RSS

ወያኔ ሕወሃቶች- ከመሳብ ይልቅ የሚጎትቱ ሸክሞች

10 Jul

ከይኸነው አንተሁነኝ

ሐምሌ 10 2013

በሀገራችን ከሚገኙ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ከሆኑት አንዱ በሆነው ንግድ ባንክ ውስጥ አንድ የምትገርም ግን ውጤታማ የሆነች አሰራር አለች። በተለይ አገልግሎት ከሚፈልገው ማሕበረሰብ ጋር ቀጣታ ግንኙነት ያላቸው የዚህ መስሪያቤት ሰራተኞች፤ ባለጉዳይን ላለማጉላላትና በጊዜ ለመሸኘት ይመስላል፤ አንደኛው ሰራተኛ በጊዜው በቦታው ያልተገኘ ሌላ ባልደረባውን  ሃላፊነት የመሸከምና ስራውንም አሳምሮ የመስራት ልምድ አዳብረዋል። በሗላ በሗላ ጠይቄ እንደተረዳሁት እዚህ አገልግሎት መስጫ ተቋም የሚቀጠሩ ሁሉም ባይሆኑ አብዛኞቹ ሰራተኞች በተመሳሳይ ወይም በተቀራራቢ ሙያ የሚመረቁ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ቀጣሪ ድርጅታቸው ባንክ ከራሳቸው ሃላፊነት አልፈው የጋደኞቻቸውንም ሃላፊነት ያለ ችግር መከወን እንዲችሉ ተገቢ የሆነ ስልጠና እንደሚሰጥ ለማወቅ ችያለሁ። አላማየ ንግድ ባንክ ስለሚባለው አገልግሎት መስጫ ተቋም ለማውራት አይደለም። ይልቅስ ከላይ እንደ መንደርደሪያ የጠቀስኳት የዚህ ድርጅት አሰራር ከዛሬው ዝግጅቴ ጋር የሚያገናኝ አንድ አብይ ነገር ስላላት እንጅ።

የምንሰራበት ተቋም ትንሽም ይሁን ትልቅ ሃላፊነታችን ከባድም ይሁን ቀላል አሰራሩም ዘመናዊም ሆነ ገና ያልተሻሻለ እንደ አጠቃላይ መመሪያ አንድን ስራ በብቃት ለመከወን ለስራው የሚያበቃ ተገቢ ትምህርት ሊኖረን ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ በጊዜ የተፈተነ የስራ ልምድና ተከታታይነት ያለው የስራ ላይ ስልጠናም እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው። ይህን ሁሉ ሂደት ያጠናቀቀ ታዲያ ስራውን በብቃት ይከውናል ተብሎ ይጠበቃል።  ለስራው ብቁ የሆኑትም እየተለዩ ይቀሩና እራሳቸውን አንደ ሰራተኛ እንዲሁም መስሪያ ቤታቸውን እንደ አሰሪ ድርጅት አንቱ ከማስባል ደረጃ ይደርሳሉ። ይሁን እንጅ ከዚህም ሁሉ ሂደት በሗላ ስራቸውን መከወን የሚቸግራቸው አንዳንድ ሰራተኞች መታየታቸው አይቀርም። ስለሆነም  ይህን መሰሉን የአሰራር ሂደት በተገቢው መንገድ መወጣት ያልቻሉት ሌላ ካቅም በላይ የሆነ ሃይል እስካላተረፋቸው ድረስ ይህም ሂደት ነውና ሂደቱ የሚተፋቸውና የሚያስወግዳቸ  ይሆናሉ ማለት ነው። ምክንያቱም ማንኛውም መስሪያ ቤት እንደሰራተኛ የሚያየን መሰረታዊ ሙያችንን እየተሰጠን ካለው የስራ ላይ ስልጠና ጋር አዋህደን ቀጣሪ መስሪያ ቤታችን የሰጠንን ሃላፊነት መወጣት ስንችል ብቻ ነው። ይህን ካላደረግን ግን ከገሙ እንቁላሎች እንደ አንዱ ተቆጥረናልና ከስራ ብንባረር የሚደንቅ አይሆንም።

አንዳንዴ ግን እጅግ በሚገርምና እስካሁን እያወራን ከነበረው ፍጹም በተቃረነ መልኩ የራሳቸውን ስራ በብቃት የሚከውኑ ሰራተኞች እንደ ገሙ እንቁላሎች ተቆጥረው ሲተፉና ሲወገዱ ብቃት የሌላቸው ማለትም እንደዚህ ጽሁፍ አተያይ የገሙ እንቁላሎች ግን እንደ ጠንካራ ሰራተኛ በደረጃና በስልጣን ከፍ ከፍ ሲሉ ይታያሉ። እንደዚህ አይነቱን አሰራር ለማረጋገጥ ምስክር ፍለጋ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገን የሰሞኑን ይወያኔ ሕወሃት ሹመት አሰጣጥ መመልከት ብቻ በቂ ይሆናል።

መቼም ሁላችንም እንደምንገነዘበው የገማን እንቁላል አቃፊ ዶሮ ቀይሮ በማስታቀፍ ወይም ቦታ ቀይሮ በማሟሟቅ ጫጩት ማድረግ አይቻልም። የገማ የተበላሸ ነውና ከመጣል ወይም ከመቀበር ሌላ ምንም ተስፋ የለውም። ታዲያ ግን እንዲህ አይነት አሰራር የሚሰራው በነባራዊው ዓለም ሃቅ እንጅ ከዚህ ውጭ ለሚንቀሳቀሱት ለእንደ ወያኔ ሕወሃት አይነቶቹ አይደለም። ወያኔ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም የገሙ እንቁላሎችን፤ ተሰብረው አካባቢውን በመጥፎ ሽታቸው እንዳይበክሉት እየተጠነቀቀ፤ ይዘው መከወን ካቃቷቸው ሃላፊነቶች በላይ ሃላፊነት እየሰጠ ሲመድብ መቆየቱ እሙን ነው። የሰሞኑም የዚሁ ቀጣይ ሂደት ነው።

ሰሞኑን ወያኔ ሕወሃት ሹመት ሰጠሗቸው ያላቸው ወያኔዎች በሙሉ ሌሎችን ማገዝ ይቅርና የራሳቸውን ሃላፊነት በተገቢው መንገድ መወጣት ያቃታቸውና የሕዝብን አመኔታ ያጡ ናቸው። ድንበርን ቆርሶ ለጎረቤት በማስረከቡ ሂደት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የነበሩና የሀገርን ሉአላዊነት ማስከበር ያልቻሉ ልፍስፍሶች፤ ደረጃውን ያልጠበቀ የትምህርት አሰጣጥ ሂደት በመቅረጽና በማስፈጸም ትውልድን የገደሉ ድኩማን፤ እንደ ተኩስ መለማመጃ ዒላማ ካርቱን ክቡሩን ሰው ግንባሩንና ደረቱን በጥይት የበጣጠሱና እንዲበጣጠስ ትእዛዝ በመቀበል ሲያስፈጽሙ የነበሩ በጭካኔ የተሞሉ አረመኔዎች ከመሆናቸውም በተጨማሪ ሹመት ይቅርና ለነበሩበት የስልጣን ወንበር ብቃት ያልነበራቸውና ሊወገዱ የሚገባቸው የገሙ እንቁላሎች ነበሩ።

አንዳንዶቹ የወያኔ ተሿሚዎችም ዘረኝነት እጅግ ያጠበባቸውና በሰፈራችን ለምን አለፋችሁ በማለት እንደ ዉሻ የሚጮሁ ዜጎችን በሀገራቸው አላስኖር ብለው የሚያባርሩና ለርሃብና ለስደት የዳረጉ አመለካከተ ድሃዎች፤ ሀገርን ሊወክሉ የማይችሉ አይናቸውን እንዳፈጠጡ ንግግራቸውን በውሸት ጀምረው በውሸት የሚጨርሱ የዘመናችንና የሀገራችን ከንቱ የገሙ እንቁላሎች ነበሩ። ሁሉም ከዝንጆሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ አይነት ቢሆኑም ገዥው ወያኔ ሕወሃት ነውና የተሻለ ለተባለ ወንበር ታጩ። በመሆኑም እነዚህ ሁሉ የገሙ እንቁላሎች ለሚያበላሹት ስራና ለሚያቆሽሹት አሰራርና አካባቢ ካሳ ከፋይ ምስኪኑ ህዝባችንና ሀገራችን መሆናቸው እጅግ አሳዛኙ ነገር እንደሆነ አለ።

ከቀደመው ልምዱ መማር የማይችለው ወያኔ ከዚህ በፊትም በሚንስትር መስሪያቤቶችም ሆነ በወታደራዊና ሲቪል ተቋማት ባለው አቅሙ ሁሉ አሽከሮቼ ናቸው የሚላቸውን እየቀያየረ ለማሰራት ሳይሆን ለመመደብ ሞክሯል። ወያኔ ሕወሃት አውርዶ ከጣላቸው በሗላ እንደገና መልሶ በመሾምና ወታደራዊ ማዕረገቸውን ሳይቀር ገፎ ሲቪል በማድረግ ለስልጣን ጊዜው መራዘም እንዲያግዙት ለማድረግ ሞክሯል ግን ጠብ ያለ ነገር አልታየም። ምክንያቱም ሲጀመር ሁሉም አቅም የሌላቸው ድኩማኖች ነበሩና ነው። እጅግ ያፈጠጠው ሃቅ ግን አንደ ጎጠኛ ተቋም ከራሱ ከወያኔ ጀምሮ በስሩ ያሰለፋቸውም ቢሆኑ አንድም የአገልግሎት ዘመናቸውን የጨረሱና ከማዳን ይልቅ የሚመርዙ እንክብሎች፣ ከመሳብ ይልቅ የሚጎትቱ ሸክሞች፣ ከተስፋ ይልቅ በጫካ ትዝታ የናወዙ ጉጉየዎች፣ ከመስራት ስርቆት ከሃቅ ይልቅ ውሸት መልካም ነው ብለው እየከወኑ ያሉ ውርስ መተው የማይችሉ ምንም እንጥፍጣፊ ሲሳይ ያልቀራቸው ከላይ እንዳልኩት የገሙ እንቁላሎች መሆናቸው ነው።

ወያኔ ሕወሃት አንዱን ባንዱ በመቀያየር ድሃውን ወያኔ ድርሻውን ዘርፎ ሃብታምና መልካም ታዛዥ እንዲሆን አድረጓል። አምባገነንነትንና ጎጠኝነትን አስፋፍቶበታል። መመታትና መሰደድ ያለባቸውን አስመትቶ አሰድዶበታል። በጥቅሉ ወገንን አሳዝኖበታል ሀገርንም አቆርቁዞበታል እንጅ ወያኔዎችን በመቀያየር ያየነው ለውጥ ወይም እድገት ይለም። የሰሞኑ የስልጣን ችሮታም ከዚህ የተለየ ምንም አዲስ ነገር አያመጣም።

ስለሆነም በቅርብ የተጣሉ ትኩስ እንቁላሎችን በመጠቀም እንጅ ቦታ በመቀያየር የገማን እንቁላል ጫጩት ማድረግ እንደማይቻል ሁሉ ሲጀመር የዘረኝነት ትስስር፣ የጥቅም ሰንሰለትና የበቀል ጥማት እንጅ ሙያ፣ የስራ ፍቅርና የወገንና የሀገር ተቆርቋሪነት ያላገናኛቸውን ወያኔ ሕወሃቶች ወንበር በመቀያየር ለሀገርና ለወገን እንዲጠቅሙ ማድረግ አይቻልም።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on July 10, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: