RSS

ጃንደረባ ሎሌ በጌታው ብልት ይፎክራል

04 Apr

ይኸነው አንተሁነኝ

ሚያዚያ 4 2013

ሽምግልና በትዝታ ከመኖር ይጀምራል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። ጉልበት ሲሟሽሽ እነደፈለጉት መንቀሳቀስና ያሰቡትን መከወን ሲቸግር ያኔን እያስታወሱ፤ ሩጠው መቅደም ታግለው መጣል በሚችሉበት እድሜ ያደረጉትንም ሆነ ለማድረግ አስበው ሳይሳካ የቀረውን እያነሳሱ ቢቆዝሙ መቼስ የግል ታሪክ ነውና ይበል ቢባል ነውር አይሆንም። በሌላ በኩል ግን የወገኖቻችንም ሆነ የሀገራችን የቀድሞ የጀግንነት ታሪክ፣ የሚያኮራው የአትንኩኝ ባይነት ገድል፣ የዚያ ወይም የዚህ ድንቅ ቅርስ ባለቤትነት አሻራው ምዕት ዓመታትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ደማችንን የሚያሞቀን ቢሆንም የወላጆቻችን እንጅ የኛ ሃቅ የለበትም። ከሰሜን እስከ ደቡብ ጫፍ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ጽንፍ የፈሰሰው የወላጆቻችን ንጹህ ላብ እንዲሁ በከንቱ አልቀረም፤ ዛሬም ድረስ ታላንትን በግዙፉ ይዘክራል። ይህ ሁሉ የወላጆቻችን ተምሳሌት ታዲያ በጥዑም ቅናት አንሰፍስፎ፣ እንደ ገሞራ አንገብግቦ፤ አብሮ መስራትን ከፍቅር አዋህዶ፣ መተሳሰብን ከሃይይማኖትና ብሔር ለይቶ፣ ጎጠኝነትን በአንድነት ፀበል ፈውሶ፣ ወገንተኝነትን እስከ ኢትዮጵያዊነት አስፍቶ፣ አንተ ትብስ አንችን በብሔር ብሔረሰቦቻችን አንግሶ በቁርጠኛነት እኛን በእልህ አስነስቶ ለማቆምና የኛን ታሪክ በራሳችን ዘመንና  በእኛው ብዕር  እንድንጽፍ ትምህርት ካልሰጠን ምን ይጠቅመናል? ሁሉም የነሱ የትዝታ አሻራ እንጅ የኛ አይደሉምና።    

ሽህ ጊዜ እየተሰበሰቡና ረብጣ ረብጣ ብር በገፍ እየረጩ ስለ ጋደኛ ዝክረ ታሪክ እያወሩ ቢኮፈሱ፤ የሚረጋገጡም ሆኑ የማይረጋገጡ ድርሳናትን ቢደጉሱና ጉንጭ አልፋ ውዳሴ ቢያዘንቡ “ጃንደረባ ሎሌ በጌታው ብልት ይፎክራል” ከማስባል የዘለለ ሌላ ትርፍ የለውም። የሀገራችንን ወቅታዊ ነባራዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በአንክሮ ለተመለከተም በሕወሃት የሚዘወረው ወያኔ ያለጥርጥር ጃንደረባ ገዠ መሆኑን በግልጽ ያስተውላል። በባዶ ወንበር በሚወከል፣ ገጸ ምስሉ በሚመለክ እንዲሁም የሙት መንፈስ ንግግሩ በተደጋጋሚ እየተገለበጡ በሚስተጋቡለት የወያኔ ቁንጮ የሙት መንፈስ የሚመራና በጨበጣ የሚፎክር ስልብ የጉጅሌ ቡድን እንጅ የወቅቱ ሕወሃት በራሱ ቆሞና አቅዶ ለመተገብር አቅም አንሶት እየተንገዳገደ ያለ ለመሆኑ ሰሞኑን ካካሄደው ጉባኤ መረዳት ይቻላል።

የቀዘቀዘን መንፈስ እየዛገ ያለን ጉልበት ቀስቅሶ ሕዝብን አስተባብሮ በዓለም ደረጃ በጉልህ የምንታወቅበትን ድህነትና ስደት በቅጡ ለማረቅ የተሳነው ጃንደረባው ሕወሃት፤ ሕዝባችንን በአመለካከቱ በሃይማኖቱ እንዲሁም በቋንቋው በመከፋፈል አንድ ሆኖ መረዳዳትና መተሳሰብ እንዳይችል በማድረግና የስልጣን ወንበሩን በማመቻቸት ላይ ሙሉ ጊዜውን ሲያጠፋ እያየን ነው። በቅርቡ የተከወነው የጃንደረባው ሕወሃት ጉባኤም በመተካካት ፕሮፓጋንዳ ይታጀብ እንጅ በነቀዘ ቡድንተኝነትና ድርጅታዊ አሰራር  የራስን የስልጣን ኮርቻ ለመቆናጠጥ በያቅጣጫው የተጣጣሩበት እንደነበር ገሃድ ሆኗል።

አጋር የሚባሉትም ሆኑ ወያኔን የፈጠሩት አባል ጉጅሌ ቡድኖች ካስቀመጧቸው ቦታ እስከሚያነሷቸው ድረስ በተቀመጡበት የሚጠብቁ እንጅ በራሳቸው ሂወት ዘርተው የሚላወሱ አልሆኑም። ስለነዚህ አጋርም ሆኑ መስራች ነን ስለሚሉት ቡድኖች የሚያስበውና የሚጨነቀው እንዲሁም ምን መስራት እንዳለባቸው ትእዛዝ የሚሰጠው በሙት መንፈስ የሚመራው ጃንደረባው ሕወሃት ነው። ይህማ ባይሆን ኖሮ የሀገሪቱ ወህኒ ቤቶች በግፍ ያላንዳች ከልካይ  በኦሮሞዎች ሲሞሉና የንግግር ቋንቋቸው ኦሮምኛ ሆኗል እየተባለ  ሰፊውን የኦሮሞ ሕዝብ እወከወላለሁ እያለ ራሱን የሚኮፍሰው የወያኔ አንዱ መስራች  ኦህዴድ ዝም ብሎ ባላየም ነበር።

በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በዲላ፣ በጉራጌ ዞን፣ በአዋሳ፣ በዋካ እንዲሁም በሌሎችም በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝባችን ባንዱ ወይም በሌላ ምክንያት አይሆኑ ሲሆንና ሰብኣዊ መብቱ በወያኔ ታጣቂዎችና ልዩ ሰራዊት መብቱ ሲገፈፍ የዚህን አካባቢ ሕዝብ እወከወላለሁ የሚለውና መስራች ነኝ ባዩ ደሕዴን አንዳች ድምጽ አላሰማም። እንዴውም ቻዝ እያለ ድርጊቱን የሚያስፈጽምና የጌታውን የሕወሃትን ሃሳብ የሚተገብር አቅም የሌለው ለዋሳ ቡድን ሆኗል።

አጋር የሚባሉት ቡድኖችም ቢሆኑ  የነበረባቸውን የጉልበት የእውቀትና የልምድ እጥረቶች ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በማንቀሳቀስ ጉድለታቸውን ሲያሟሉ እንዳልቆዩና እንዲሁም ራሳቸውም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እየተዟዛሩ ችግራቸውን ሲቀርፉ እንዳልኖሩ ሁሉ፤ ለዚህ በችግራቸው ወቅት አብሯቸው ለቆመው ሰፊ ሕዝብ በመቆም ፋንታ “ለተሾመ ይሟገቱለታል ለተሻረ ይመሰክሩበታል” እንደሚባለው ከሕወሃት ጋር በመወገን ያካባቢውንም ሆነ በስራ ምክንያት ወደ እነሱ የገባውን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለማሰቃየት መትጋታቸው ጉዳዩን አስተዛዛቢ ከማድረጉም በተጨማሪ ለቁጥር በስም የሚጠቀሱ ቡድኖች እንጅ አቅም ኖሯቸው የጃንደረባውን ሕወሃት የአገዛዝ መንገድ ለመቀየር የሚችሉ አለመሆናቸውን አስመስክረዋል።

ከሁሉም እጅግ የሚደንቀውና የሚያስገርመው፤ የወላጆቻችንን ፊውዳላዊ ስርአት ለማስወገድ ከእኛ ከልጆቻቸው የቀደመ አልነበረም በማለት በሰፊ አፉ የሚለፈውና አማራውን ወከሏል የሚባልለት የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) ያሁኑ አርበ ጠባቡ ብአዴን ሟሙቶ መጥፋት ነው። ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሚባል መልኩ በመመሪያ በብዛት በተለይ አመርኛ ተናጋሪው እየተመነጠረ ሲባረር ብአዴን የት አለ? ሕጻናትና ነፍሰጡር እናቶች ሲበለቱና ሲሰየፉ፣ የረጅ ያለህ፣ የወገን ያለህ እረ እባካችሁ ድረሱልን እያሉ በተስፋ ማጣት የቦዙትን ዓይኖቻቸውን በዙሪያ ገባው ሲያንከራትቱ ብአዴን በርግጥ የት አለ? ለዘመናት የደከመበት ላቡን ጠፍ አድርጎ ያጠራቀመው ሃብቱ በጠራራ ጸሐይ በግልጽ በሕዝብ ፊት ብልጦች እየተሻሙና እጣ እየተጣጣሉ የግላቸው ሲያደርጉት ብአዴን ምንም ትንፍሽ አለማለቱ “በጎደሎ ቀን የገዛሁት ጋሻ ሳያስገድለኝ አይቀርም አለ ፈሪ” እንደሚባለው ብአዴን አማራ የሚባለውን ብሔር ወክለሃል መባሉ የመጥፊያው ምንገድ እንዳይሆን ከመስጋቱም በላይ አቅሙ ከመታዘዝ ሌላ የማያወላዳ መሆኑን አሳብቆበታል።

በጀግንነቱ ይታወቅ የነበረውን የአማራ ሕዝብ በተለሳለሰ ቋንቋ ትጥቁን እንዲፈታ ያስተባበረው ብአዴን፤ በዚህ ሰፊ ሕዝብ ላይ በተጠናና በተደራጀ መልኩ የስነ ልቡና ጥቃት በመሰንዘር አቅመ ቢስ እንዲሆን በርተቶ ሰርቷል። በአሁኑ ሰአትም የተነሳሽነት መንፈሱን በመስለብ እንዲሁም አለ የሚለውን ቀሪ አቅም በመደፍጠጥና ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ በመስበክ ላይ ይገኛል። ወቅቱ የልማት ነው፣ ከባለራዕዩ መሪያችን ብልህነት የተሞላበት አመራር ጋር ወደፊት እየተባለ ሌት ከቀን የሚጨቀጨቀው የአማራ ሕዝብ እውነትም “ልብ ሲያልቅ ጥርስ ከደመኛው ጋር ይስቃል” ሆነና ከገዥው ጃንደረባው ሕወሃት ጋር ተባብሮ ግርፋትና ስደቱን፣ ሞትና ርሃቡን ችሎ ደንዝዞ በመከተል ላይ ይገኛል። 

ምንም እንኳ ከጥቂት ጥቅም ተጋሪዎች በቀር ሞትኩለት የሚለውን የትግራይ ሕዝብ ጥቅም ያላረጋገጠው ጃንደረባው ሕወሃት በፕሮፓጋንዳ ብልጠት ልክ የትግራይን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ዋልታና ማገር ሆኖ እየሰራ እንዳለና በዚህ ምክንያትም ጥርስ ውስጥ የገባ በሚያስመስል ንግግር “ለልጅ ሲሉ ይበሉ ለወገን ሲሉ ይጠሉ”ን እየዘመረ የማለያየትና የማጋጨት መርሁን በሰፊው ቀጥሏል። በመጥፎ አጋጣሚ ከነኝህ ፈውስ የለሽ ኮሶ ጉጅሌ ድርጅቶች የተጣባችው ሀገራችንም ሆነች ምስኪን ሕዝባችን የገፈቱ ቀማሽና የአገዛዝና የስልጣን ማራዘሚያ ስልቶች ቤተሙከራና መሞከሪያ  እንደሆኑ ቀጥለዋል።

የሰሞኑ የወያኔ ጉባኤ የሚያረጋግጠውም ጃንደረባው ሕወሃት መቼም ቢሆን ስለ ሀገርና ሕዝብ የሚጨነቅ አለመሆኑንና በራሱ በሕወሃት ውስጥ ከሚፈጠር አለመግባባትም ውጭ ለስልጣኑ የሚያሰጋ አንዳች ነገር አለመኖሩን ነው። “ሰባት ወልዳ አቃቢትነት” ማለት ይህ ነው። ኢትዮጵያችንን በዓለም ዙሪያ በጀግንነት ያስጠሩ ዛሬ የሉም። የትቁር ሕዝቦች መሪና ምሳሌ ያደርጓት እነኝያ ጥቋቁር ንዑድ አናብስት ለጆቿ ለዛሬ የሚሆን አንዳች ዘር አልተኩላትም። ያ የጀግንነትና ገናና ታሪክም ከነሱ ጋር አብሮ የሄደ እንጅ የዛሬዎቹ የእኛ አንዳች አሻራ የለበትም። የኛ የዛሬ ታሪክ በጃንደረባው ሕወሃት ነፃነታችን ተገፎ እንደቆሻሻ ተቆጥረንና ከዜግነት በታች ተዋርደን መታየታችን ነው። ዛሬ በእኛነታችን ዓለም የሚያውቀን በርሃብ ተገርፈን ለትርፍራፊ የምግብ ሲሳይ ከቆሻሻ ገንዳ ላይ ስንተራመስና ስደት እጣ ፈንታችን ሆኖ ማንም እንደፈለገ እየዘገነ ያሻውን ሲያደርገን ነው። ያባት ውርስ ያባት ነው፤ የወላጅ ሃብት ቢጠቀሙበትም አያኮራም፤ እንዳሻ ቢመዙትም አያረካም። በላባችን የተቦካ በደማችን የተጻፈ፤ እኛ የኛ የሆነ ስራ ሊኖረን ይገባል። የራሳችን አሻራ ያረፈበትን ስራ ለመስራትና ከስደት ከርሃብ እንዲሁም በጃንደረባው ሕወሃት መሰሪ አካሄድ ከተጣለብን የነፃነት እጦት በመውጣት ጉልህ ታሪክ የመጻፊያው ጊዜም አሁን ነው።  

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on April 4, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: