RSS

ትዝብት – ውሃ ቅዳ ውሃ መለስ ወያኔና ሰሞንኛ እንቅስቃሴው

07 Dec

ከይኸነው አንተሁነኝ

08/ 12/ 2012

1. ውሃ ቅዳ ውሃ መለስ ወያኔና ሰሞንኛ እንቅስቃሴው

በወያኔ ውስጥ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው ብሎ ነበር አሉ ባለ ራዕዩ የወያኔው መሪ። ባለስልጣኖች በስልጣናቸው ቢባልጉ በወያኔ መንደር በታወቀው የግምገማ ጁዶ አማካኝነት እንዘርራቸዋለን ለማለት ይመስላል የባለራዕዩ ጎጠኛው መለስ ንግግር። የሚደንቀውና ይህን ጉዳይ አሳሳቢ የሚያደርገው ግን ልክ አሁን በወያኔ መንድር እንደሚታየው ባለጌው ከጨዋው አጅግ በዝቶ በሚታይበት ጊዜ ምን ይደረጋል የሚለው ነው። ሙሰኛው ከሀቀኛው፣ ልግመኛው ከሰራተኛው፣ አስመሳዩ ከደህነኛው በተለይም መሪው ከተመሪው በዝቶ እጅግም ገዝፎ በሚታይበት ጊዜ እራስን ፈጽሞ ከመለወጥ የተሻለ አዋጭ ዘዴ በወያኔ መንደር ምን ይሆን? ለዚህም ቢሆን ግን ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ የሆነው ወያኔ መላ ያጣ አይመስልም፤ የወያኔ የግምገማ ወንፊት ለወያኔዎች ተቃርኖ የሌላት (woyane friendly) ናትና። ድሮም ቢሆን በወያኔ ውስጥ ግምገማ ምልክት ማሳያ አቅጣጫ ጠቋሚና መስመር ሰጭ እንጅ ቀጭ አልነበረችም ሆናም አታውቅም የወያኔ ተፈጥሮ ለዚህ የተመቻቸ ስላልሆነ። ምንም እንኳ ሌባ ብንሆን፣ ምንም ያክል ሕዝብን ብንበድል፣ ያሻንን ያክል የሀገር ሃብት ብናወድም፣ በሕዝብ ሃብት ብንበለጽግ የወያኔን አለቃነት እስካወቅን ድረስና ወያኔ እንደ ዓይኑ ብሌን በሚጠነቀቅላት ስልጣኑ እስካልመጣንበት ድረስ የወያኔ ግምገማ ጓደኛችን ነች። በስልጣን ላይ ስልጣን፣ በሃብት ላይ ሃብት በአምባገነንነት ላይ አጉራ ዘለልነትን እየጨመርን እንሄዳለን እንጅ በወያኔ ግምገማ ምክንያት የዛፍ ላይ እንቅልፍ ብሎ ነገር የለም። ታዲያ ይሄ ለወያኔዎች እንጅ ለእውነተኛ ኢትዮጵያዊያን አይሰራም።

አነሳሴ እንኳ ስለ ወያኔ ግምገማ መተረክ አልነበረም ለዚያማ እነሱ ምን የዘው፤ ይልቅስ ከግምገማ ጋር የተያያዘ ስለሚመስልና ሰሞኑን በወያኔ መንደር ስለተፈጸመ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የሆነ ድራማ አንዳንድ ለማለት እንጅ። ጉዳዩ እንዲህ ነው፦

ጄ/ል መሓመድ ሲነሳ ጄ/ል ሞላ ተመለሰ አሉ ጋዜጠኛ አርአያ እንዳለው። ሲጀመርስ ጄ/ል ሞላ ለምን ተነሳ ብሎ መጠየቅ መችም ችግር ያለው አይመስለኝም። እውነት ግን ለምን ተነሳ? ለነገሩ ላንድ የስራ ቦታ ወያኔያዊ ትስስር እንጅ አግባብነት ያለው የትምህርት ደረጃና በቂ የሆነ ተዛማጅ የስራ ልምድ ለማይጠይቀው ወያኔ እንዲህ ያለው ጥያቄ ምናልባት የሌሊት ቅዠት ለሆን ይችላል። ከዚያ ይልቅ የሚያስደንቀው ትላንትና ተነሳ የተባለው ዛሬ ተመለሰ መባሉ ነው። ምክንያቱም እንደ ወያኔ ላለው ከ 38 ዓመት በላይ ድርጅታዊ አሰራር ልምድ አለኝ ለሚል ድርጅት አንድን ጄኔራል ትላንትና አንስቶ ዛሬ ይመልሳል ብሎ ለማመን ስለከበደኝ ነው። አሃሃሃ ይቅርታ ለካ ያች ጉደኛ ግምገማ የሚሏትና ሚስጥር ተጋሪ ቁርጠኛ የልብ ጋደኛ ማስመቻ ግለ ሂስ የምትባል ቀልድ አለችና ለካ። ሁሉም ቅድም እንዳልኩት ነው፤ የወያኔ ግምገማ ለወገኖቿ (ለወያኔዎች) ብርቱ አይደለችም። ታስደነግጣለች፣ ምልክት ታሳያለች አቅጣጫ ትጠቁምና መልሳ አስተማምና ወደ ቀድሞ ቦታ ወይም ለተሻለ አለቅነት ታበቃለች። ይኸው ነው በቃ።

በዚሁ አጋጣሚ በነካ እጄ ግን፤ የሰሞኑ የወያኔ ዓይን ያዥ  እንቅስቃሴ ምን የሚያሳይ ይመስላችሗል? መችም በውቅያኖስ ውስጥ አንዳች ነገር ሳይፈጠር ሱናሚ አይነሳም። ይህ የሰሞኑ የተሳከረ የወያኔ እጀብ እጀብም ባካባቢያቸው አንዳች ነገር እንዳለ ጠቋሚ ነው። ባላጋራ ሲገፋ ወዳጅ ይጎትታል አይደል የሚባለው። በወያኔ በራሱ ውስጥም እንኳ ቢሆን እንዲህ ያለው መሳሳብ የተለመደ ነው ምክንያቱም ጥበትና ጎጠኝነት ደንበር የላቸውምና ነው። በነዚህ ጄኔራሎች ሹም ሽርም ያየነው ዋና ጉዳይ ይህንኑ ነው፤ በጄኔራል ሞላና በጄኔራል መሓመድ ቡድኖች መካከል ያለው ለመሳሳብ የሚደረግ ፍጥጫና ፍትጊያ። በዚህ የተነሳም በወያኔ ውስጥ ከላይ እስከ ታች ድረስ እየተዛመተ ያለው አለመተማመንና መቧደን እያየለ መምጣቱ፤ መጨረሻው አጓጓኝ። በራሳችን አቅምና ልምድ ብቻ የምንቀሳቀስባት ኢትዮጵያ ናፈቀችኝ። እስኪ ወደ ቀጣዩ ትዝብቴ ደግሞ ልለፍ፦

2. የከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት የዩናይትድ ስቴትስ ጉብኝት

ወታደር ይነግዳል እንዴ ወገን? ኢይይይይ የኔ ነገር እረሳሁት ማለት ነው አሳምሮ ይነግድ። እንዴ ስንቶቹ ናቸው ከተቀደደ የሗላ ኪስ ባንድ ጊዜ ባለ 5 እና 6 ወለል ፎቅ ባለቤት ሆነው የኪራይ ንግድ እያጧጧፉ የሚገኙት። ስንቶቹ ናቸው በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ከተሞች ብዛት ያለው የቦታ ካርታ እየወሰዱ እሱን በመቸብቸብ ባለ ሚሊዮን ጄኔራሎች የሆኑት። የሙገር ሲምንቶን አይር ባየር በማሻሻጥ ስንቶቹ ወታደሮች ባንዲት ጀምበር ባለሚሊዮን እንደሆኑና ሙገር ሲምኒቶ ፋብሪካን ድራሹን እንዳጠፉት ከእኛ ወዲያ ማን ምስክር አለ። ስኳር ፋብሪካዎቻችንም ቢሆኑ እንዲህ አይነቱን የወታደሮች አላግባብ ሃብት ማካበት ከማገዝ የጸዱ አይደሉም። እርግጥ ነው ወታደሮቻችንማ አሳምረው ይነግዳሉ፣ ታክስ የማይከፍሉ ከመሆናቸውና በሕዝብ ሃብት በነጻ ከመጠቀማቸው አንጻር ሰታዩ ደግሞ ይዘርፋሉሉሉሉ ቢባል ይቀላል። ከዚህ ይልቅ እኔን በጣም የደነቀኝ ወታደሮች ከመዋዕለ ንዋይ ፍሰት (ኢንቨስትመንት) ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ስራ ሊሰሩ ነው  ዋሽንግተን የገቡት መባሉ ነው።

እንዴ ጎበዝ ወታደርነት እኮ ሳይንስ ነው። ውጤታማ የሚያደርግ የራሱ የሆነ የተቀላጠፈና ቀላል ወጭ ወይም መስዋትነት የሚጠይቅ መንገድ ያለው ኩነት። እና ከእንዲህ ያለው ሳይንስ አውጥቶ ወታደሮችን ወደ ኢንቨስትመንት ምን ዶላቸው? እንዴው ነገርን ነገር ያነሳዋል ነውና ከዚህ በፊት የተዘገበ አንድ ዜና ትዝ አለኝ። ወታደራዊ ሳይንስንና የወያኔን ወታደር ግንኙነት የሚቃኝ ነው ነገርየው። ጉዳዩ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የተፈጸመ ነው። በጊዜው የነበረውንና ፍጹም ወታደራዊ ሳይንስ ያልነካካውን የኢትዮጵያና የኤርትራ እልህ የተሞላበት ጦርነት አንድ የውጭ ጋዜጠኛ የታዘበውና የዘገበው ባ16ኛው ክፍለ ዘመን ከተደረጉት ጦርነቶች እንዳንዱ አድርጎ ነበር። ልክ በቡድን እንደሚፋጁት የዱር እንሰሳት። ከዚህ አንጻር ሲመዘኑ ደግሞ የወያኔ ወታደሮች በማያውቁት የኢንቨስትመንት መስክ ይቅርና አለንበት በሚሉት ወታደራዊ ክፍልም ቢሆን በስም እንጅ በተግባር እንደጫካዎቹ አውሬዎች መሆናቸው ማየሉ ነው ክፋቱ።

የሆነስ ሆነና ማን ወይስ እነማን ናቸው ጉዳዩን የፈጸሙት አትሉም? ነገሩ ወዲህ ነው፤ የመከላከያ ሚንስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ እና ጄኔራል ሳሞራ የኑስ፤ ውይይይ ይህ ጄኔራል ምነው ስሙ በያቅጣጫው በረከተሳ አባዝተው በተኑት እንዴ? ወታደራዊ ክህሎት እንዳላቸው አይታወቅም እንጅ ቢኖራቸው እንኳ ያ ክህሎት ለወታደራዊ ሳይንስ ብቻ ነው። በማህበራዊ ሳይንስ፣ ባስተዳደርና ፋይናንስ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ወይም በሌላ መስክ ክህሎት ሊሆን አይችልም።

በእርግጥ በወያኔ አሰራር ሁሉም ቀመር የለውም ምክንያቱም ወያኔዎች ሁሉንም መሆን ይችላሉና። ጄኔራሉ ጄኔራልነቱን ጥሎ የሕዝብ አስተዳደር ላይ ሊመደብ ይችላል ወይም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሃላፊ ሊሆን ይችላል ካልሆነም የቴሌኮሚኒኬሽን፣ የውሃና ፍሳሽ አልያም እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለውን አትራፊ ድርጅት ሊገድል ይችላል። እጅግ ሲከፋ ደግሞ እንደ ዓይነ ስውር መሪ ከሗላ ሆኖ ዩኒቨርሲቲዎችን ሊያስተዳድር ይችላል። የሰሞኑ የጄኔራሎች የአሜሪካ ጉብኝትም እንግዲህ ወታደሩ ሁሉን ማድረግ እንደማይሳነውና እያደረገም እንደሆነ ለማሳየት የተደረገ አይመስላችሁም?

ከዚህ በመነሳት፤ ያየነውና የሰማነው እንዲህ አይነት ጉዳይ የሚያስጨንቀንና ጥያቄ የሚሆንብን፤ ከእንዲህ አይነት ስርአትና አሰራር ሊገኝ የሚችለው ትርፍ ምን ሊሆን እንደሚችል ስናስብ ነው። ላለፉት 21 ዓመታት ከሀገራችን ዓመታዊ ገቢ በተጨማሪ ወያኔ በቢሊዮን የሚቆጠር እርዳታ ዶላር ቢያገኝም የሚበዛው ከጥቂቶች መጠቀሚያነት አላለፈም። ሕዝባችን ግን ዛሬም ድረስ የርሃብ ምሳሌ እንደሆነ አለ። ከርሃብና ስደት ከድህነትና ጉስቁልና በቀር ባለፉት የወያኔ አገዛዝ ዘመኖች ሌላ እድገት አልታየም። ድሮስ ወታደር በሚያስተዳድርበት ሀገር ከዚህ ሌላ ምን ሊጠበቅ ይችላል። ሀገራችንንም ሆነ ሕዝባችንን ከእንዲህ ያለው ውርደት ለመታደግ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሕዝባዊ አስተዳደር ለመተካት የሁላችንም ትብብር ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ ቀጠሮ አያስፈልገውም። አበቃሁ።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on December 7, 2012 in AMHARIC, ARTICLE, POLITICS

 

Tags: , , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: