RSS

የወያኔ ጉጅሌ ከዘረኝነት ውጭ መኖር እንደማይችል ያውቃል

30 Mar

አምባገነን መንግስታት አገዛዛቸውን ለማቆየት ከሚጠቀሙበት ዋነኛ መሳሪያቸው ከሆነው የጦርና የደህንነት ሃይል ውጭ በርካታ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ልዩነትን ማራገብና ህዝብን መከፋፈል፣ ማስፈራራት፣ ዜጎች መረጃ እንዳያገኙ አማራጭ ሚዲያዎችን ሁሉ ማፈንና መዝጋት ብሎም የጥቂቶቹን ስብእና በጥቅማጥቅም  በመግዛት ሎሌና ጋሻ ጃግሬ በማድረግ፤ እንዲሁም በአገዛዛቸው የተማረረውን ህዝብ የተስፋ ዳቦ ላያድሉት እየጋገሩ ነገ የተሻለ ቀን ይመጣል እያሉ መስበክ ከብዙ ጥቂቶቹ ዘዴዎቻቸው ናቸው።

የሰሞኑን የወያኔ ጉባኤና ያወጣቸውን መግለጫዎች ልብ ብሎ የሚያጤን ኢትዮጵያዊ ሁሉ አንድ ነገር በግልጽ ማየት ይችላል። እሱም የጉባኤዉ ተሳታፊዎችና የወያኔ/ኢህአዴግ መሪዎች የሚጋሩት፤ አብሮ ያቆማቸዉና ከምንም በላይ የሚያያይዛቸው አንድ ነገር ቢኖር ፍርሃታቸው መሆኑ ነው። በአለም ዙሪያ በከፍተኛ ፍጥነት እየናኘ አምባገነኖችን እንደማእበል ከወዲያ ወዲህ እያናወጠ፣ እየጠራረገ በማስወገድ ላይ ያለው የህዝብ የዴሞክራሲና የሰበአዊ መብት መከበር ጥያቄ፣ የእነሱንም በር እያንኳኳ መሆኑ ከፍተኛ ፍርሃት ለቆባቸዋል።

እነዚህ ዘረኛ ቡድኖችና ግፈኞች የሚጋሩት ህዝባዊነት ያለው መርህና የሀገር ራእይ የላቸውም። ለዚህም ነው ጉበኤያቸዉን ሞቶ በተቀበረ ሰዉ መሪ ቃል ጀምረዉ በዚሁ በሞተ ሰዉ ራዕይ የጨረሱት። የዚህ ሰዉ ራዕይ ደግሞ ዘረኝነት፤ስደት፤ እስር፤ ግድያ፤ንቀት፤ዘለፋና ህዝብን ማዋረድ ነዉ። የኢህአዴግ/ወያኔ መሪዎች የሚያስተዉል አዕምሮ ስለሌላቸዉ አልተረዱትም እንጂ ለኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ በዘጠነኛ ጉባኤያቸዉ በግልጽ የነገሩት ነገር ቢኖር ፓርቲያቸዉ ኢህአዴግ የራሱ የሆነ ራዕይ የሌለዉ ጭራሽ በሞተ ሰዉ ራዕይ የሚንቀሳስ ሙት ፓርቲ መሆኑን ነዉ።

የወያኔ ጉጅሌ  ከዘረኝነት ውጭ መኖር እንደማይችል ያውቃል። ወያኔና ጉጅሌዎቹ በሙሉ የሚመኙት በዝርፊያ የደለበው ሀብታቸውና ምቾታቸው እንዲቀጥል፣ ሌላው ህዝብ በገዛ ሀገሩ ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ ክብሩን አዋርዶ መኖር መቀጠል አለበት ብለው ያምናሉ። የወያኔ መኳንንት; ኪስ እንዲደልብና ጓዳው እንዲደራጅ፣  በልማትና ትራንስፎርሜሽን ስም ሌላው ህዝብ  መሬትና ንብረቱ መዘረፍ አለበት። ወገን ከአያት ከቅድመአያቱ  ያገኘውን መሬት ለህንድና ለአረብ ቱጃሮች እያስረከበ መሰደድ አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆቹን በርሃብ ጠኔ እየቀጣ፣ እያስራበ፣ ህዝቡ የወያኔ ገዥዎችን ልጆች ፈረንጅ ሀገር ከፍሎ ማስተማር አለበት። በኢትዮጵያ ህዝብ ስም የሚመጣው ብድርና እርዳታ ሁሉ የወያኔ ቱጃሮች ማድለቢያ፣ መጨፈሪያ መሆኑ ይቀጥላል።

በወያኔኛ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ማለት ይሔ ነው። የመለስ ራእይ ማለት ባለፈው 21 አመት ያላየነው ምትሃት አይደለም። ሰፊውን የሀገራችንን ህዝብ የበይ ተመልካችና አጨብጫቢ አድርጎት የኖረው የመለስ ዜናዊ ዘረኛ የ21 አመታት አጅንዳ ነው። የወያኔና የሎሌዎቹ የጉባኤ መደምደሚያ ውሳኔ የቃላት ጋጋታ፣ ተበትኖ ሲፈተሽ ትርጉሙ “ላለፉት ሁለት አስርተ አመታት በገዛ ሀገራችን እንደ ሁለተኛና ተዋራጅ ዜጋ አድርጎን የቆየው አጅንዳ ተጠናክሮ ይቀጥላል፣ ግድያውና እስራቱ ይጨምራል፣ አርፋችሁ እየተዋረዳችሁ እየረገጥናችሁ የምናደርገውን ጉዞ እንቀጥላለን” ማለት ነው።

ወያኔና ሎሌዎቹ ከራሳቸው ጥቅም ውጭ ለማንም እንዳልቆሙ ደጋግመውም ነግረውናል አሳይተውናልም።

ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ይህ የወያኔ የግፍና የዘረፋ ስርአት እንዲወገድ መታገል ብቻ ሳይሆን ህዝባችን ትግሉን እንዲቀላቀል ጥሪውን ያቀርባል። የወያኔ ግፍኛ ስርአት መቀጠል የሚችለው ህዝባችን እስከፈቀደ ጊዜ ብቻ ነው።

ዛሬ በርካታ የሀገራችን ወጣቶች በወያኔ ዘረኛ ስርአት ተማረውና ተሰቃይተው፣ የጠባቡ ቡድን አባል ካልሆናችሁ ዳቦ ከቶ አትቆርሱም ተብለው ተገፍተዋል። የነጻነት ሃይሎችን ልሳን ሰምታችኋል፣ የመብት ጥያቄ ጠየቃችሁ፣ ተሰበሰባችሁ፣ በሚል ከውድ ሀገራቸው መሬት የተባረሩት ወጣቶች፤ ይህ ግፍኛ ጨቋኝ ስርአት ያቆም ዘንድ በእኛ ይብቃ ብለው ራሳቸውንና ሀገራቸውን ነጻ ለማውጣት በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ ወያኔን ለመፋለም ቆርጠው ተነስተዋል። ታዲያ ህዝባችን በመለስ የተጀመረውና አሁን በጉባያቸው ያረጋገጡልንን አዋርዶና በዘር ከፋፍሎ የመግዛት ራእያቸውን ለማስቆም፣ ሰቆቃን በኢትዮጵያ ምድር ለማብቃት  ከተነሱት ውድ የኢትዮጵያ የቁርጥ ልጆች ጋር  አብሮ መሰለፍ እና ትግሉን መቀላቀል ወቅቱ የሚጠይቀው ኢትዮጵያዊ የሞራል ግዴታ ነው እንላለን፡፡

 

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on March 30, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: