበረሰቡን በህሪ ለማረቅ ያልተጻፉ ህጎች ሆነው ያገለግላሉ። በዚህ መሰረትም ምንም እንኳ ባሕል ሰፋ ያለ ስነ ሃሳብ ቢይዝም ማንኛውም የማሕበረሰቡ አባል ያካባቢውን ባሕል፣ ሃይማኖት፣ አፈ ታሪኮች፣ ወጎች፣ የሰርግና የለቅሶው ስርአቶች፣ አካባቢንና ሀገርን የማስጠበቅ የጀግንነት ትውፊቱንና ሌሎችንም ሁሉ መቼና እንዴት እንደተማራቸው ሳያውቅ ተክኖባቸው ይገኛል።

እነዚህ ያልተጻፉ ነገር ግን በማሕበረሰቡ ውስጥ ለዘመናት ጸንተው የቆሙት እሴቶቻችን መቼ መነሳትና መርዳት እንዳለብን፣ አንድ ነገር የትና እንዴት መከወን እንዳለበት፣ በግልም ሆነ እንደ ማሕበረሰብ መቼ ማዘን፣ ማልቀስ፣ መደሰት ወይም መቆጣት እንዳለብን ይነግሩናል። እርግጥ ነው እነዚህ እሴቶች እንደየማሕበረሰቡ የእድገት ደረጃ በመጠኑም ቢሆን እየተሞረዱና በሚመች መልኩ እየተስተካከሉ የሚቀጥሉ እንጅ ፈጽሞ የሚጠፉ አይደሉም። ስለሆነም ወንድሞቻችንን የሚያሳዝነው ካላሳዘነን፣ ወገኖቻችንን ያስቆጣው ካላስቆጣን  በውስጣችን አንዳች አደገኛ ነገር እየተከወነ መሆኑን ለመጠርጠር ብዙ መባዘን አያስፈልገንም።

ፋሽስት ወያኔ ሀገራችንን መግዛት ከጀመረበት ከዚህ ካጭሩ እድሜ እንኳ ብንነሳ ብዙ ሊያስቆጡን፣ ሊያናድዱን፣ ሊያበሳጩን የሚችሉ ነገሮች ተከውነው እኛ ግን ዝም ብለን ቀጥለናል። እንዲህ አይነት ነገሮች ሲታዩ እንዴት? ለምን ይህ ሆነ? ብለን እራሳችንን መጠየቃችንና ማስጨነቃችን ይገባ ነበር ግን በተገቢው መጠን እየተደረገ አይደለም።

ዐይናችን እያየ በፊታችን ሁለት ሰዎች ሲጣሉና ለድብድብ ሲጋበዙ  እያየን ዝም ብለን ካለፍን ለራሳችን ለምን ብለን ጥያቄ መጠየቅ ያለብን ያመስለኛል። ወደ ሀገራችን የእለት ከእለት እውነታ ስንመጣ ግን ከአካባቢያችን ማሕበረሰብ አንዱ ወይም አንዷ፣ የክፍል ጓደኛችን፣ ጎረቤታችን ወይም የስራ ባልደረባችን፣ እጅግ ሲቀርብ ደግሞ የቤተሰባችን አባል በወያኔ የተዛባ አመለካከትና ፍርድ አይሆኑ ሲሆን እያየን “ዝም አይነቅዝምን” አጉረምርመን ጸጥ ብለናል። ችግሩ ግን አልቆመም ቀጥሏል። ይህ ችግር ትላንት ያልደረሰበት ዛሬ እየቀመሰው ነው። ትላንትናና ዛሬ የታለፍን ደግሞ እኛ ከጓደኞቻችን የተለየን አይደለንምና ነገ የኛ ተራ መሆኑ አይቀሬ ነው። ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሽስት ወያኔ የጥቃት ሰለባ ለመሆን በወረፋ ተቀምጧል ብሎ በድፍረት ለመናግር የሚያስችል ሁኔታ ላይ ነው የምንገኘው። ምክንያቱም ጥቃቱና መብት መጋፋቱ በፍጹም ከኖርንበት ማሕበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ ውጪ ሕጻናትንና እናቶችን ጨምሮ አቅመ ደካማ ሽማግሎችንና አካል ጉዳተኞችን ሳይቀር የጠቀለለ ነበር። የተማረ ያልተማረ፣ አራሽም ሆነ ነጋዴ፣ የቢሮ ሰራተኛ መምህሩ ሁሉም የፋሽስት ወያኔ የጥቃት ሰለባዎች ነበሩ ናቸውም። ነገር ግን ሁሉም የግሉን እዳ በግሉ ወሰደ እንጅ ወረፋ እየተበቀ ያለው ሌለው ሰፊው ሕዝብ ስለ ወንድሙና ስለእህቱ ጉዳት ለምን? ብሎ ለመጠየቅ አልቻለም፤ የተዘጋጀም አይመስልም። ልክ እንደቆመ ውሃ ጸጥ ረጭ ብሎ ተቀምጧል።

የቆመ ውሃ ምናልባትም በውስጡ ሂዎት ያላቸው ነገሮች ሊኖሩበት ይችሉ ይሆናል እንጅ በራሱ ግን ከመሻገት፤ በመሽተት አካባቢን ከመበከል ውጭ ሌላ ትርፍ የለውም። መብቱን የተገፈፈና በግዞት የሚኖር ሕዝብም ራሱን ለማስከበር እስካልተንቀሳቀሰ ድረስ የውሃው አይነት ተመሳሳይ እጣ ነው የሚኖረው። እየደረሰበት ያለውን ግፍ መርሳት አይችልም በጽናት ለመታገል ግን በተለያዩ ምክንያቶች አቅቶታል። ስለዚህም እያሰቃየው የለውን የውስጡን ስሜት ለመሸፈን ራሱን በተለያዩ ሱሶች ውስጥ ደብቆ ነገን በተስፋ ያጠብቃል። ተስፋ ግን እንቅስቃሴ እንደምትፈልግ የተረዳ አይመስልም። ተስፋን እውን ለማድረግ ተስፈኛው የሚከውናቸው በጣም ብዙ ትግሎችና ውጣ ውረዶች መኖራቸውን ረስቷቸዋል አልያም ሆን ብሎ ዘሏቸዋል።

የምናስባቸውን ነገሮች ለማየትና ነገ የምንፈልገውን ለመሆን ዛሬ የማንፈልገውን ለማድረግ ዝግጁዎች መሆን ይኖርብናል። ለማሕበረሰባችን እሴቶች ልንገዛ ይገባል። ቀደም በማሕበረሰብ ደረጃ አይደለም በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘራፍ ያስብሉ የነበሩ ድርጊቶች ዛሬ በግለሰብ ደረጃ እንኳ ሊያስቆጡን አልቻሉም። ወጣቱ ራሱን መፈተሽ ይኖርበታል። ዛሬ በፋሽስት ወያኔ በሀገራችን እየተከወነ ያለው ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና መሕበረሰባዊ ህጸጽ ምድርን እንኳ ቢሆን ማንቀጥቀጥ የሚገባው ነበር ግን ወጣቱ ዝም ብሎ በማየት ላይ ይገኛል። ሀገርም ሆነች የማህበረሰብ ወጎች የሚጠበቁት በራሱ በማህበረሰቡ እንጅ በሌላ አይደለም። አካባቢውንና የራሱን እንስሳዊ ማህበረሰብ በራሱ መንገድ ለማስከበር ተፈጥሯዊ ህግ እንደሚያስገድደው የጫካ እንስሳ፤ ወጣቱ አካባቢውን ለማስከበር የሞራል ግዴታ ብቻም ሳይሆን ተፈጥሯዊ ሃላፊነት አለበት።  ስለሆነም ከሌላ ቦታ እርዳታ ከመጠበቅ ይልቅ በራሱ ለመንቀሳቀስ መሞከር ይኖርበታል። ባለቤት ከተንቀሳቀሰ ጎረቤት መርዳቱ አይቀርምና። ባሁኑ ሰአት በፋሽስት ወያኔ እየተከወነ ያለው የመብት ገፈፋ፣ ግርፋት ስደትና ግድያ ሊያስቆጣውና ዘራፍ አስብሎ ሊያስነሳው ይገባል። መጭውን ዘመን ጨለምተኛ ሆኖ ምንም እንደማይመጣ ወስኖ ራስን ከማምከን በፊት የሚመጣው ካለፈውና ካለው የተሻለ እንደሚሆን በመገመት ያን ዓለም እውን ለማድረግ ዛሬ እንቅፋቶችን ማስወገድ ያገባዋል።

ይህን ማደረግ ያልቻለ ወጣት፣ ዛሬ የውስጡን ጥያቄ ለመመለስ ብቃት የጎደለው ወጣት፣ ዛሬ ለውንድሙ የጩኸት ጥሪ ዝም ጭጭ ያለ ወጣት፣ የትላንታውን ግፍ ዘንግቶ የዘሬውን አይኑ ስር እየተደረገ ያለ ያቮላን ኮረብታ የሚያክል ስህተት ለማየት የተቸገረ ወጣት ነገ ምን አይነት ሂዎት ሊመራ ይችላል?

ዛሬ ፋሽስት ወያኔ እየከወነው ያለውን ኢፍትሃዊነት ያልተቸ ያልተገዳደረ ኢትዮጵያዊ ነገን እንዴት በተስፋ ሊጠብቅ ያችላል? እኛ ለመታገል ዝግጁዎች እስካልሆንና ወያኔ እስከቀጠለ ድረስ እኮ ነገ ከዛሬው የከፋ ጨለማ ነው። ሁላችንም ወያኔን ለማስወገድ እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ትግል ያቅማችንን የየግላችንን ትንሽ ትንሽ ጣል ጣል በማድረግ  ራሳችንን በተለያዩ ሱሶች በመደንዘዝ ከሚመጣ የቁም ሞት፣ ሕዝባችንን ከውርደት ሀገራችንንም በፋሽስት ወያኔ ተንኮል ተበጣጥሳ ከመጥፋት እንታደጋት።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on November 9, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: