RSS

ወያኔ በስልጣኑ ለመቆየት ወዳጆቹንም አርዷል!!!

21 Aug

ይኸነው አንተሁነኝ

ነሐሴ 21 2013

በብዙ የዓለማችን ሀገሮች የነፃነት ታሪክ የነፃነት መንገዶች አልፎ አልፎ አጭርና ቀላል  ይሁኑ እንጅ ብዙውን ጊዜ ግን ውስብስብና ረጅም ውጣ ውረዳቸውም የትየለሌና አሰልች፣ ሀብት ጉልበትና ጊዜ ጨራሽ እጅግ ሲከፋም ጥቂት የማይባል የሰው ሂዎት በመስዋትነት የሚጠይቁ   ናቸው። በዚህም ምክንያት በሕዘቦች የአርነት እንቅስቃሴ በሀገሮች የነፃነት ትግል ወቅት ብዙ አሰቃቂና አሳዛኝ ታሪኮችን መስማት አዲስ ላይሆን ይችላል። ሕዝቦች ለአርነት በሚያደርጉት ጉዞ ታግለው የሚያታግሉ ድርጅቶችን ፈጥረው በአንድ ዓላማ ስር ተስተጋብረው በመታገል ነጻነታቸውን ያሳጣቸውን ከሰው በታች አድርጎ ሲገዛቸው የነበረውን አገዛዝ ለማንበርከክና አሽቀንጥሮ ለመጣል ሞተው መንገድ ከፍተዋል ራሳቸውም መንገድ ሆነዋል፣ ደምና አጥንታቸውን ገብረዋል፣ ልጄ ቤቴ ትዳሬ ሳይሉ ዱሩ ቤቴ በማለት ብዙ የወጣትነት ዘመናቸውን አሳልፈዋል። በጥቅሉ አይሆኑ ሆነዋል።

በዚህ መንገድ በጥቂት ሰዎች የተጀመረ የነፃነት ጉዞ ቀስ በቀስ ከአካባቢው ጭቁን ማሕበረሰብ ከለላ ማግኘት ይጀምራል። የስንቅና ትጥቅ እንዲሁም የሞራልና የታጋይ እገዛ እየተደረገለትም ይጎለብታል። የወጣበትን ማሕበረሰብ መስሎ እየወጣና እየገባም እጥለዋለሁ ብሎ እየታገለው ስላለው ገዥ ቡድን መረጃዎችን ይሰበስባል። ጥቃትም ይሰነዝራል። ስለሆነም ለሕዝብ አርነት ለሀገር ነጻነት እታገላለሁ ለሚል ቡድን የወጣበት ማሕበረሰብ መከለያ ጫካው፣ ማረፊያ ቤቱ፣ ቢርበው አጉራሹ ከመሆኑም ባሻገር የማይነጥፍ የሰራዊት ምንጩ ነውና ከጥቃት ሊከላከለው የሚሰስተው ነገር ሊኖር አይገባም። ሆኖም ግን አንዳንዴ ነገሮች ባጋጣሚ ሳይሆን ሆን ተብለው ወደ ሗላ እንዲባርቁ ይደረጋሉ።  ሕዝብ ስላበረታ፣ ስላገዘ መንገድ መርቶ ለድል ስላበቃ፣ ስላጎረሰ፣ አብሮ ስለታገለና መረጃ በማቀበል ስለተባበረ ”ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ” ይሉት አይነት ብሂል ይፈጸምበታል። የሞት ጽዋ ይደገስለታል። እንደ ተኩስ መለማመጃ ካርቱን ወደ እሩምታ ሜዳ እንዲነዳ ይደረጋል። በታላቁ መጽሐፍ እንደምናውቀውና ከንጉስ ዳዊት የሰራዊት አለቆች አንዱ እንደነበረው ኦሪዮ የሞት ደብዳቤያቸውን ባላዋቂነት እንደያዙ ወደ መሰዊያው እንዲወርዱ ይደረጋሉ። ያለ እውቀት በድፍረት ያለ ፍርሃት በደስታ እየተንደረደሩ በመድረስ ያገዙ እየመሰላቸው ይታረዳሉ። የጥይት ማብረጃም ይሆናሉ። ግን ግን እንዲህ አይነት ስራ የሚሰራ ቡድን እንዴት ነው የነጻነት ታጋይ የሚባለው? ምን አይነት ጭካኔስ ነው ሲያጎርሰው የነበረን ሕዝብ እራሱ ባቀነባበረው መንገድ ባንድ ጊዜ እነዲጠፋ የሚፈለገው? እንዴትስ ነው ያገለገለን ግለሰብ በማመስገን ፋንታ እስከ ወዲያኛው ዱካው እንዳይገኝ የሚደረገው?

እንግዲህ በተለይ እንደ ፋሽስት ወያኔ ያሉ የነጻነት ታጋይ ቡድን ነን ባዮች የረገጡትን መሬት የመጡበትን መንገድ የተናገሩትን ንግግሮች ሁሉ ብናስተውል የራሳቸውን ሕዝብ እየበሉ የኔ ወገኔ የሚሉትን እያረዱ እዚህ የደረሱ ናቸው። ባጋጣሚ ሳይሆን የራስን አገልጋይ ክንድ የሆነን ሕዝብ አሳልፎ በመስጠት የሚመጣን ጉዳት ከሚገኘው ጥቅም ጋር በማመዛዘን አስበውበት በደንብ ተዘጋጅተውበት በራሳቸው ሕዝብ ቁማር የተጫወቱ የስም የነጻነት ታጋዮች ናቸው።

የፋሽስት ወያኔ ቁንጮዎች በዚህ ወይም በዚያ ምክንያት እነሱ የማይፈልጓቸውን የራሳቸውን ጥቂት ታጋዮች ከግዙፍ ጦር ጋር እንዲፋለሙና እንዲጠፉ አስደርገዋል፣ በውጊያ መሃል የራሳቸውን ታጋይ ከጀርባ በመምታትም የጭካኔ ስራ ሲሰሩ ኖረዋል። እነሱ ያደረጉትን ተመሳሳይ ድርጊት የፈጸሙትን የበታች ታጋዮች ከሕግ ውጭ በማለት አጥፍተዋል። በዚህም ምክንያት ፋሽስት ወያኔ ወገኔ ብለው የማይቀርቡት ቢቀርቡት እንኳ የማይታመን እንደሆነ የመጣበት ዱካ አፍ አውጥቶ እየተናገረ ይገኛል።

ከየትኛውም ሃይማኖት ብሔር እድሜና ጾታ ብንወከል፣ ከዚህ ወይም ከዚያ ፖለቲካ ፓርቲ ወይም አመለካከት ብንወግን፣ በቁጥር ትንሽ ወይም ብዙ ብንሆን ወይም በየትኛውም የስልጣን እርከን ላይ ብንገኝ፤ ለወያኔ ቁንጮዎች የኛ መስዋትነት የነገን የንጋት ጮራ የሚያሳያቸው ከመሰላቸው የነሱን እድሜ ለመቀጠል ግብአት በማድረግ ወደ መሰዊያው ለማስገባት ቅር አይላቸውም።

እንዲህ አይነቱን የወያኔ ፋሽስታዊ የጭካኔ ድርጊት በማስረጃ ለማስደገፍ ብዙ ሩቅ መባዘን ሳያስፈልግ ራሳቸው በተንቀሳቃሽ ምስል ቀርጸው ሁሌ ለሕዝብ የሚያሳዩትን የሀውዜንን ሕዝብ እልቂት ብቻ መመልከት ከበቂ በላይ ሊሆን ይችላል። በጊዜው የወያኔን መሰሪ አካሄድ የተረዳው የትግራይ ህዝብ ለወያኔ ሲያቀርብ የነበረውን ማንኛውንም እገዛ ቀነሰ። በተለያዩ አካባቢዎችም ስለትግሉ አላስፈላጊነትና እያደረሰ ስላለውም ጉዳት መጠየቅ ጀመረ። በዚህ ያልተደሰቱት የፋሽስት ወያኔ ቁንጮዎች  ባጉራሾቻቸው ላይ ተንኮል ሸረቡ። የወለዱ ያሳደጉና ለቁም ነገር ያበቁ ወላጆቻቸውንም ከዱ። የሃውዜን የእልቂት ድግስም በፍጥነት መቀላጠፍ ጀመረ።

የፋሽስት ወያኔ ቁንጮዎች ይህንን እልቂት ሲያቅዱና በተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) እንደሚዘጋጅ ሲወስኑ ስለሚያልቀው ጋሻ መከታ ሕዝባቸው ሳይሆን ወደፊት ስለሚያገኙት ባለ ብዙ ፈርጅ ጥቅማቸው እያንሰላሰሉ ነበር። የዚህ የሀውዜን ሕዝብ ጅምላ ግድያ ሲሳካ የሚመጣውን የጉልበት የሀብትና የዲፕሎማሲ ሽልማት በማሰብ እያዛጉ ነበር።

በመሆኑም የቸገራቸውን የሰራዊት እጦት ለማሟላት፣ ከዓለም ማሕበረሰብ ሁሉን አቀፍ የእርዳታ አቅርቦትን ከፍ ለማድረግ፣ እየታገልነው ነው በሚሉት ገዥ ሃይል ላይ የዲፕሎማሲ ኪሳራ ለማድረስ እንዲሁም እርዳታም እንዳያገኝ በማድረግ ማዳከምን ያካተተ ባለብዙ ፈርጅ እቅድ ነበር የፋሽስት ወያኔ የሀውዜን ሕዝብ አሰቃቂ የጭፍጨፋ እቅድ። እየገኘ ስላለው ወይም ወደፊት ስለሚያገኘው እንጅ እየጠፋ ስላለው ደንታ የሌለው ወያኔ በሽ ለሚቆጠረው የሀውዜን ሕዝብ አርድ ምንም ጭንቅ አልነበረውም። ፈረንጆች ”Who cares for the dead fish” እንደሚሉት መሆኑ ነው።

ባንድ በኩል ”አሳውን ለማጥፋት ባህሩን ማድረቅ” ብሎ ጠላት መጣብህ እያለ የትግራይን ሕዝብ የሚቀሰቅሰው ፋሽስት ወያኔ በሌላ በኩል ደግሞ ባሕሩ እንዴት እንደሚደርቅ መረጃዎችን አቀናብሮ ለጠላት ያቀብላል። ያስጨፈጭፋልም። እንዲህ አይነት ለመስማት የሚቀፉ ለህሊና የሚዘገንኑ ለአእምሮ የሚከብዱ አሰቃቂ ድርጊቶችን እየከወነ ለአገዛዝ ወንበር የበቃው ዘረኛው ወያኔ እስካሁንም ድረስ የግፍ ግድያውንና የራሱን ሰው በራሱ እቅድ ማጥፋትን አሁን በቅርቡ እንኳ የደሴውን ሃጅ ኑሩን በራሱ ሰዎች በማጥፋት አስመስክሯል። የራሱን የወያኔ ደጋፊዎችን ጨምሮ ከሕጻን እስከ ሽማግሌ እድሜ ሳይለይ፣ ከየትኛውም የሀይማኖትም ሆነ የፖለቲካ ተቋም ቢኮን ግድ ሳይለው፣ ጾታን የትምህርት ደረጃንና ሙያን ሳይለይ፣ ቋንቋንና ብሔረሰብን እንዲሁም የስልጣን ደረጃን ሳይመርጥ የዚህ የጥፋት እቅድ ሰለባ አድርጓል።

ዛሬም ድረስ በፕሮፓጋንዳ ተጠልፋችሁ ወይም የጥቅም ተጋሪ ሆናችሁ በፈሽስት ወያኔ ካምፕ ውስጥ ያላችሁ ወገኖቻችን ወያኔ ያዘጋጀላችሁ የመጥፊያ እቅዳችሁ ወረፋ እየጠበቀ እንጅ የተረሳችሁ እንዳይመስላችሁ። እንደ እንስሳት ማድለቢያ ጣቢያ ለነገ የመስዋእት እርድ ለማድረግ እያሰባችሁ እንጅ እየተንከባከባችሁ እንዳይመስላችሁ። የወያኔ ቁንጮዎች የነገን ፀሐይ ለመመልከት ለጭንቅ ቀን መረማመጂያ ድልድይ ለማድረግ እየቀለቧችሁ እንጅ እያሳደጓችሁ እንዳይመስላችሁ። በሱ እናንተ ባላችሁበት አካባቢ ያለው ፀሐይ የሙቀቱ ግለትም ሆነ የብርሃኑ ሃያልነት ጊዜያዊ መሆኑን አስተውሉና አስተማማኝና ዘላቂ  ጠንካራ ሙቀትና ብርሃን ወደ አለበት የሕዝብ ክንድ ተመለሱ።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on August 21, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: