RSS

ወያኔ መቼ ይሆን እራሱን የሚያየው?

07 Feb

ከይኸነው አንተሁነኝ

የካቲት 07 2013

የታየው ድንገት የሚጠፋበት፣ የተፈለገው ለመድሃኒት ያክል እንኳ የሚታጣበት፣ ከኔ ጋር ነው ተብሎ የነበረው ሳይታሰብ የሚለይበትና ስምምነት የተደረሰበት ሳይቆይ የሚፈርስበት ወቅት። ሰአታት ወቅቶችና ዓመታት ብቻ አይደሉም ትእይንቶችም እንደ ሸማኔ መወርወሪያ እየተምዘገዘጉ ነው።ጎን ለጎን ከአቻ የስልጣንና የደረጃ ጓደኛ ጋር፤ ከላይ ወደ ታች ወይም ከታች ወደ ላይ አለቃ ከምንዝር ምንዝር ካለቃ ሳይለይ የሚቧደኑበት የሚተሻሹበት የሚጓተቱበት ዘመን። ዘመነ ጭንቅ ንትርክ። ተረጋግቶ በቅጡ መቀመጥ ሳይጀመር ድሮም ካቅም፣ ከችሎታና ከልምድ ውጭ ከተሰጠ የወያኔ ወንበር ጋር እጥላለሁ አትጥልም ትግል የሚጀመርበት ወሳኝ ምእራፍ ተጀምሯል። ምድርን ከውስጧ እየሞቀ ቀቅሎ የሚያፈላትና የሚያነትራት ገሞራ አይነት ውስጠ ትርምስ ወያኔን ፈንድቶ ሊበታትነው መብላላቱን ጨርሶ መናጥ ከጀመረ ረፈደ። ምናልባት ለወያኔ የቀረው ነገር ንዝረቱን ማቆም ሳይሆን የሚያስከትለው አደጋ ሰፊና አሰቃቂ እንዳይሆን ጥቂት መድከም ሊሆን ይችላል። እሱም ቢሆን ከተሳካ ነው።

የህወሃት መከፋፈል አይቀሬ መሆኑን የሚያመላክቱ ጥርት ያሉ ምልክቶች መታየት ከጀመሩ የቆዩ ቢሆንም እንዲህ እንደ ሰሞኑ ሃሳቦች ወደ ተግባር አልተቀየሩም ነበር። አሁን ግን እያንዳንዱ ከፍተኛ የህወሃት አለቃም ሆነ አባል መስመሩን ለይቷል። ሁሉም በቃልም ሆነ በደብደቤ የማስጠንቀቂያም ሆነ የትብብር መልእክት ደርሷቸዋል። ሁሉም ማን ከማን ጋር እንደተሰለፈ በዝርዝር ባያውቅም ለራሱ ግን መበታተን ከመጣ ከነማን ጋር ሊሰለፍ እንደሚችል ወስኖ ፊሽካ የሚነፋበትን የመጨረሻዋን ሰአት እየተጠባበቀ ይገኛል።

ጊዜው ለነገ የሚባል ነገር የሚተውበት አይደለም ፈጣን ውሳኔ የሚሰጥበት እጅግ ወሳኝ ጊዜ እንጂ። ህወሃት በራሱ ውስጥ የሚብላላው ችግር ሳያንሰው፤ የሌሎች ወያኔን የመሰረቱ ድርጅቶች አሰላለፍ ምን ሊሆን እንደሚችል አለማወቁም አስጨንቆታል። በአባላቱ መካከል ያለው የአሰላለፍ አለመስከንና ወጥ አለመሆን አሳስቦታል። ልክ እንደ 1993ቱ የወያኔ ክፍፍል እዚህ ያሉት እዚያ እዚያ ያሉት እዚህ አይነት አጋጣሚ እንዳይከሰት እርግጠኛ ለመሆን ወያኔ ያለእረፍት ደቂቃ በደቂቃ እየደከመ መሆኑ ይሰማል። ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በሗላም ሊመጣ የሚችለው ውጤት አሉታዊ ይሁን አወንታዊ የሚታወቅ ባለመሆኑ ለህወሃት ሌላ ፈተና ሌላ ራስ ምታት እንደሚሆን አይጠረጠርም።

የወያኔ ሌላው ክፋይ ኦህዴድ ሰላም አጥቷል። የዚህ ድርጅት ሰላም ማጣት ለሌሎችም የወያኔ ክፍልፋዮች እንዳይተርፍና አጠቃላይ ትርምስ እንዳይፈጠር ወያኔ ከወራት በፊት ጀምሮ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር ይታወቃል። ሆኖም ግን የተሳካለት አይመስልም። ኢህዴድም እንደ ፈጣሪው ህወሃት በሰብሶ ሊፈረካከስ ከጫፍ እንደደረሰ እየወጡ ያሉ ወቅራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። እዚህም መቧደኑ በፍጥነት እየተካሄደ ሲሆን መቺና ተመቺ በማለትም እራሳቸውን እንደመደቡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ነገር ግን የተለያዩ የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት ግን ለምሳ ሊያደረጓቸው ያሰቧቸውን እነሱ ቀድመው ቁርስ ላለማድረጋቸው ምንም ማረጋገጫ የለም። እዚህ ላይ መቺ የነበረው ተመቺ ሆኖ ሊገለባበጥ መቻሉ አይደለም ጉዳዩ የነሱ ያላግባብ ትርምስ ሀገራችንንም ሆነ ምስኪን ሕዝባችንን ለአደጋ እንዳያጋልጠው እንጂ። ስለሆነም  ”የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሃዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ” እንደሚባለው በዚያም አለ በዚህ ለወያኔ ጭንቀቱን የሚጨምር እንጂ ፋታ የሚሰጠው አልተገኘም።

በሌላ በኩል ደግሞ ለወራት የእንወያይ ጥያቄያቸው መከጤፍ የተቆጠረባቸው 29ኙ የተቃውሞ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ለምርጫ እንዳይመዘገብ ጥሪ እንዳቀረቡ ይሰማል። ወያኔ ቀድሞውኑ ሲፈራው የነበረው ይህንኑ ነበርና ለስሙ የነበረው ምዝገባ ጭራሹኑ አልም እንዳይል ሰግቷል። ምናልባት ይሄ ውሳኔ      ሁሌም አጭበርብሮ ተመረጥኩ ለሚለው ወያኔ ምንም ሊሆን ይችላል ነገር ግን የመራጩን ሰልፍ እያሳዩ መስረቅና በባዶ ሳጥን ማጭበርበር ለወያኔም ሆነ ለታዛቢ ድርጅቶች የሚያስተላልፈው መልእክት በጣም የተለያየ ነው። ስለሆነም ወያኔ የምዝገባ ቀናትን ማራዘምን ጨምሮ ሌሎችንም የማይፈልጋቸውን ውሳኔዎች ለመውሰድ የተገደደው ሁኔታው በፈጠረበት ከፍተኛ ጭንቀት እንደሆነ ይሰማል።

በአክሱም፣ በባህርዳር፣ በጎንደር፣ በጅማ በአዲስ አበባ፣ በሀረር የኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች እያሰሙ ያሉት የእንደመጥ ጥያቄ ምንም እንኳ ምክንያታቸው የተለያየ ቢሆንም ባንዱ ወይም በሌላው ጥያቄያቸው ከመልካም አስተዳደር እጦጥ ጋር የተያያዘ ነው። በተማሪዎች መካከል የሚደረገው መድሎ፣ እየቀረበላቸው ያለው አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀ አለመሆን፣ የግል ወይም የጋራ መብታቸው በተደጋጋሚ መጣስና ተወያይቶ ለማስተካከልም ዝግጁ አለመሆንና ሌሎችም ተማሪዎቹን ከእለታት የምግብ አለመመገብ አድማ አንስቶ ግቢውን ጥለው እስከመውጣት የሚደርስ ወሳኔ እነዲወስኑ አድርጓቸዋል። ለቀደሙት የሀገራችን ገዥዎች መውደቅ በተለይም ለንጉሱ መዳከምና በሗላም ከስልጣን መውረድ የመጀመሪያዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸውን በደንም የሚያውቀው ወያኔ  የእነዚህን የዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ጥያቄ ባግባቡ ተቀብሎ በቂ መልስ አለመስጠቱና ቀጥሎ የሚሆነውንም መገመት አለመቻሉ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከቶታል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ነፍጥ ያነገቡ ኢትዮጵያዊያን ተቃዋሚ ድርጅቶች አንድነት ሃይል ነው በማለት ወደ ትብብር መምጣታቸው፤  አልፎ አልፎም ቀላል የማይባል ጥቃት መሰንዘራቸው ብቻ ሳይሆን ይኸው ዜና በሕዝባችን ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀባይነትና ድጋፍ ማግኘቱ፤ ባጭር ጊዜ ውስጥም እነዚሁ ሃይሎች በአባላት እየተበራከቱ መሆኑ መሰማቱ በወያኔ ዘንድ ከፍተኛ መተራመስ አስከትሏል። በዚህ አዲስ ክስተት የተደናገጠው ወያኔ ተቃዋሚዎች ጥቃት ወዳደረሱባቸውና ችግር ሊፈጠርባቸው ይችላል ወደተባሉ ሌሎች አካባቢዎች ከፍተኛ ወታደራዊ ሃይል ማጓጓዙም ታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከዓመት በላይ ሳይበርድ የቀጠለውን የሙስሊሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለማቀዝቀዝ እጅጉን የተቸገረው ወያኔ ድጋፍ ፍለጋ ወዲህ ወዲያ እያለ ሲሆን፤ በተለይም ክርስቲያኑን ከሙስሊሙ በማጋጨት ተጠቃሚ ለመሆን የሙስሊሙ እንቅስቃሴ ለክርስቲያኑ አደጋ እንደነበር አስመስሎ ለማሳየት ከዚህ በፊት እንዳየነው አኬልዳማ ድራማ አይነት አዘጋጅቶ ለሕዝብ አሳይቷል። ምንም እንኳ  የሚፈልገውን ያህል ድጋፍ  ከሕዝብ ባያገኝም።

ክርስቲያኑ ሕብረተሰብ ወያኔ ባዘጋጀለት የግጭት ሴራ ተባባሪ እንደማይሆን ባለፈው አንድ ዓመት አስረግጦ አስመሰክሯል። አንድነትንና መከባበርን አጥብቆ የሚሻውና በራሱ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና መከራ በዝምታ እየተመለከተ ያለው ይህ ክርስቲያን ምእመን፤ እየደረሰበት ባለው ችግር ምክንያት ነገ ምን እርምጃ እንደሚወስድ ግልጽ ባለመሆኑ ወያኔ እየሳበ ያለው ምላጭ ወደ ራሱ ባርቆ ጉድ እንዳያደርገው በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ተዘፍቋል።

እርስ በርሱ የተቆላለፈውና ያንደኛው ውጤት በሌላኛው ላይ ተጽእኖ በማድረግ መዘወሪያውን ወዳልታሰበ አቅጣጫ እንዳያዞሩት የሚያሰጉት እነኝህ ሁሉ እንቅስቃሴዎች እዚህ ካልተጠቀሱ ሌሎች ኩነቶች ጋር ተዳምረው ወያኔን ከፍተኛ ጭንቀትና እርስ በርስ ጥርጥር ውስጥ ከተውት ሰንብተዋል።

ወያኔ በእርግጥ ያልታደለ ድርጅት ነው እንጅ የዚህ ሁሉ መፍትሄ እራስን መመልከት ወደራስ ማየት ነበር። የሁሉም ችግሮች መነሻ ሌሎች በማለት ፋንታ ሕዝቡ ምን ይላል ለዚህስ እኛ ምን አደረግን ብሎ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ የዕይታ መነጽር ውጭ ራስን መፈተሽ ማየትና መፍትሄውን ከራስ መጀመር ቢሞክር በእርግጥም የችግሮቹ ሁሉ ቁልፎች በቀላሉ በተገኙ ነበር። ወያኔ ግን የባለራዕዩን እይታዎች መርጦ በመንቀሳቀስ ላይ በመሆኑና ይህ ደግሞ እስከ አሁን የሆነውና እየሆነ ያለው ጥፋት ቀጣይ ስለሆነ ውጦቱ እልቂት ነው። ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ እሩቅ መሄድ ሳያስፈልገን  ከላይ የተዘረዘሩትንና እየሆኑ ያሉትን ግልጽ ድርጊቶች ማስተዋል ብቻ በቂ ነው። አበቃሁ።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on February 7, 2013 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: , , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: