RSS

በደል ይረሳል ወይስ ይለመዳል (3)

13 Dec

ከይኸነው አንተሁነኝ

ታህሳስ 13 2012

ኩልል ካለው ብሩህ ሰማይ የተንጠለጠለችው ደማቅ ፀሐይ ባጀብ የወጣች ያህል አካባቢው በሙሉ ግሏል። የአዲስ አበባው ጥቁር አስፋልት ከሙቀቱ የተነሳ ከርቀት ሲመለከቱት የባህር ግማሽ አካል መስሎ ለዓይን የሚያሰጋ ነጸብራቁን ከመርጨቱም  በላይ ሙቀቱ የተጫሙትን ጫማ አልፎ ውስጥ እግርን መለብለብ ጀምሯል። ሽምጡን ጨርሶ እንደተመለሰ ላብ ያጠመቀው ሰጋር ሰንጋ ፈረስ አልፎ አልፎ በሬንጅ ቅላጭ የተወለወለው አስፋልት ከጫማ ጋር ፍቅር እየያዘው ለእርምጃ አስቸግሯል። እዚህም እዚያም ከሚሯሯጡት ጥቂት ታክሲዎችና የከተማ ባሶች በቀር ሁሉም ጸጥ እረጭ ብሏል። የሰው እንቅስቃሴ ላመል ነው። ሁሉም በየቤቱና ቴሌቪዥን ባለበት መዝናኛና የቀበሌ ክበቦች ታድሟል። በያለበት ዓይኖቹን በየቴሌቪዥን መስኮቶች ላይ ሰክቶ ቀጥሎ የሚመጣውን ትእይንት በጉጉት ይጠባበቃል።  1997ዓ/ም የበጋ ወራት እለተ ሰንበት ከስአት ነበር ጊዜው።

ወያኔ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ነኝ ብሎ ለዓለም ባዋጅ ለማስመሰል በጠባቡም ቢሆን የከፈተው ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የእንወያይ መድረክ ክፉኛ እየወዘወዘው፣ ማንነቱን እያጋለጠበትና እያስኮረኮመው ይገኝ ነበር። ዘግይቶም ቢሆን ከፓርቲነት ጎራ የተቀላቀለው ቅንጅት ደግሞ ያለችውን ጊዜ ባግባቡ ለመጠቀም በተገኘው አጋጣሚ ጊዜና መድረከ ሁሉ ባለ በሌለ ሃይሉ እውነተኛ የሕዝብ ወገን መሆኑን ለማስመስከር የሚታገልበትና የሚሮጥበት ፈታኝ ጊዜ።

ወያኔ ከስም አይጠሬው ጎጠኛ መሪው በቀር አሉኝ የሚላቸው ቱባ ቱባ ባለስልጣኖቹ ከዛሬ በፊት በነበሩት የተለያዩ መድረኮች ቀርበው ተራ በተራ በዝረራ ተሰናብተዋል። የዛሬውም በተመሳሳይ መልኩ እንደሚደመደም ተስፋ ተጥሏል። የሀገራችንን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማሕበራዊ ህጸጾች በሚያነሱ ጉዳዮች ላይ በመወያየት አይቀጡ ቅጣት እየተቀጡ ባሳዛኝ ሽንፈት ለሕዝብ እራቁታቸውን በታዩበት ወቅት ግን በነገር ወግተው ያቆሰሉንን፣ በችግራችን በጭንቀታችን የሳቁብንንና የተሳለቁብንን ወያኔዎች የሚዳስስ ነበር በተለይ ያዛሬው ዝግጅቴ መሽከርከሪያ። እስኪ አብረን እንዝለቅ፦

የዕለቱ ውይይት ተረኛ የወያኔ ቡድን መሪ ገነት ዘውዴ ነበረች። ለወትሮው ሴትዮዋ ከባላባቱ ወገን ሆና የባላባቱን ስርአት አምርራ የተዋጋች፣ በአብዮቱ ጊዜ ሀገራችን ዴሞክራሲያዊ እንድትሆን ካቅሟና ከእድሜዋ በላይ የታገለች ወዘተ ወዘተ እየተባለ የሚደረደርላት ገነት ዘውዴ ዛሬ ግን መስመር ሳተች። ውይይቱ እንዳሰበችውና እንደፈለገችው ያልሄደላት ወ/ሮ ”አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” እንደሚባለው ያገኘችውን አጋጣሚ በመጠቀም ጥቃት ሰነዘረች። አወ ማሕበራዊ እሴቶቻችንን፣ ሀገር የሚያውቃቸው ነባራዊ እውነታዎችን እና ካንድ የተማረ ዜጋ የሚጠበቅ ሃላፊነትን ዘንግታ አቆሰለችን። በችግራችን በስቃያችን ተሳለቀችብን። ሳይማር ያሰተማራትን ሕብረተሰብ ለማሳወቅ ለማሳደግ በመጣር በመሞከር ፋንታ ዘመን የማይሽረው መቼም መች ቢሆን የማንረሳው ሹፈት አሾፈች። ለዚያውም ከሀገራችን ሕዝብ 85 በመቶ በላይ በሚገመተውና የሕዝብ ዋልታና ማገር  ከለላና መከታ በሆነው አርሶ አድረ ገበሬ ላይ። እንዲህ ነበር ታሪኩ፦

”አቤት አስተማሪ ያለበት አባዜ አስተዋይ ተማሪ በጠየቀው ጊዜ” አይደል የሚባለው። አወ እናም ውይይቱ ቀጥሏል። ድንገት ግን አንዱ ጥያቄ አነሳ ”ለወትሮው ሀገራችንን በምግብ እህል አቅርቦት ቀጥ አድርገው ከያዙት ትርፍ አምራች አርሶ አደሮች አካባቢ አንዱና ዋነኛው የሆነው የጎጃም ገበሬ ተቸግሯል ተርቧል” አለና ላፍታ ቀጥ አለ። ቀጠለናም ”ችግሩን ሰቆቃውን ርሃቡን ፀሐይ ሞቀው አገር አወቀው፤ ይባስ ብሎ ጸጉሩ ከመቆሙና ከመገርጣቱም በላይ በተለይ ቁመናውን ሲያስተውሉት እግሮቹ የእጅ ያህል ከስተዋል ቀጥነዋል። ለዚህ እንደ ወያኔ ምን መፍትሄ አላችሁ?” የሚል ነበር ጥያቄው። እንደ ነሐሴ ነጎድጓዳማ መብረቅ ልብ ቀጥ በሚያደርግ የደስታ የሲቃ የድጋፍ ጭብጨባ፣ ጩኸትና ፉጨት አዳራሹ የተፈረካከሰ  እስኪመስል ድረስ ኖጋ። መቀመጫ ወንበሮች በስሜት በያቅጣጫው ተንሸራተቱ። ሁሉም ከወጥመድ ለማምለጥ ጊዜ እንደሚጠብቅ የዱር እንስሳ ላመል ከመቁነጥነጥ በቀር በስሜት ተውጦ ትንፋሹን ውጦ ጸጥ እረጭ ብሏል። (ወያኔ ውይይቱን ለመመልከት የመጣው ሕዝብ ጭብጨባ ያቁምልኝ ብሎ በማለቃቀሱ ጭብጨባ ቀረ። እንዴውም በሗላ ላይ ጭራሽ ወደ ውይይት አዳራሽ ተመልካች እንዳይገባ ተከለከለ እንጂ በእያንዳንዱ የውይይት መድረክ የነበረው የጭብጨባ አጀብ ልዩ ነበር) ወ/ሮዋ ግን  ከወደ ግራ ግንባሯ አካባቢ ወደ መሃል አናቷ ላመል ተከፍሎ ከወደ ቀኝ ግንባሯ በኩል ደግሞ የክፉ በግ ቀንድ መስሎ ጠቅለል ያለውን ሙሉ በሙሉ አፍሮ ያልሆነ ገብስማ ጸጉሯን ብእር በያዘ ቀኝ እጇ ደጋግማ እየደነቆለች ከምጸት ፈገግታ ጋር አኗን ከማቁለጭለጭ በቀር ለጊዜው መልስ ይለችው ነገር አላገኘችም ነበር። ቀጠለችና ግን ተበረታታ የሞትሞቷን ትለው ገባች።

”እንዴት መሰለህ” በማለት ጀመረች ገነት ”እንዴት መሰለህ አንተም እንዳልከው የጎጃም ገበሬ ትርፍ አምራች ነው። ወተት ቅቤው ከጓዳው ማርና እሸቱ ከጓሮው ነው። ችግር የለበትም። የተመኘውን የምግብ አይነት በፈለገው ሰአትና መጠን ማግኘት ይችላል። የፈለገውን ምግብ በፈለገው ሰአት ማግኘት መቻሉ ደግሞ አመጋገቡን እንዲያመጣጥንና እንዲያስተካክል እረድቶታል። ስለሆነም ባሁኑ ሰአት በጎጃም ገበሬ ላይ የሚታየው ተክለ ሰውነት ከመራብ ወይም ከመቸገር የመጣ ሳይሆን ከተስተካከለና ከተመጣጠነ አመጋገብ የተገኘ ግሩም አቋም ነው። ፈረንጆች እንዲህ አይነቱን የሰውነት ቅርጽ ስሊም ኔቸር ይሉታል (slim nature)። ስለዚህ በእኛ በኩል ይህንኑ አኗኗሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል እንጅ ሌላ የምንለው የለንም” በማለት የተንጠለጠለ መነጽሯን ወደ ሗላ ገፍታ ጨረሰች። አወ እንዲህ አርጎም ሹፈት የለም። እንዲህም አርጎ ማቁሰል አልታየም። የጎጃም ገበሬ የእግር ንቃቃት ሳንቲም የማስገባት ያህል ተበርግዶ ባለበት ወቅት፣ ቁርስ የሚባል በልቶ ምሳ ወይም እራት በሚዘለልበት በዚያ ሰአት፣ ከነ ልጆቹ ምድጃ ስር ተኮልኩሎ ላመል የሚሻማው ቆሎ ባጣበት በዚያ ጊዜ ካንድ ሕዝብን እወክላለሁ ብሎ ለውድድር ከቀረበ ግለሰብና ፓርቲ እንዲህ ያለ ምንጊዜም የማይረሳ አንጀት ቆራጭ ንግግር ሲነገር ያሰረጸው የስቃይ ስሜት፣ የፈጠረው የበቀል አምሮት እንዴት ይረሳል እንዴትስ ይለመዳል።

እንሆ ከሰባት ዓመት በሗላ እንኳ ረመጡ እየጨሰ፣ ጥቃቱ ዘልቆ እየተሰማ፣ መናቅ መዋረዱ ውስጥን እየቆጠቆጠ፣ ከሁሉም በላይ ይህን እና ከዚህም በላይ ግድያና ጭፍጨፋ የፈጸሙ አረመኔዎችን ማንም ሳይጠይቃቸው አሁንም አለቃና ገዳይ እንደሆኑ መቀጠላቸው ያነገበግባል ያቃጥላል። ከዚህም ሲከፋ ደግሞ ወገኖቻችንን ያዋረዱት ሁሉም ከህሊናና ከህግ በላይ ሆነው የጃቸውን ሳያገኙ እስካሁን በነፃነት ሲንቀሳቀሱ ሲታይ አቅምህን እንድትፈተሽ ጡንቻህን እንድትዳስስ ያስገድድሃል።

እናም ያን ሁሉ ጉድ የፈጸሙት ወያኔና ወያኔዎች የጃቸውን እስካላገኙና እኛም ትክክል ነው ብለን ባሰብነው መንገድ ለቁስላችን መድሃኒት እስካልሰጠነው ድረስ የደረሰብን የበደል ስሜት አይረሳም። የመናቅና የመዋረድ ህመም ያመረቅዛል እንጅ አይጠፋምና። ለዚህ ደግሞ አንድነት ሃይል ነው ብለን በመተባበርና ጠንክረን በመነሳት ወያኔን መደምሰስ ይጠበቅብናል። ወያኔዎችን ደግሞ ለፍርድ እንዲቀርቡ በማድረግ፣ በማስተማርና በማሰልጠን ለይቅርታ ዝግጁ ሆነው አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ማድረግ ስንችል የደረሰብንን በደል ባንረሳ እንኳ የበቀል ስሜቱ ይከስማል። የጎሪጥ መተያየቱ ይጠፋል። ቀስ በቀስም አንድነታችን እየጎለበተ፣ መለያየታችን እየጠበበ፣ እነሱና እኛ መባባሉም ለመል እየሆነ ይሄዳል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ጊዜው አሁን ነው። አበቃሁ።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on December 13, 2012 in AMHARIC, ARTICLE, POLITICS

 

Tags: , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: