RSS

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለሁለተኛ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ

07 Nov

ኢሳት ዜና:-”ይህች አገር ከማናቸውም የዓለማችን አገሮች በላይ ንብረት አላት። እኛን ሀብታም ያደረገን ግን ያ አይደለም። በታሪክ በጣም  ግዙፍ የሆነ ወታደራዊ ሀይል አለን።ጠንካሮች ያደረገን ግን ያ አይደለም።ዩኒቨርሲቲያችን፣ባህላችን ሁሉ  በዓለማችን ምርጦች የሚባሉ ናቸው።ዓለምን ወደኛ ዳርቻ ያመጡት ግን እነሱ አይደሉም። አሜሪካን  የተለየ ያደረጋት ፤ የምድራችንን የተለያዩ ህዝቦች፤ በህብረት ያስተሳሰረችበት  ሰንሰለት ነው” ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡት 44ኛው  የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ።
ላለፉት በርካታ ወራት  የዓለምን ትኩረት ይዞ የሰነበተው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ  ትናንት ሌሊት በፕሬዚዳንት ኦባማ  አሸናፊነት እልባት አግኝቷል።

የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወድድሩን ለማሸነፍ ከተፎካካሪዎቹ አንድኛቸው ፤ ኢሌክቶራል ኮሌጅ ከሚባሉትና  ከእያንዳንዱ የአሜሪካ ስቴት ከሚሰበሰቡት  ቁልፍ ድምፆች 270 ድምጽ ማሸነፍ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት የሆኑት ባራክ ኦባማ 303 ድምፆችን በማግኘት የዋይት ሀውስ ትኬታቸውን ለተጨማሪ አራት ዓመታት አራዝመዋል።

እስካሁን ያልታወቀውን የፍሎሪዳ 29  ኢሌክቶራል ኮሌጅ ድምጽ ውጤት ሳያካትት ፤ኦባማ 303፤ ተፎካካሪያቸው ሚት ሩሚኒ ደግሞ 206 ድምፆችን ነው ያገኙት።

አሸናፊ ለመሆን የሚያስፈልገው 270  ድምጽ ከመሆኑ አንፃር የዘገየውን የፍሎሪዳ ውጤት ሚስተር ሩሚኒ ሙሉ በሙሉ እንኳ ቢያሸንፉ፤ በአጠቃላይ ውጤቱ ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም።

የ 51 ዓመቱ ጎልማሳ  ባራክ ኦባማ ከድል በሁዋላ በቺካጎ አደባባይ ወደሚጠብቋቸው  ደጋፊዎቻቸው ደረሱ። በኢሊኖይ አደባባይ  ሲጠባበቋቸው የነበሩት በሺዎች የሚቈጠሩ ደጋፊዎቻቸው፦<< አራት ተጨማሪ ዓመታት>>(ወይም በ እንግሊዝኛው አባባል ፎር ሞር ይርስ) በሚል የደስታ ጩኸት ተቀበሏቸው።

ፕሬዚዳንቱም  ምስጋናቸውን በመግለጽ ንግግራቸውን ቀጠሉ፦<<በዚህ ምሽት፣በዚህ ምርጫ እናንተ ፤ የአሜሪካ ህዝቦች ፤ መንገዳችን  ከባድና ጉዘችን ረዥም መሆኑን አስታውሳችሁናል።አሜሪካውያን  ራሳችንን  አንስተናል፤ባለፈው ጉዟችን ብዙ ታግለናል።  ይሁንና ለአሜሪካ  የተሻለው ጊዜ፤ ከፊታችን የሚመጣው እንደሆነ ልባችን ያውቀዋል>>  በማለት። የደጋፊዎቻቸው ጭብጨባም አስተጋባ።

ባራክ ኦባማ ከድላቸው በሁዋላ በቺካጎ-ኢሊኖይ  ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት  በዚሁ ታሪካዊ ንግግር  አሜሪካን ይበልጥ ወደፊት በማሳደግ ረገድ ከተቀናቃኛቸው ከሚስተር ሩሚኒ ጋር ተመካክረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

እንዲሁም በምርጫ ዘመቻው ላሳዩት ጠንካራ ፉክክር  ቀንደኛ ተቀናቃኛቸውን ሚስተር ሩሚኒን እና የሪፐብሊካኑን ዕጩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ፓውል ሪያንን ከልብ አመስግነዋል።

ምርጫውን እንዲያሸንፉ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል ላሏቸው ለምክትላቸው ጆን ባይደንና ለባለቤታቸው ሚሸል ኦባማም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ባራክ፤በሁለተኛው ምርጫ አሸንፈው ወደ ዋይት ሀውስ ማምራታቸው ፤  ለአሜሪካና ለአሜሪካውያን ከዚህ በፊት ሲያደርጉት ከነበረው በይበልጥ ተግተውና ጠንክረው እንዲሠሩ ልዩ መነሣሳትን  ብርታትን እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።

ከፓርቲያቸው ጋር ብቻ ሳይሆን ከሪፐብሊካኑ ጋር ጭምር አንድ ላይ እንደሚሠሩ የተኛገሩት ፕሬዚዳንት ኦባማ፦<<ሁላችንም አሜሪካውያን ቤተሰቦች ነን።እንደ አንድ ህዝብ የምንወድቀውም፤የምንነሳውም አንድ ላይ ነው>> ብለዋል።

ሪፐብሊካኑ ተወዳዳሪ ሚስተር ሩሚኒ በበኩላቸው በቦስተን ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ለፕሬዚዳንት ኦባማ  የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል። ከምክትላቸው ከፓውል ሪያን ጋር ምርጫውን ለማሸነፍ የሚችሉትን ሁሉ ማድረጋቸውንም ሩሚኒ ጠቅሰዋል።

<<ከእንግዲህ  በፖለቲካ ምክንያት የምንጨቃጨቅበት ጊዜ አይደለም። ሪፐብሊካንም ሆንን ዲሞክራቶች፤ ከፖለቲካ  ጥቅም በፊት ህዝቡን ማስቀደም አለብን>> ብለዋል-ሚት ሩሚኒ።

ደጋፊዎቻቸው ላሳዩት ጥንካሬና ለሰጧቸው ድጋፍም  ጥልቅ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሪፐብሊካኑ ጆርጅ ቡሽ ድምፃቸውን ለባራክ ኦባማ መስጠታቸው የምርጫው አስገራሚ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።

ከፍተኛ ፉክክር በታየበት በዘንድሮው  ምርጫ፤44ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ 2 ጊዜ በመመረጥም፤ የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት ሆነዋል።

የምርጫውን ሂደት የተከታተሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ገፆቻቸው በሰጧቸው አስተያየቶች፦<<እኛስ መቼ ይሆን ለነፃና ፍትሀዊ ምርጫ የምንበቃው?>> በማለት በአሜሪካውያን መቅናታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ኦባማ -ሩሚኒን ያሸነፉበት አጠቃላይ ውጤት በመቶኛ 51 ለ 49 መሆኑን ፤ 99 ነጥብ 6 -በ 0 ነጥብ 4 በመቶ   ልዩነት ከተጠናቀቀው የ2000ው የ ኢትዮጵያ ምርጫ ጋር ያነፃፀሩ  በርካታ የፌስ ቡክና የትዊተር ተጠቃሚዎች፤ <<ኢትዮጵያውያን  የአሜሪካ ዓይነት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ልናይ የምንችለው ፤ዲቪ ደርሶን አሜሪካ ስንሄድ ብቻ ነው>> ሲሉ ተሳልቀዋል።

ሌላው ኢትዮጵያውያኑ ቀናንበት ያሉት የአሜሪካ ምርጫ ክስተት፤  ተፎካካሪዎቹ ከተሸናነፉ በሁዋላ አንድ ላይ ለመስራት  ያሳዩትን ፍላጎት ነው።

አበበ ከበደ የተባለ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ በገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ ፦<<በአሜሪካ በምርጫ ማግስት ተፎካካሪዎች ፦ ድምጽ እናከብራለን፤ተባብረን እንሠራለን፣ በጋራ ለአገራችን እንተጋለን ሲሉ ፤በኢትዮጵያ በምርጫ ማግስት፦ የድምጽ መጭበርበር አቤቱታዎች ይበረክታሉ፣ተፎካካሪዎችም  ወደ እስር ቤት ይጋዛሉ>> ብሏል።

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on November 7, 2012 in AMHARIC, NEWS

 

Tags: , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: