RSS

የምንጊዜም ጥቅም እንጅ ዘላቂ ወዳጅነት የለም የወያኔ መመሪያ

21 Sep

ይኸነው አንተሁነኝ

መስከረም 21 2013

ላንድ ሀገር ለመምራት ለተዘጋጀ ፓርቲ ወይም ድርጅት አስተዳድረዋለሁ ከሚለው ሕዝብ ጋር በቀላሉ ለመገናኘት ወይም ደግሞ በቀላሉ ተቀባይነትን ለማግኘትም ሆነ ላለማግኘት በመጀመሪያ ደረጃ የሚከተለው የፖለቲካ አመለካከት (አይዲዮሎጂ) ወሳኝ ነው። የያዘው ወይም እከተለዋለሁ ብሎ የሚያስበው አመለካከቱ የሚገነባውን የልማትም ሆነ የጦር ሃይል  ንቃተ ህሊና ለማነጽ እጅግ አስፈላጊ ነው። ወደፊት እመራዋለሁ ለሚለው ማሕበረሰብ እየተከተለው ባለው አይዲዮሎጂ የእድገት አቅጣጫን ለማሳየት በግልባጩም ሁለንተናዊ ምክርና ድጋፍ ለማሰባሰብም ይረዳዋል። በተለይ ደግሞ በትጥቅ ትግል ወደ ስልጣን ለመጣ ድርጅት ሲከተለው የነበረውን አይዲዮሎጂ ጦሩም ሆነ ደጋፊው ሕዝብ የማተቡን ያህል የሚተማመንበትና የሚሞትለት እንደሚሆን መገመት ቀላል የመሆኑን ያህል በዚሁ ዙሪያ የሚመጡ ለውጦችም የዚያኑ ያህል አስፈሪና ውጤታቸውም አደገኛ ሊሆን ይችላል።

ሀገር በመምራትና ሕዝብን በማስተዳደር ሂደት ሊከሰቱ የሚችሉ የፖሊሲ ወይም የአሰራር ለውጦች የሚጠበቁ ቢሆንም መሰረታዊ የሆነ የአመለካከት ለውጥ ማድረግ ግን በትግል ወቅት ለዘመናት የተገነባውን ጦር አመለካከትና የደጋፊ እይታ ያዘበራርቃል። የበታች የድርጅቱ ሰራተኞችና ሰራዊቱ በበላይ አለቆች ላይ እምነት እንዲያጡ ያደርጋል። እጅግ በጣም ሲከፋ ደግሞ ለመመለስም ሆነ ለማቀዝቀዝ አስቸጋሪ የሆኑ ጥያቄዎችንና አመጽም ሊቀሰቅስ ይችላል። በተለይ ይህን አይነት ለውጥን በተመለከተ በመምራት ስም ሀገርና ሕዝብ እየገዛ ያለው ፋሽስት ወያኔ አንዱ ጉልህ ማሳያ ይሆናል። ”ባንዴ ተገልብጠሽ ጎፈር ሆንሽብኝ” እንዳለው ቀላጅ ባንዲት ጀምበር ከኮሚኒስት ካፒታሊስት ወደሚመስል ርዕዮት፣ በጋራ የተገኘውን በጋራ ተካፍሎ ከመኖር ወደ ዝርፊያና የግል ሃብት አካባችነት፣ ቁጥጥር ከሚደረግበት ወደ የይስሙላ ገበያ መር የኢኮኖሚ ስርአት ራሱን ገልብጧልና።

ይህ መቶ በመቶ መገልበጥ ለጥቂቶቹ የወያኔ ሰዎች የበጀ ቢሆንም ለብዙው ግን የተመቸ አልነበረም። በተለይ አስራ ሰባት ዓመት ሙሉ ተሸክሞ ደምና አጥንቱን ገብሮ ለስልጣን ያበቃውን የወያኔ ጦር ሞራል የገደለ ነበር። ያ የግል ሃብት የሚባል የለም በጋራ ሰርተህ ያገኘኸውን በጋራ ትካፈላለህ እየተባለ ሲነገረው የነበረው ጦር የአገዛዝ ወንበር ሲጨበጥ ተረሳ። የራስን መቀመጫ በበለጠ ለማደላደል በተደረገው ሩጫ ፋሽስት ወያኔ ተሸክሞ ያመጣውን ጦር አይደለም እንደ ቡድን ራሱንም ረሳ። ሁሉም ሳይታሰብ የተገኘውን የሀገርና የሕዝብ ሃብት ወደ ግል ኪሱ ለማስገባት ተጣደፈ። በመሃሉ ግን ይህ የተዘነጋ የወያኔ ጦር ለመመለስ ያስቸገረ በዚህ ሰአት ለመስማት የከበደ ጠንካራ ጥያቄ አነሳ። ”ሲነገረን የነበረው ሲሰበክልን የኖረው በጋራ የመከፋፈል መርህ የታለ” ሲል በድፍረት ጠየቀ። ከዚህ በሗላ ወደ ሗላ መመለስ የለም ያሉ የሚመስሉት የፋሽስት ወያኔ ቁንጮዎች መልስ ግን ዘግናኝ ነበር። ባጭሩ ”ጉአፍ ጽረግለይ” ቆሻሾችን አስወግድልኝ በሚል መርህ በአስር ሽዎች የሚቆጠረው፣ ያንን በጋራ ሰርቶ በጋራ የመካፈል ስብከት ሲምግ የኖረው የወያኔ ጦር የወያኔ ቁንጮዎች ባንዲት ጀንበር አመለካከታቸውን እንደቀየሩ ሁሉ እየዘመረ የሞተላቸውን፣ እየደማ ያሻገራቸውን ድልድይ ሆኖ ለአገዛዝ ያበቃቸውን ጦርም ባንዲት ጀምበር ክደው በተኑት። ፋሸስት ወያኔ ከራሱ በቀር ለማንም ለምንም ደንታ እንደሌለው የደርግን ጦር ከመበተኑ በበለጠ በዚህ ስራው ተረጋገጠ። ሁሌ እንደሚሉትም የምንጊዜም ጥቅም እንጅ ዘላቂ ወዳጅነት የለም ብለው ፍቅራቸውን ከጦራቸው አቋረጡ። ወደ ሌላ ባለ ተራ አዲስ ወዳጅ ፍለጋ።

ፋሽስት ወያኔ በእንዲህ አይነት ተመሳሳይ ዘግናኝ ተግባሮቹ ብዙ ወዳጆቹን አስቀይሞ በትኗል እንደገናም መቶ በመቶ ተገልብጦ ወደ ራሱ ለመሳብና ለማቅረብ ሞክሯል። ገና የአገዛዝ ወንበር ከመጨበጡ በፊት ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲከተለው በነበረው አንዱ ካንዱ ተስማምቶ እንዳይኖር የማድረግ መርህ ብሔር ብሔረሰቦችን አጋጭቷል። የተለያዩ ሃይማኖቶችን ተቻችሎና ተከባብሮ አብሮ የመኖር ባህል በተጠና ዘዴ ለማናጋት ሞክሯል። እንደገና ተገልብጦ ግን ተቻችሎ የመኖር እሴትን ለመናድ የተሰለፉትን አልምርም እያለ ጣቱን ሌሎች ላይ በመቀሰር ይከሳል። የብሄር ብሔረሰቦች ቀን እያለም ከበሮ ይደልቃል፤ ጉንጭ አልፋ ንግግር ይለፋል ያስለፍፋል። ”ባንድ ራስ ሁለት ምላስ” ይሏል ይህ ነው። ትላንት ይሄ ብሄረሰብ በዚህ ጉዳይ ምን አገባው፣ ይህን ብሔረሰብ  እንደፈጣን ሎተሪ ብትፍቅው ውስጡ ሌላ ነው፣ ሽንታምና የመሳሰሉትን መጥፎ ንግግሮች በመናገር የሰደባቸውን ያንቋሸሻቸውንና ያዋረዳቸውን ብሄረሰቦች እንደገና ተገልብጦ የብሔር ብሄረሰቦች ቀን በማለት ፋሽስት ወያኔ ሲጠላው የኖረውን የኢትዮጵያዊያን አንድነት በዘፈንና ከበሮ በማስደለቅ እየፈጠርኩት ነው ሊለን ይዳዳዋል። ሳልፈልግህ እገፋሃለሁ ስታስፈልገኝ እጠራሃለሁ ነው ነገሩ። ምክንያቱም የምንጊዜም ጥቅም እንጅ ወጥ ወዳጅነት የለማ በፋሽስት ወያኔ አስተሳሰብ።

የደርግን የፆታና የሙያ ማህበራት አመሰራረትና አደረጃጀት አምርሮ ሲጠላ የነበረው ፋሽስት ወያኔ ዛሬ ግን ራሱ ብሶ የሴቶች ፎረም የወጣቶች ፎረም እያለ የፎረም መአት በመደርደር ሕዝባችንን በማማረር ላይ ይገኛል። በደርግ የካድሬና የስለላ መረብ አሰራርም ሆነ ጭካኔ ተማሮ እንዳልነበር የኢትዮጵያን ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ካድሬ ለማድረግ በአንድ ላምስት የስለላ መረብ ውስጥ ለማካተት ጥረት በማድረግ ላይ ነው። እያደረሰ ያለውም ጭካኔ ወደር የማይገኝለት መሆኑ በዓለማቀፍ የዜና ተቋማት ሳይቀር እስከ መዘገብ የደረሰ ሆኗል። ይህ ሁሉ እንግዲህ የሚያሳየው ፋሽስት ወያኔ ማንኛውንም ነገር ሲፈልግ የሚያነግሰው ሳይፈልግ ደግሞ የሚያራክሰው መሆኑን ነው። ምንም ነገር ቢሆን ከፋሽስት ወያኔና ከጥቂት ቁንጮዎች ጋር ያለው ቅርርብና ወዳጅነት እንጅ ለሀገርም ሆነ ለሕዝብ ካለው ጠቀሜታ አንጻር አይለካም።

ፋሽስት ወያኔ ከጫካ ይዞት በመጣውና በቀጠለው የአገዛዝ አካሄዱ ምክንያት ሞክሮ ያጣውን የሕዝብ ድጋፍ ለመመለስና ሕዝብን ለማሰባሰብ በማሰብ ለይስሙላም ቢሆን ጨርቅና የጨው መቋጠሪያ እያለ ሲሳለቅበት የነበረውን ባንዲራ ክፍ አድርጎ የባንዲራ ቀን እያለ በማክበር ሕዝብን ሲያጭበረብር ከርሟል። የሰሞኑ የወያኔ ነጠላ ዜማም ይኸው ነው። በባንዲራ ቀን የተረሱትን ወጣቶች፣ ስራ አጥ ወልጌ አደገኛ ቦዘኔ ሲባሉ የነበሩትን ወጣቶች የማባበል ተማጽኖ እንደሚደረግ ተገልጿል። በዘር መስመር ለተደራጁት ወያኔ ጀነራሎች ረብጣ ረብጣ ዶላር ማስገኛነት ሲያገለግሉ የነበሩ ህቡዕ የእህት ወንድሞቻችን የአረብ አገር ማስኮብለያ መንገዶች አፋዊም ቢሆን እንደሚቋረጡ የተለመደው የማይፈጸም ቃል ተገብቷል።

ይሁን እንጅ ፋሽስት ወያኔን ላለፉት የአገዛዝ ዘመናቱ ሁሉ አሳምሮ የሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን እንዴት ሊያምነው ይችላል። መሰለፍ ዴሞክረሲአዊ መብታችሁ ነው እያለ ለሰልፍ የወጣን ሁሉ በጠራራ ፀሐይ በጥይት ሲቆላ የኖረ፤ መብቱን ተጠቅሞ የተሰበሰበን ዜጋ በስብሰባ አዳራሹ ሲያፍን የቆየው ፋሽስት ወያኔ አሁን ስለ ባንዲራ ክቡርነት እያወራ ውጡ ሲል እንዴት ሊታመን ይችላል። ስለ ብሔረሰቦች መደማማትና መተላለቅ ቁስል እየነካካ አንዱን ካንዱ ሲያባላ የነበረው ወያኔ ዛሬ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እያለ ሙዚቃ ቢያሰማ ከበሮ ቢደልቅ ለበጎ ብሎ ማን ሊቀበለው ይችላል። ”አባይን አላምነውም ጭብጦዬን ከበላ ወዲህ” ነው ነገሩ። ፋሽስት ወያኔ ትላንት አንድ እንዳንሆን በብዙ ሰርቷል። አንዳችን ሌላኛችንን እንዳናምን በከፍተኛ ሁኔታ ጥሯል። ያሳለፋቸው መንገዶቹ የሚያሳዩትም ፋሽስት ወያኔ በታኝ እኩይ ሃይል መሆኑን ብቻ ነው። ስለሆነም ይህን በታኝ ሃይል በጋራ አስወግዶ በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረተች የጋራ ሀገር ኢትዮጵያን ከመመስረት በቀር በፋሽት ወያኔ ”የምንጊዜም ጥቅም እንጅ ዘላለማዊ ወዳጅነት የለም” መርህ የሚመሰረት ፍትሃዊ አንድነት፣ በፍቅር የተዋጀ የብሔር ብሔረሰቦች ቀንም ሆነ እውነተኛ የባንዲራ ቀን ሊኖር አይችልም።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on September 21, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: