RSS

ባለራዕዩን መተቸት የለውጥ ምልክት አይደለም!!!

13 Oct

ከይኸነው አንተሁነኝ

ጥቅምት 13 2013

በዲሞክራሲ ስርአት መነጋገር ባህል ነው። መተቻቸትም ድክመትን ነቅሶ በማውጣት የተሻለና ጠንካራ ስብእና እንዲኖረን ባማድረጉ ሂደት ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል። የተሻለ ዲሞክራሲ አላቸው የምንላቸው ሀገሮች ሕዝቦችም አሁን ላሉበት ደረጃ የበቁት ለመነጋገር ዝግጁ በመሆናቸው፣ ሳይሰለቻቹ በመደማመጣቸውና ባጋጣሚው የሚሰነዘሩ ገንቢ ትችቶችን ሙሉ በሙሉ በመቀበል ለማሻሻል በመስራታቸው እንደሆነ እሙን ነው። ትችትን በቀጥታ ለተናጋሪው በማቅረብ እርምት እንዲደረግባቸው መሞከር እንዳለ ሁሉ አንዳንዴም ተናጋሪው በሌለበት ሁኔታ ሃሰቡን በመተቸት ከውጤቱ ሌሎች አንዲማሩ ማድረግ ይቻላል። ከዚህ ሁኔታ መረዳት የምንችለው እንግዲህ ትችት ሰዎችን በመሞረድ ብቃትን ለመጨመር ከማገልገሉም ባሻገር በተለይ በአምባገነን ስርአቶች ሲከወን መተቻቸት የተለመደ ካለመሆኑ አንጻር  የለውጥ ምልክት ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል።

ይህን እንዳለ ይዘን ሰሞኑን ከፋሽስት ወያኔ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተብየዎች አንዱ የስም ተሿሚ ደመቀ መኮንን ባለራዕይ የሚሉትን ጎጠኛ መለስ ዜናዊን ተቸ በሚል በያቅጣጫው ሲናፈስ ይሰማል። ከአንባገነን ገዥዎች የተሰነዘረ ትችት ነው በሚልም እንደለውጥ ሊወሰድ ይችል ይሆናል። ግን አይደለም።

ሲጀመር ደመቀ መኮንን ያለቆቹ ታዛዥ ነው። በራሱ ተነሳሽነት በህሊናው ተመርቶ የሚያደርገው ነገር የለም። በራሱ ህሊና የሚመራ ቢሆንማ ኖሮ ርዝመቱ ከአንድ ሽ ስድስት መቶ ኪሎሜትር በላይና ስፋቱም ከሰላሳ እስከ ስድሳ ኪሎሜትር የሆነን የሀገራችንን ለም መሬት አሳልፎ ለሱዳን በማስረከቡ ሂደት ወያኔን ወክሎ ሀገር ለመግደል ባልተደራደረና ባልፈረመም ነበር። እናም ይህ ሰው ጎጠኛው መለስ ዜናዊ የተናገረውን ወይም ሲያደርገው የነበረውን ለመተቸት አቅም ያለው ሰው አይደለም። የሞራል ብቃትም የለውም። ነገር ግን ስልጣን ያገኘበትን ኩኩ ብሎ ታዛዥነት በመድገም በል የተባለውን በማለት ”ደመቀ መኮንን ባለራዕዩን ተቸ” ተብሎ ተነገረለት። ይህማ ባይሆን ኖሮ ደመቀ መኮንን ዛሬ ቦታው ቃሊቲ ነበር። ጉዳዩ በቀላሉ ከታየለት ማለቴ ነው። ከዚህም ከከፋ የፋሽስት ወያኔን የጫካ ሂዎት እያስታወሱ የጻፉ የጊዜው ጓዶች ያጋለጡትን ሚስጥር ማንበብ በቂ ይሆናል። በፋሽስት ወያኔ የጫካ ዘመንም ሆነ የአገዛዝ ወንበር ከያዘ በሗላ ብዙ አመራሮችና ታጋዮች ጎጠኛው መለስ የተናገረውን አይደለም ሌሎች ተናግረውት እሱ ያመነበትን ሀሳብ በመተቸታቸው የሂዎት መስዋትነት እንደከፈሉ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ቆየ። ስለሆነም የሰሞኑ ትችት በይለፍ ፈቃድ የተነገረ እንጅ በደመቀ መኮንን ህሊና አመንጭነት የተባለ እንዳልሆነ እንረዳለን።

ይህ ትችት ባለራዕዩ ጎጠኛው መለስ ዜናዊ ከመሞቱ በፊት ጀምሮት የነበረው ራስን ከፍ ከፍ የማድረጉ ዘመቻ ቀጣይ ክፍል ነው። ፋሽስቱ መለስ የአጼ ቴዎድሮስንና የዳግማዊ አጼ ሚኒልክን ስራዎችና ድሎች በማንቋሸሽ ምንም እንዳልከወኑ በማስመሰል፤ ከዚህም ሲከፋ እኒህን የምንኮራባቸውን የሀገራችን ነገስታት ሀገራችን አሁን ላለችበት ሗላ ቀርነት ምክንያቶች አድርጎ በማቅረብ፤ እድገት የመጣው እሱ እየገዛት ባለችው ኢትዮጵያ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ለማሳመንና ስሙንም በነዚህ በከበሩ ሰዎች ቦታ በመተካት ዘላለማዊ አድርጎ ለመትከል ይደሰኩር እንደነበር አያዘነጋም። ይህ ልራስ ስእል የመትጋት አባዜ ቀጥሎ እሱ በሂዎት ካለፈም በሗላ በተከታዮቹ በሕዝብ ተቀባይ ያጣ ስሙን ደጋግፎ ለማቆም መንገዶችን፣ ት/ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ መናፈሻዎችንና ሌሎችንም በስሙ በመጥራት ህያው ለማድረግ የተሞከረ ሲሆን በተለይ በስሙ ፋውንዴሽን በማቋቋምና የጥናት ማእከሎችን በመገንባት በሂዎት እያለ ታላቅ ያልነበረን ሰው ከሞተ በሗላ ትልቅ ስብእና ለማላበስ ጥረት ሲደረግ መቆቱም አሳፋሪው ገጽታ ነበር።

እንግዲህ የደመቀ መኮንን የሰሞኑ ትችትም ጎጠኛው መለስ ስልጣኑን ሁሉ ሰብስቦ ይዞ ነበር፣ በዚሁ የተነሳም አንዳንድ የስራ መስኮች  እየደከሙና እየተዘጉ ነበር ለማለት ሳይሆን ባለራዕዩን የበለጠ የማግዘፉ ተልእኮ አንዱ ክፍል ነበር። ትችቱ ማንኛውም ሰው በሚረዳው ትክክለኛ የትችት አካሄድ የተናጋሪውን ወይም ድርጊት ፈጻሚውን ሃሳብ በመሞረድ የተሻለ አድርጎ ለማቅረብ የተባለ አልነበረም። ይልቁንስ ትችቱ፤ አንደኛ  ጎጠኛው መለስ ጠንካራ፣ አርቆ አሳቢ፣ አንድ ሰው በፍጹም ሊሰራው የማይችለውን ሲሰራ የኖረና ባንድ ሰው ባቻም ሊተካ የማይችል፣ ልዩ ፍጡር ነበር ብሎ አጉልቶ ለማሳየት የተባለ ነው። በሁለተኛ ደረጃም እሱን ተክቼ እየሰራሁ ነው የሚለውን ሃይለማሪያምን ደካማ አድርጎ በመሳል አቅምህ ዝቅተኛ ነው፣ ከባለራዕዩ ጋር ልትወዳደር አትችልም፣ ስለሆነም በአሰራር ሂደት ችግር እንዳይፈጠር አጋዥ ያስፈልግሃል  የሚለውን ሃሳብ ለራሱ ለሃይለማሪያምም አስረግጦ ለማሳመን ሲሆን በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የተደረገው ካንድ በላይ ምክትል ጠቅላይ ምንስትር ሹመት የተተኪ አቅም አለመመጣጠንን ታሳቢ ያደረገና በተለይም ለሃይለማሪያም ደሳለኝ ጤንነት በማሰብ የተደረገ አድርጎ በማቅረብና በማሳመን ከሕዝብ ሙሉ የሆነ የሃሳብ ተቀባይነትን ለማግኘት የተሞከረ ሙከራ ነበር። ከዚህ ሁሉ የማስመሰል ድራማ በሗላ ካንድ በላይ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር የመሾሙ ዓለማ ታዲያ ያንበሳውን ድርሻ ስልጣን መጨበጥ ነበርና ይህንንም ሕወሃት ፈጽሞታል። በዚህ መሰረት የደመቀ መኮንን የሰሞኑ ትችትም የዚህ ሁሉ ሽፋን ነበር ለማለት ይቻላል።

ምንም እንኳ መተቻቸት የመማማር መርህ፣ የትልቅነትና የለውጥም ምልክት ቢሆንም ይህን ሁሉ ጉድ ለመሸፈን የተነገረው የደመቀ ይስሙላ ትችት ግን የለውጥ ምልክት ሊሆን አይችልም። ቢሆንማ ኖሮ ፋሽስት ወያኔ ሰላማዊ ሰልፎችን በመፍቀድ የለውጥ ምልክት አሳየ ከተባለ በሗላ ተመልሶ ጥሬ ባልሆነም ነበር። ከዚያም አልፎ አስደማሚ ሰላማዊ ሰልፍ ያካሄዱ ፓርቲ መሪዎችን ራሱ በራሱ አሻንጉሊት ፓርላማ አሸባሪ ካለው ግንቦት 7 ንቅናቄ ጋር በማያያዝ አስራለሁ እያለ ወገቡን ይዞ ባልተውረገረገ ነበር። ፋሽስት ወያኔ ለለውጥ ዝግጁ ቢሆንማ ኖሮ ራሱ ሕገ መንግስቴ ባለው መሰረት ይቅርታ የጠየቁ እንደ ውብሸት ታየ አይነት የህሊና እስረኞች ተመሳሳይ ጥያቄ ካቀረቡ ሌሎች እስረኞች ተለይተው ጥያቄያቸው ውድቅ ባልተደረገም ነበር። አወ ወያኔ የለውጥ ሃዋሪያ ሊሆን አይችልም። የለውጥ ሃዋሪያ ሊሆን የሚችለው በውይይትና በትችት የሚያምንና ተያይዞ የተገኘውንም ውጤት ለመቀበል ዝግጁ የሆነ ብቻ ነው። ውይይቶችንና ትችቶችን በሰከነ መንገድ አስኪዶ ውጤታቸውን በተገቢው መንገድ ለመተግበር ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መሆንን ይጠይቃል። ፋሽስት ወያኔ ደግሞ ዴሞክራሲን በስም እንጅ በተግባር አያውቀውም። ስለሆነም በፋሽስት ወያኔ አካባቢ ዴሞክራሲያዊ ውይይትም ሆነ ግልጽ የሆነ ትችት የለም። እየታየ ያለው የይስሙላ ውይይትም ሆነ የሽፋን ትችት ሽፋኖች እንጅ የለውጥ ምልክቶች አይደሉምና።

 
Leave a comment

Posted by on October 13, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , , ,

Leave a comment