RSS

ከተዘጋው በር ጀርባ

15 Mar

ተመስገን ደሳለኝ

እነሆ በሶስተኛው በር ተገናኝተናልና አብዝቼ አላማርርም፡፡ ባማርርስ የት እደርሳለሁ? ማነው አገዛዙንስ ከስሶ የረታ? ደግሞስ ከመቼ ወዲህ ነው በሀገሬ መሬት ላይ ህግ የበላይ ሆኖ የሚያውቀው? ለማንኛውም የጠፋው ብርሃን በዚህ መልኩ ዳግም ይፈነጥቅ ዘንድ ስለተከፈለው ዋጋ ወይም ውጣ ውረድ ገድል የመፃፍ ፍላጎት የለኝም፡፡ ፍላጎቴ ከባልደረቦቼ ጋር በፀና መንፈስ በጀመርነው ጎዳና እንተም ዘንድ የመንግስትን አፈና አውግዛችሁ የሞራል ድጋፍ ለሰጣችሁን ኢትዮጵያውያን፤ እንዲሁም የአለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ተሟጋች ተቋማት ላሳያችሁት አጋርነትና ተቆርቋሪነት፣ በሀገሬ ላይ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ይሰፍን ዘንድ ዋጋ በከፈሉና እየከፈሉ ባሉ ወንድምና እህቶቼ ስም ልባዊ ምስጋናዬን ማቅረብ ነውና-ቺርስ ለነፃነታችን!  …አሁን በዚህ አምድ ላነሳው ወደ አሰብኩት ርዕሰ ጉዳይ ልንደርደር፡፡

የዘንድሮ ጥር እና የካቲት ወራት ለየት ባለመልኩ በሁለት ክስተቶች ላይ ትኩረት ስበው ነበር ያለፉት፡፡ አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው ሃያ ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ያሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ገዥው ኢህአዴግን የሚመለከት ነው፡፡ የእኔ የዛሬ ትኩረትም ሁለተኛው ነውና ጉዞ ወደ አጀንዳችን፡፡ እንደመግቢያ በኢትዮጵያ የፖለቲካውን መዘውር የጨበጡ ገዢዎች በሙሉ አራምደዋለሁ ብለው በይፋ የሚያውጁትን ርዕዮተ-ዓለም ለማስረጽ የሚሄዱባቸው መንገዶች የየራሳቸው መለያ (ገፅታ) እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በርካታ መለያዎች አሉት፡፡ በቀደሙት ስርዓታት ከማይታወቁ እና የኢህአዴግ መለያ ከሆኑት መካከል ለ‹‹ዶክመንተሪ ፊልም›› ያለው ፍቅር ዋነኛው ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ‹‹አስገኘሁት›› ከሚለው የኢኮኖሚ እድገት አንስቶ፣ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ላይ እስከሚፈፅመው ቅጥ-ያጣ ጉልበተኝነት ድረስ መከራከሪያው በጉምቱ ፖለቲከኞቹ የሚዘጋጀው ዶክመንተሪ ፊልም ብቻ የሆነው፡፡ ህገ-መንግስት፣ የተለያዩ ህጎች፣ አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች… በስርዓቱ መዝገበ ቃላት ላይ ቦታ ኖሯቸው አያውቅም፡፡

በሀገር ጉዳይ እና በመብት ጥያቄ ላይ ‹‹የነቃ ተሳትፎ ያደርጋሉ›› ወይም ‹‹ሊያደርጉ ይችላሉ›› ብሎ የጠረጠራቸውን እልፍ-አእላፍ የኦሮሚያ ተወላጆችን በኦነግ ስም ለመምታት በርካታ ዶክመንተሪ ፊልም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተስተናግዷል፡፡ እነ እስክንድር ነጋን እንዳሻው ከሚቆጣጠረው ፍርድ ቤት ተሽቀዳድሞ በሽብርተኝነት ለመወንጀል የቀረበውን ‹‹አኬልዳማ›› የተባለውን ቀሽም ፊልምስ ከቶስ ማን ይረሳዋል? የእስልምና ሀይማኖት መንፈሳዊ መሪዎች ላይ ለተመሰረተው የሀሰት ክስ ማስረጃ ‹‹ይሆነናል›› በሚል ቀመር ተዘጋጅቶ፣ ባለፈው ወር እንድንመለከተው የተደረገው ‹‹ጀሃዳዊ ሀረካት›› ፊልምም ስርዓቱን ራሱ ምን ያህል እንዳከሰረው ከማንም የተሰወረ አይደለም (በነገራችን ላይ ‹‹መለስ እንደወታደራዊ ሳይንስ መሀንዲስ›› የተሰኘው ዶክመንተሪ ፊልም አቶ መለስን በእጅጉ በተጋነነ ስብዕና አፍርሶ ለመስራት የተደረገ ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ለሰራዊቱ አመራር እጅግ ቅርብ ከሆኑ ሰዎች ሰምቻለሁ፡፡ በተለይ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት መለስ ስለነበራቸው ሚና አስመልክቶ የተተረከው ክፍል የፊልሙን ቅሽምና በሚገባ የሚያሳይ እንደሆነ ነው ያነጋገርኳቸው ያረጋገጡልኝ፡፡ እዚህች ጋ የምናገኘው ተጨማሪ አስቂኝ ነገር ሰራዊታችን ሻዕቢያን ከድንበራችን በኃይል ለማባረር ከምርጥ የጦር ታክቲክ /ብልሀት/ ይልቅ የሰው ኃይልን በብዛት መጠቀሙ ተደጋግሞ ሲተችበት የቆየ እውነት ሆኖ ሳለ ‹‹መለስ የጦር ጠበብት በመሆኑ በነደፈው ስልት ነው ኤርትራን ያሸነፍነው›› የምትለዋን የፊልሙን ‹‹ውዳሴ-ዘመለስ›› ስናደምጥ ነው) የሆነ ሆኖ ‹‹ጀሃዳዊ ሀረካት›› የተሰኘውን ፊልም ስመለከተው እንደተለመደው ተራ ከመሆኑም በላይ እርስ በእርስ በሚጣረሱ ጭብጦች የተሞላ ሆኖ አግኝቸዋለሁ (በዚህ ፊልም ላይ ከእነ ማስረጃዬ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)፡፡ ይሁንና ለነገ ሊተው የማይገባው አንድ ጉዳይ ግን አለ፡፡ ይኸውም በመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በሚኒስትር ደኤታ ማዕረግ ምክትል ሀላፊ የሆነው አቶ ሽመልስ ከማል ከሁለት ሰዓት ዜና በኋላ በታየው ‹‹ጀሃዳዊ ሀረካት›› ፊልም ላይ ያልተካተተ፣ ነገር ግን በእኩለሌሊቱ የኢቲቪ ስርጭት ወቅት በድንገት የታየውን (ኡስታዝ አቡበከር ሁለት እጆቹ በካቴና ታስረው መርማሪዎቹ ለሚጠይቁት ጥያቄዎች መልስ ሲሰጥ የሚያሳየውን) ፊልም በተመለከተ ለ‹‹ኢትዮ ቻናል›› የሰጠው ቃለ-መጠይቅ ነው፡፡ ለቁም ነገር ባይሞሉ ወሬዎች ከተሞላው የአቶ ሽመልስ ምላሽ ውስጥ እስኪ አንዷን እንምዘዝ፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝየመንፈሳዊ መሪዎቹ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ዶክመንተሪው በፍርድ ቤት ስራ ጣልቃ የሚገባ መሆኑን ጠቅሶ እንዲታገድለት ያቀረበው አቤቱታ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት አግኝቶ እንዲታገድ ቢወሰንም፣ የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ግን ተፈፃሚ እንዳይሆን ተከላክለዋል፡፡ በኋላም የአገዛዙ የፕሮፓጋንዳ ማሽን ኢቲቪ ፊልሙን መልቀቁ ወንጀል መሆኑን መነሻ በማድረግ ጠበቃው በተለያዩ ሚዲያዎች ላሰማው ተቃውሞ የሰጠውን አፀፋ ማለቴ ነው፡፡ ሚንስትር ዴኤታው፡- ‹‹…ፕሮፓጋንዳ ታስቦበት የተወሰነ እውነትን ደፍቀህ ሌላውን መርጠህ የምትፈልገውን ዓላማ እንዲከተልልህ ለማድረግ ህብረተሰቡ ላይ የአስተሳሰብ ጫና ለማድረስ ነው›› ካለ በኋላ፣ ‹‹…ይሄ ነጭ ቅጥፈት ነው፡፡…›› ሲል በራሱ መንግስት ላይ ምፀት የምትመስል ውንጀላን ተናገረ (መቼም ይህች ፍረጃ ደርጉ ተቀናቃኞቹን ይከስበት ከነበረው ‹‹ነጭ ሽብር›› የተገለበጠች ሳትሆን አትቀርም)፡፡

ይህ የአቶ ሽመልስ ምላሽ እንኳን ከሚያገለግለው ስርዓት ውጭ ላለው ታዛቢ ቀርቶ፣ ለራሱ ድርጅት ካድሬም ቢሆን ከልጆች ጨዋታ ያለፈ ትርጉም ሊኖረው እንደማይችል አይጠፋውም ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለእውነት ደፈቃም ሆነ ስለነጭ ውሸት የምር እንነጋገር ከተባለም የአቶ ሽመልስ እና የጓዶቹ ብቻ በርካታ መጽሐፍትና በርካታ ዶክመንተሪዎች እንደሚወጡት አልጠራጠርም፡፡ ስርዓቱ እውነትን በምን ያህል ደረጃ እንደሚደፍቅም ለማወቅ በአንድ ወቅት አለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ተቆርቋሪ ተቋማት ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን፣ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን፣ ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸውን… አስሮ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ደፍጥጧል›› በሚል ላቀረቡት ተቃውሞ፣ አቶ ሽመልስ አይኑን በጨው አጥቦ ‹‹እስክንድር ነጋን በጋዜጠኝነት አናውቀውም›› ያለውን ማየት ብቻ በቂ ይመስለኛል (እስክንድር በተለያዩ ጊዜያት ከስድስት ያላነሱ በስሩ የሚያስተዳድራቸው ጋዜጦች እንደነበሩት ይታወሳል)፡፡ እንዲሁም አቶ በረከት፣ አቶ መለስ ያደረበት ህመም ‹‹ነፍስ-ውጪ፣ ነፍስ ግቢ›› ላይ እንዳደረሰው በይፋ አምኖ ሳለ፣ ምክትሉ አቶ ሽመልስ ‹‹ይሄ የኢሳት እና የእሳት ወሬ ነው›› ሲል ማጣጣሉም የ‹‹ነጭ ቅጥፈት››ን ሰፈር አመላካች ይመስለኛል፡፡ ‹‹መንግስት በአደባባይ ይዋሽ ዘንድ በህግ ተፈቅዷል›› ካልተባለ በቀር፡፡ ከተዘጋው በር ጀርባ…

የድህረ መለስ አስተዳደርን ተከትሎ በህወሓት እና ኦህዴድ ውስጥ ‹‹ያደፈጠ ፖለቲካ›› እንዳለ በርካታ ተንታኞች መግለፃቸው ይታወሳl:፡ በተለይ ደግሞ ህወሓት ዛሬም ድረስ ከአናት ካሉ አመራሮቹ በቀር፣ በየትኛውም ደረጃ በሚገኙ አባላቱ ላይ ሳይቀር ህቡዕ ገብቶ የሀገሪቱ ቀጣይ ‹‹መልክ›› ምን መምሰል አለበት? የሚለውን የቤት ስራ ለማጠናቀቅ ደፋ-ቀና እያለ ነው፡፡ ፓርቲው እመራቸዋለው ከሚላቸው ዜጎቹ፣ ይጠብቁኛል ከሚላቸው ደጋፊዎቹና ይሞቱልኛል ከሚላቸው አባላቶቹ ጀርባ ሆኖ ዛሬም እንደተረበሸ ሾልከው የሚወጡ ድምፆች ያሳብቃሉ፡፡ ይህንን መከራከሪያ የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም የታተመው ‹‹The Economist››  መፅሄትም ‹‹Ethiopia’s new leadership is practicing hero-worship›› በሚል ርዕስ ባስነበበው መጣጥፍ ‹‹Jockeying among the elite has been kept behind firmly closed doors. In public it espouses business as usual. (በልሂቃኑ መሀከል ያለው መተጋገል በጥብቁ ከተዘጋው በር ጀርባ እየተካሄደ ቢሆንም፣ በአደባባዩ ግን ነገሮች በነበሩበት እየቀጠሉ እንደሆነ ለማስመሰል እየተሞከረ ነው) ሲል አጠናክሮታል፡፡ እናም ከመወያያ አዳራሹ ደፍ እንዳያልፉ የተደረጉትን ፖለቲካዊ አጀንዳዎች በጨረፍታ እንያቸው፡፡

፩  በሀገሪቱ መፃኢ ዕድል ላይ እንደዋነኛ ስጋት ተደርጎ የተወሰደው ‹‹በህወሓት ውስጥ ተፈጠረ›› የተባለው ልዩነት ነው፡፡ የልዩነቱ አንጓ ምክንያት ተደርገው ከሚቀርቡት መካከል ቀልቤን የሳቡት፡- መለስ ‹‹ብቸኛው ሰው›› (Strong man) እንዲሆን የትሮይ ፈረስ ሆነው አገልግለዋል ተብለው የተፈረጁ የአመራር አባላት መኖር፣ ‹‹መለስ ከፖለቲካውም ሆነ ከኢኮኖሚው ጨዋታ አግልሎን ነበር›› በሚል ቅሬታ ስር የተሰባሰቡ ባለስልጣናት፣ ‹‹የትግራይ ህዝብን ከሌላው ብሄር የሚነጥል ስልት በመከተል ተሳስተናልና ማስተካከል አለብን››  የሚል አቋም የያዙ አመራሮች መምጣት፣ አውራጃዊነት፣ ዝምድናና ጋብቻ የፈጠረው ቡድንተኝነት… በመጀመሪያው ረድፍ ይቀመጣሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም ‹‹አቶ መለስ በህይወት በነበረበት ጊዜ ድርጅቱን ደካማ በማድረጉ፤ የእርሱ ህይወት ካለፈ በኋላ ስልጣን ከድርጅታችን እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል›› በማለት ጥቂት የአመራር አባላትን እና የታችኛው ካድሬን በፓርቲው ላይ የማነሳሳት ሙከራ ባደረጉት አቦይ ስብሃት ነጋ እና በተቀረው የህወሓት አመራርም መካከል አደጋ ሊያደርስ የሚችል ልዩነት ተፈጥሮ እንደነበር ይነገራል፡፡ የሆነ ሆኖ በአቦይ ስብሀት ነጋ ፊት-አውራሪነት እየተንቀሳቀሰ ነው ተብሎ የሚታሰበው የህወሓት ግንጣይ፣ በእነአባይ ፀሀዬና ደብረፅዮን መስመር ከተሰለፈው ብዙሀኑ አመራር ጋር የነበረውን ልዩነት ባለፉት ሁለት ወራት በምን መልኩ እና በማን ሸምጋይነት ለድርድር ቀርበው
ስምምነት ላይ እንደደረሱ ግልፅ ባያደርጉትም፣ መግባባት ላይ መድረሳቸውን አንድ የድርጅቱ የቅርብ ሰው አረጋግጠውልኛል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ስብሃት ነጋ፣ አቶ መለስ ከአደባባይ ከራቀ ጀምሮ ከ‹‹ፋጡማ›› እና ‹‹በቀለ›› ጋር በማነፃፃር ሲያጣጥሉ የነበሩበትን አካሄድ አርመው (በድርጅቱ ቋንቋ ግለ-ሂስ አድርገው) እንደአብዛኛው የኢህአዴግ አመራር ‹‹የመለስ ራዕይን ለማስፈፀም…›› የሚሉ ቃላቶችን በንግግራቸው መጀመሪያ ሲጠቀሙበት ተስተውለዋል፡፡ከዚህ በግልባጩ ደግሞ ሁሉም የህወሓት ሰዎች ሙሉ በሙሉ መግባባት ላይ እንዳይደርሱ ያስቸገራቸው ሌላኛው ደግሞ የቀድሞዎን ቀዳማዊት እመቤትንና ተከታዮቿን ፍላጎት ተመስርተው የሚነሱ ጥያቄዎችን በቀላሉ መመለስ አለመቻሉ ነው፡፡ የእነወ/ሮ አዜብ መስፍን ጥያቄ የሁለቱንም ፖለቲካዊ ጥማቶች አርክቶ፣ በህወሓት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ አብዛኛውን አመራር ከጎኑ ማሰለፍ ከቻለው ቡድን ጋር ለመቆም አሁንም ጊዜው ገና ይመስላል።

በእርግጥም በቢሊዮን የሚቆጠር ንብረት ያለው የኤፈርት ስራ-አስኪያጅነት መንበር ዛሬም በአዜብ እጅ መሆኑ፣ የበላይነት ያለውን የህወሓት አመራር ምቾት ቢነሳ አስገራሚ ላይሆን ይችላል፡፡ ይህን ጉዳይ ለጥጠን አዜብ መስፍን በሚያዚያ ወር ለሚካሄደው የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት እጩ ሆና ከመቅረቧ ጋር ካያያዝነው፣ ምናልባትም የኤፈርት ስራ አስኪያጅነት ቦታዋን በከንቲባነት ለመለወጥ ስምምነት ላይ ደርሳ ሊሆን ይችላል ብለን እስከ መከራከር ልንደርስ እንችላለን፡፡

እንደተጨማሪ መላ-ምት የአዜብን ወደ ከንቲባነት የማምጣት የፓርቲውን መግፍኤ ከሌላ ጫፍም ማየት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ይኸውም የሴትዮይቱ ፖለቲካዊ ስብዕና ከመለስ የቀድሞ ማንነት፣ እንዲሁም አሁን እየተባለ ካለው ‹‹ባለራዕይነቱ›› ጋር መተሳሰሩን ጠንቅቆ የሚያወቅው ህወሓት በቀጣዩ የ2007 ዓ.ም የፌደራል ምርጫን በሟቹ ስብዕና ስም መወዳደሩ ማትረፍ፣ ያለማትረፉን ለማረጋገጥ የወ/ሮይቱን ከንቲባነት የፕሮፓጋንዳው ሙቀት መለኪያ ለማድረግ አስቦ ሊሆን ይችላል የሚል ነው፡፡ ማለትም የአዲስ አበባ ነዋሪ ‹‹የመለስ ሀሳብ ሳይከለስና ሳይበረዝ›› ለምትለዋ ወ/ሮ አዜብ የሚሰጠው ምላሽ፣ ፓርቲው በቀጣዩ ምርጫ የመለስን ስም በመሸጥ ለመወዳደር የሚያደርገውን ዕቅድ መወሰኛ ሁነት ይሆነዋል፡፡

ሌላው ፈተና ሆኖ ዛሬም ድረስ የዘለቀው ‹‹እነስዬ ይመለሱ›› የሚለው የታችኛውን ካድሬ ግፊት፣ ህወሓት ሊሆን እንደማይችል አሳምኖ ማስቆም አለመቻሉ ነው፡፡ የዚህ ሀሳብ አቀንቃኞች መከራከሪያ አድርገው የሚያቀርቡት ‹‹በ1993 ዓ.ም ህወሓት ለሁለት መከፈሉን ተከትሎ ጠንካራው አመራር ሲባረር፣ በምትኩ ብቁ የሆነ ተተኪ ስላልተፈጠረ ድርጅታችን ተዳክሟልና የቀድሞ አመራሮቹ ወደ ድርጅቱ ተመልሰው ፓርቲያችን መጠናከር አለበት›› የሚል ነው፡፡ የሀሳቡ ደጋፊዎች ‹‹የተሻለ አመራር የሚሰጥ ብቃት ያለው ሰው ባለመኖሩ ነው ስልጣኑ ከህወሓት እጅ የወጣው›› የሚል እምነት አላቸው፡፡ ይሁንና ህወሓት አሁን ባለበት ደረጃ ይህንን ጥያቄ ማስተናገድም ሆነ ማንሳት እንደማይቻል አቋም የያዘ ይመስላል፡፡ በአናቱም ‹‹መለስ እንደወታደራዊ ሳይንስ መሀንዲስ›› የሚለው ዶክመንተሪ ፊልም እንዲቀርብ የተደረገው ‹‹የድርጅታችን አንጎልና ልብ መለስ ብቻ ነበር›› የሚል የጎንዮሽ መልዕክት በማስተላለፍ ‹‹እነ ስዬ ይመለሱ›› የሚለውን ጥያቄ ለማምከን በሃሳቡ ነቃፊዎች የተቀመረ ነው ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡

፪  በኦህዴድ ውስጥ የተፈጠረው ቀውስም እንዲሁ መፍትሄ አላገኘም፡፡ ምናልባትም ኦህዴድ ከተመሰረተ ጀምሮ እንደ ድህረ-መለስ ዘመን አይነት በስብሰባ የመወጠር ታሪክ አጋጥሞት የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ኦህዴድ መፍትሄ እንዳያገኝ እንቅፋት ሆነው ከተከሰቱበት ችግሮች መካከል ዋነኛው ከእግሩ ራሱን ችሎ የቆመ ይምሰል እንጂ፣ አናቱ በህወሓት ውስጥ መገኘቱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይኽም ከእነአባይ ፀሀዬና ከእነአዜብ መስፍን ልዩነት የሰረፀ ይመስለኛል፡፡ በጥቅሉ የኦህዴድ አመራር አሰላለፍ አባዱላ ገመዳ፣ ኩማ ደመቅሳ፣ ሙክታር ከድር… የመሳሰሉት ከጠቅላይ ሚንስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ጀርባ ሆኖ የፖለቲካ ስልጣን በያዘው ጠንካራው የህወሓት አመራር ስር ሲሆን፤ አስቴር ማሞ፣ ሶፊያን አህመድ፣ አለማየሁ አቱምሳ… ደግሞ ወደ እነ አዜብ መስፍን ቡድን የማዘንበል አዝማሚያ ይታይባቸዋል፡፡ (በኦህዴድ ውስጥ የቡድን አባቶች እነዚህ አመራሮች ናቸው) ሁለቱም (የህወሓት ቡድኖች) ኦህዴድን ‹‹ችግር መውጪያ›› ማድረግ መፈለጋቸው ነው ድርጅቱን መረጋጋት የነሳው፡፡ በተጨማሪም የኦህዴድ አመራሮች ከህወሓት ሁለቱ ቡድኖች ጋር ለመሰለፍ መስፈርት ያደረጉትም የድርጅታቸው መለያ የሆነውን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ መንደርተኝነትን እና የጥቅም ግጭትን ለመዳኘት፣ በህወሓት ሰዎች የተያዘውን አቋም ነው፡፡ በአናቱም የህወሓት የታሪክ ንባብ እንደሚነግረን በድርጅቱ ውስጥ ልዩነቶች ሲከሰቱ በአሸናፊነት ለመውጣት የትኛውንም ህግ መጣስ እና ሀገራዊ ጥቅምን አሳልፎ መስጠት አዲስ ነገር አለመሆኑን ነው (ቀጣዩ የኦሮሚያ የፕሬዝዳናት ወንበርም ለኦህዴድ አመራር ማማለያ ሆኖ ቀርቧል)

፫  የድህረ-መለስ ኢህአዴግ ከፖለቲካው ጋር ለተያያዙ ችግሮቹ እልባት ለመስጠት ከህግ ውጪ መስራትን እንደ ስልት የያዘው ይመስላል (የሶስቱ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሮች ሹመት አንዱ ማሳያ ነው)፡፡ ስርዓቱ የጠቀስኳቸውን የውስጥ የቤት ስራዎቹን በአግባቡ ያለማጠናቀቁ መንግስታዊ ተቋማትን በማቀዛቀዝ ሀገሪቷን እየጎዳት እንደሆነ ከውስጥም ከውጭም እየተሰማ ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኩት የዘ ኢኮኖሚስት መፅሄት ዘገባም ‹‹ከመለስ ውጪ ህልውናቸውን ማስቀጠል የተሳናቸው›› እና ‹‹ግራ የተጋቡ›› ያላቸው መሪዎች ኢኮኖሚውን ነፃ የማድረጉን ጉዳይ ከሚቀጥለው አገራዊ ምርጫ ወዲያ አሻግረውታል ሲል አመራሩን አብጠልጥሏል፡፡ ሌላኛው ተያያዥ ጉዳይ የሀገሪቱ ህዝባዊ ተቋማት የእርስ በእርስ የስራ ግንኙነት በመለስ ዘመን በነበረው ልክ እንኳን መሄድ ያለመቻሉ ነው፡፡ ለዚህም ማስረገጫ የሚሆነው በቅርቡ የወጣው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጪ ዜጎች በጥብቅና እንዳይሰማሩ የሚያግደው አዋጅ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ የነጋገርኳቸው አንድ የህግ ባለሙያ እንደሚሉት ስለጉዳዩ የፍትህ ሚንስቴር ባልስልጣናትንም ሆነ የጠቅላይ ሚንስትሩን ፅ/ቤት ሲጠይቁ ‹‹እንዲህ የሚባል አዋጅ መውጣቱን አናውቅም›› ሲሉ መልሰውላቸዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ተቋማት የማያውቁት አዋጅ እየወጣነው ከተባልን ሀገሪቱን ማን እየመራት ነው? የሚለው ጥያቄ አሁንም መጠየቅ የሚችል ይመስለኛል፡፡ እናም በየተቋማቱ ውስጥ ያሉ ዝቅተኛና መሀከለኛ አመራሮች ‹‹የሚመራንና ሪፖርት የምናደርግለት አጣን›› የሚል ጉሩምርታ እያሰሙ ነው፡፡

የሆነ ሆኖ ስርዓቱ አሁንም ህግ በመጣስ፣ ደንብ በመሻር የመቀጠል ፍላጎቱን የሚያመላክቱ ፍንጮች እየታዩ ነው፡፡ እንደምሳሌም የፓርላማ ውክልና ያላቸው ተመራጮች ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ለመወዳደር የሄዱበት መንገድ ለዚህ ድምዳሜ ተጨማሪ ማሳያ ነው፡፡ አዜብ መስፍን፣ ሲራጅ ፈጌሳ፣ ተፈራ ደርበው፣ መኩሪያ ኃይሌ፣ ወርቅነህ ገበየው የፓርላማ ተመራጭ ሲሆኑ፣ የአገልግሎት ዘመናቸው የሚያበቃውም ከ2007 ዓ.ም. በኋላ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ እንደራሴዎች በቆረጣ ወደ አዲስ አበባ ምክር ቤት ለመግባት እጩ ተመራጭ ሆነው ቀርበዋል፡፡ ይሁንና ችግሩ ለውድድር መቅረባቸው አይደለም፤ የምክር ቤቱ አሰራር በሚፈቅደው መልኩ አለመሆኑ እንጂ፡፡ በምክር ቤቱ ደንብ መሰረት አንድ አባል ከውክልናው ለመልቀቅ ሲፈልግ ደብዳቤ ጽፎ በአፈጉባኤው በኩል የምክር ቤቱ አባሎች እንዲያውቁት ማድረግ ግዴታው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ባለስልጣናት ግን ከፌደራል ወደ አዲስ አበባ ምክር ቤት የዞሩት ይህንን መስፈርት በተከተለ መልኩ ሳይሆን በቀጥተኛ የፓርቲው ውሳኔ መሆኑን በፓርላማው የመድረክ ብቸኛ ተመራጭ የሆነው አቶ ግርማ ሰይፉ አረጋግጦልኛል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በዙሪያቸው የዴኢህዴን ሰዎችን በማሰባሰብ በራሳቸው ለመቆም የመሞከር አዝማሚያ እያሳዩ ከመሆናቸው በተጨማሪ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት እና አንዳንድ የመለስ ፖሊሲዎችን በመከለስ ‹‹አሻንጉሊት››  የሚል ትችት ለሚያቀርቡባቸው ነቃፊዎቻቸው፣ ጥንካሬያቸውን ማሳየት እንደሚፈልጉ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ለደኢህዴን ቅርብ የሆኑ ሰውም ‹‹ኃ/ማርያም ከጠርሙሱ የወጣ ጂኒ የሚሆንበት ጊዜ ያን ያህል ሩቅ ላይሆን ይችላል›› ብለውኛል፡፡ በእርግጥ ይህንን መላ-ምት ያጠናከረው እርሳቸው ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ፣ ሁለት የደኢህዴን ሰዎች በጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ሲሾሙ፣ አንድ ሌላ የፓርቲው ሰው ደግሞ የፀረ-ሙስና ምክትል ኮሚሽነር እንዲሆኑ መደረጉ ይመስለኛል፡፡ በግሌ እነዚህ ሁሉ ስራዎች ከእርሳቸው ጀርባ ያለውን ኃይል የያዙት አንጋፋ ታጋዮች ‹‹ሰውየው አሻንጉሊት አይደለም›› የሚል የማሳሳቻ መረጃ ለመስጠት እያደረጉት ያለ ነገር አይደለም ለማለትም አልደፍርም፡፡

…የሆነ ሆኖ ይህ ሁሉ የፖለቲካ አጀንዳ በተዘጋ በር ውስጥ ተፈጭቶ ሲቦካ ብአዴን የት ነው ያለው? እንዲህ ድምፁን ያጠፋው አድፍጦ ወይስ ተደፍጥጦ?

 
Leave a comment

Posted by on March 15, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , ,

Leave a comment