RSS

የሽፋን ስእሎች

19 Jun

ይኸነው አንተሁነኝ

ሰኔ 19 2013

እንዲሆንልን የተመኘነው ነገር እኛ በፈለግነው መልኩ ሳይሆን ሲቀር ምኞታችንን ሃሳባችንን የሚገልጽ ስም እንሰይማለን። ይህ አዲስ ስያሜ ታዲያ ስያሜ እንጅ በፊት እኛ የተመኘነው ስላልሆነ ይህን በማድረጋችን ራሳችንን  እንዋሻለን ወይም እንሸነግላለን። ለምሳሌ ሆስፒታሎችን ድልድዮችንና ትምህርት ቤቶችን እያፈራረሰና ባንኮችን እየዘረፈ እዚህ ለደረሰውና አሁንም ሕዝብን እያሸበረና ሰላም እያደፈረሰ ላለው ወያኔ “ተራሮችን ያነቀጠቀጠ” የሚል ሽፋን ስያሜ እንደተሰጠው መሆኑ ነው። ቢያንስ ለኛ ወያኔ ሕወሃትን አሳምረን ለምናውቀው ወያኔ ለራሱ ደቦ ሳይቆርስ ሲመኘው የነበረውን ስም እንዳወጣ እንገነዘባለን። እውነታው ግን ስም ወዲህ ተግባር ወዲያ ነው። መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ ይሏል ይህ ነው።

አንድ ሰው በመስታውት ራሱን ሲመለከት ራሱን እንጅ ሌላ ሊያይ አይችልም። ሌላ ያየ ከመሰለው እንኳ መሰለው እንጅ ራሱ አይደለም። ወያኔ ድልድይ እየደረመሰና ለሕዝብ ጥቅም የተገነባ ተቋም እያፈራረሰ፤ ሕዝብን እያተራመሰና እያሸበረ ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ከመሰለው ይህ መምሰል እንጅ ሃቁንማ እየተሸበረ ያለው ሕዝብ ያውቀዋል።

ወያኔ ሕወሃት ገና ከጫካ ዘመኑ ጀምሮ የራሱ ያልሆኑ ያሽፋን ስእሎችን ለሀገራችንና ለዓለም ሕዝብ በማሳየት ውስጥ ለውስጥ ግን የማንነቱ አሻራ ማህተም ያለባቸውን በጭካኔ የተሞሉ ድርጊቶችን በመፈጸም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ጎጠኛ ጉጅሌ ነው። ያልያዘውን ያዝኩ ያልማረከውን ማረኩ ያልገደለውን ገደልኩ እያለ ሲቀባጥር እንደነበር ያለፈው ጊዜ የወያኔ የጫካ ዘመን የውሸት የሽፋን ታሪክ አሁንም ድረስ በጉልህ ያስረዳል። ስልጣን ይዣለሁ ካለና በተግባር ግን የአፈና አገዛዙን ከጀመረ በሗላ እንኳ ብዙ የሽፋን ስእሎችን አሳይቶናል።

በይስሙላው የወያኔ ምርጫ ወቅት ከሚሰማውና ይህን ያህል ሚሊዮን ለምርጫ ተመዘገበ እና ይህን ያህሉ ደግሞ መረጠ ከሚለው ጀምሮ የወያኔ ሕወሃት የመንግስት ሃላፊዎች ነን እያሉ በወኔው ፓርላማም ሆነ ወያኔን እየወከሉ በተለያዩ ሚዲያዎች እየቀረቡ የሚያሰሙት ዲስኩር በሙሉ ከእውነታው ጋር የማይጣጣም በውሸት የሽፋን ስእል የተሞላ ባዶ ፕሮፓጋንዳ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ቦታዎች በተለያዩ የማህበረሰባችን አካላት  ሲደረጉ የነበሩትን ተቃውሞዎች አንኳሶ ለማሳየትና ሕዝብን አይወክሉም ለማለት ከዚያም ሲያልፍ ተቃውሞውን ገና ከጅምሩ ለመቅጨት ሲል ሆዳም አባላቶቹንና ሳይጠየቁ የሚወሸክቱትን እንደ ሽፋን ስእልነት በመጠቀም ወያኔ ሕወሃት ተገቢ ያልሆኑ የማን አለብኘነትና የአፈና ድርጊቶችን ፈጽሟል። የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን ወንጀለኛ ለማድረግ ታስቦና እነሱን ለማጥቃት የተቀነባበረው “ጅሃዳዊ ሃረካት” የተሰኘው የወያኔ ፊልም በሽፋን ስእልነት ማገልገሉ ጉልህ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

ወያኔ ሕወሃት በግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ስም የከሰሳቸውንና በሗላም የቅጣት ውሳኔ ያስተላለፈባቸውን ንጹሃን ወገኖቻችንን ለመወንጀል የተጠቀመው ሁሌም እንደሚያደርገው “አኬልዳማ” በሚል የሚታወቀውን የተቀነባበረ የሽፋን ፊልም ነበር።

ከላይ የተዘረዘሩትን ማሳያዎች እንደናሙና ብንወስድ እንኳ ወያኔና የሽፋን ስእሎች የማይለያዩ ያንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን እንረዳለን። ወያኔ ካለ የውሸት የሽፋን ስእል አለ። ተማሪዎች በትምህርት ቤቶችና በየኒቨረሲቲዎች፣ የቢሮ ሰራተኞች በስራ ቦታቸው፣ የወያኔ ወታደሮች፣ ሕዝባዊ የሚባለው ፖሊስና ፌደራል ፖሊስ ባሉበት፣ ኗሪው በየቀበሌው፣ በሽተኞች በየተኙበት ሆስፒታልና የኔቢጤውና የጎዳና ተዳዳሪው ሳይቀር በተመቸ መንገድ ለነሱ የሚስማማ የሽፋን ስእል እየተዘጋጀ ይቀርብላቸዋል። የሚበዛው የሽፋን ስእል ምንም ማጣቀሻ ሳያስፈልግ ወዲያውኑ ውሸት መሆኑ የሚረጋገጥ ሲሆን አንዳንዶቹን ለማረጋገጥ ግን ነጻ ሚዲያ የሚያስፈልግ ቢሆንም ለዚያ የታደልን ባለመሆናችን ዝም ብለን የምንጋታቸው ናቸው።

ለምሳሌ የቀድሞውን የወያኔ ጎጠኛ መሪ ሞት አስመልክቶ ሲተላለፉ የነበሩትን ምስሎች ስንመለከትና የተላለፈውን መልእክት ስናስተውል “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” አይነት ይሆንብናል። ሀዘን ለመቀመጥ የመጡ የጎጠኛው መለስን ጥበቃ አምነው ጎዳና የወጡ የጎዳና ተዳዳሪዎችንና የሆስፒታል የህሙማን ልብሳቸውን ሳይቀይሩና ክንዳቸው ላይ የተተከለው ሂዎት አድን ጉሉኮስ ሳይነቀል በሰልፍ የመጡ ህሙማንን ስናስተውል በእርግጥ ምስሉ ከሽፋን ስእልነትም አልፎ ወደ ፌዝነት የተቀየረም ነበር ለማለትም ይቻላል።

የዚሁ የሽፋን ስእል ቀጣይ የሆነው የወያኔ ሕወሃት የሰሞኑ የሽፋን ፊልም ደግሞ ሆዳም አርቲስቶች ወደ ሶማሌ ክልል እንዲያቀኑ ማድረግና ለሀገራችንም ሆነ ለዓለም ሕዝብ የሚወራው ሁሉ ውሸት ነው። አካባቢው ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላም ነው ብሎ ማስወራት ነበር። በመሰረቱ የጥበብ ሰዎች (አርቲስቶች) የአንዲት ሀገር ሕዝበ ነጸብራቆች ነበሩ። የሕዝቡን ስሜት በማንበብ የሚያንጸባርቁ የሚያሳዩ የሚናገሩ ደፋሮች መሆን ይገባቸው ነበር። የሕዝባችንን ህመም፣ ደስታ፣ ሀዘን፣ ሰርግና ለቅሶው፣ ባህሉና አናኗሩ መህበረሰቡ ራሱ ባፈራቸው ጥበበኞች ይዜማል፣ ይገጠማል፣ ይተወናል፣ ይሳላል፣ ይጻፋል እንዲሁም በተንቀሳቃሽ ምስልነት ይዘጋጃል። ይህ ነበር የጥበበኞች ስራ። ጥንካሬን ማጉላት ድክመትን ነቅሶ በማውጣት ማሳየት።

አሁን አሁን ግን እንዲህ ሰሞኑን እንደምናየው አርቲስት ተብየዎች የወያኔ ሕወሃት ድምጽ ማጉያ ሲሆኑ እየተመለከትን ነው። በሉ የተባሉትን ይላሉ፤ አድርጉ ከተባሉት በላይም ያደርጋሉ። ወያኔ ሕወሃትም እነሱን በመጠቀም የምናውቀውን ፀሐይ የሞቀው ሚስጥር አይደለም እኔ እንዳልኩት ነው ሊለን እየዳዳው ይገኛል። ጉዳያችን ስለ ሶማሌ ክልል ከሆነ ዘንዳ ለጊዜውም ቢሆን የእነዚህን ሆዳም አርቲስቶች የሽፋን ስእል እንተወውና እስኪ በክልሉ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ። በዚህ ክልል ምንም አይነት የውጭ ድርጅት እንዲንቀሳቀስ አይፈቀድለትም። የእርዳታም ሆኑ የሰብአዊ መብት ተቋማት አከባቢውን መጎብኘት አይችሉም። ቀይ መስቀልም ሆነ ድንበር የለሽ ሃኪሞች የሚባሉት አካባቢውን ማት አይችሉም። ነጻ ጋዜጠኞች አካባቢውን አይተው ስለ አካባቢው መጻፍና መናገር አይችሉም። ይህን በተመለከተ የስዊድን ጋዜተኞች በክልሉ በመገኘታቸው የደረሰባቸውን ማስታወስ ብቻ በቂ ይሆናል። በጥቅሉ ወያኔና ሆዳም ተከታዮቹ ብቻ እያዩ ያሻቸውን እንዲቀባጥሩ ብቻ ተለይቶ የተተወ ቦታ ነው።

ከዚህ ነባራዊ እውነታ ስንነሳ ታዲያ የሰሞኑ የሆዳም አርቲስቶች ምስክርነት የትም ሊደርስ የማይችል፣ አንድም ሰው ለማሳመን አቅም የሌለው፣ ራሳቸውን ተናጋሪዎችንና ወያኔን ግን ከፍተኛ ትዝብት ውስጥ የሚጥል ድርጊት ነው። ነዳጅ ፈላጊዎች ለደቂቃ እንኳ ተረጋግተው ስራቸውን ለመስራት የማይችሉበትና በዚህ ሳቢያም በተደጋጋሚ ጥለው የወጡበት አካባቢ መሆኑን ዓለም ከማወቁ አንጻር ጭምር ሲታይ ደግሞ የሆዳም አርቲስቶች ዙረት ብኩን የሽፋን ስእል ነበር ለማለት ይቻላል።

የማይካደው ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ግን በዚሁ በሶማሌ ክልል የሚኖረውን ሕዝባችንን ኖሮ ወደ ሲኦልነት የቀየሩ የወያኔ ታዛዥ ቅልብ ወታደሮች የሚገኙ መሆናቸው ነው። እነዚህ የወያኔ ወታደሮች የፈለጉትን የማሰርና የማሰቃየት፣  የፈለጓትን ልጃገረድ የመድፈርና መጫወቻ የማድረግ ፈቃድ አላቸው። ያሻቸውን ሰው ከፈለጉ አስከ ዘር ማንዝሩ ለማጥፋት፣ በስለት ለመቆራረጥ፣ በጋለ ብረት ለመተኮስ፣ በፈላ ውሃ ለመገሸርና ብትንትን አድርገው ዱካው እንዳይገኝ ለማድረግ ወያኔ ሕወሃት ስልጣን ሰቷቸዋል። ይህን ግፍ አናይም አምቢ ብለው ወያኔን ለመታገል ጠበንጃ ያነሱ ሃይሎችም በዚያው ናቸው። ወያኔን ያስጨንቃሉ አካባቢውንም ለመቆጣጠር ይሞክራሉ። በዓለምአቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀር በከፍተኛ ሁኔታ ሲዘገቡ የነበሩ በወያኔና በጀሌዎቹም ላይ በነዚሁ ሃይሎች  የተወሰዱ የጥቃት እርምጃዎቻቸውም ከጥቂት በላይ ነበሩ። እንግዲህ የወያኔ ሕወሃትም የሰሞኑ የሽፋን ስእል ዝግጅት ይህንኑ ነባራዊ ሁኔታ ውሸት ነው ብሎ ለመስበክና ባካባቢው ከመቼውም በላይ ሰላም አለ ለማስባልና ለዓለም ለማሳየት ያለመ ነበር።

ይሁን እንጅ እውነታውን ለሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርና ለዓለም ሕዝብም ቢሆን ቢሆን በከፍተኛ ወታደራዊ አጀብና በከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገው ጉብኝት ከሽፋን ስእልነት አልፎ ሰላም ስለመኖሩ ምስክርነት ሊሰጥ አይችልም። ሆዳም አርቲስቶችም ቢሆኑ በጎረሱት መጠን ያገሳሉ እንጅ ሚዛን የሚደፋ ምስክርነት ሊሰጡ አይችሉም። ሁሉም ከሕዝብ ልጅነት ያፈነገጡና የወጡ  እንዲሁም በሕዝባችን ዓይን ትዝብት ውስጥ የገቡና ያስተምራሉ ተብለው የሚጠበቁ አይደሉምና።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on June 19, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: