RSS

በወያኔ መዳፍ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ በገለልተኛ ተቋማት ሚዛን

29 Oct

October 26, 2012 | G7 Editorial 

ዘረኛውና አምባገነኑ ወያኔ ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች በመመንጠቅ ላይ ያለች ለማስመሰል ይጥራል። ይባስ ብሎም በሌሎች አገራት እድገት የሌለ በማስመሰል ስለ መለስ ዜናዊ “ተዓምራዊ” አመራር ይደሰኩራል። በፍትህ፣ በዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ረገድም የሚደርስብኝ የለም እያለ ይፎክራል።

“ይሉሽን በሰማሽ …” ለማለት ያህል ገለልተኛ የምርምር ተቋማት ስለኢትዮጵያ ካሉት ጥቂቶችን ለአብነት እናቅርብ።

1.     በአፍሪቃ የመልካም አስተዳደር መለኪያ /Mo Ibrahim Governance Index/

“ሞይ ኢብራሂም ፋውዴሽን” በአፍሪቃ ውስጥ መልካም አስተዳደርን ለማበረታታት የተቋቋመ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ነው። ከፋውንዴሽኑ ፕሮግራሞች አንዱ አገራቸውን በመልካም ሁኔታ አስተዳድረው የሥልጣን ሽግግር ላደረጉ የአፍሪቃ መሪዎች 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በመሸለም መልካም አስተዳደርን ማበረታት ነው። ይህ ፋዉንዴሽን ሥራውን ከጀመረ ስድስት ዓመታት ቢሞሉትም እስካሁን ለመሸለም የታደለው ግን ሶስት የአፍሪቃ መሪዎችን ብቻ ነው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2007 የሞዛቢኩን ፕሬዚዳንት ጃኩም አልቤርቶ ቺሳኖ፣ በ2008 የቦትስዋናውን ፕሬዚዳንት ፌስተስ ጎንተባንዬ ሞጋዬ እና አምና በ 2011 የኬፕ ቨርዴውን ፕሬዚዳንት ፔድሮ ቬሮና ፓይረስ ይህን ታላቅ ሽልማት አግኝተዋል። ወያኔ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና አፍቃሪ ወያኔዎች “ታላቁ የአፍሪቃ መሪ” እያሉ የሚያሞካሹት ሰው መለስ ዜናዊ በዝርዝሩ ውስጥ ገብቶ እንደማያውቅ  ልብ ይበሉ።

ፋውንዴሽኑ በየአመቱ የአፍሪቃ አገሮች በመልካም አስተዳደር ረገድ የደረሱበትን በመለካት “የሞይ ኢብራኢም የመልካም አስተዳደር ኢንዴክስ” የሚባል ደረጃ ያወጣላቸዋል። ይህ መለኪያ የሚከተሉት  ዋና ዋና መመዘኛዎች አሉት፡ –

ሀ) ደህንነት እና የህግ የበላይነት፣

ለ) የሕዝብ ተሳትፎ እና የሰብዓዊ መብቶች መከበር፣

ሐ) ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ እና

መ) ሰብዓዊ እድገት ናቸው።

አምሳ ሁለት የአፍሪቃ አገሮች በአለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ያስመዘገቡት ውጤት ከላይ በተዘረዘሩት አራት መመዘኛዎች መሠረት ተገምግመው  ያገኙት ደረጃ ሰሞኑን ይፋ ሆኗል። የመለስ ዜናዊዋ ኢትዮጵያ ከ52 አገሮች በአጠቃላይ ውጤት 46.7 ከመቶ በማግኘት 33ኛ ወጥታለች። በተለይም በፀጥታና በህግ የበላይነት እጅግ አሽቆልቁላ 38ኛ ደረጃ ላይ ወድቃለች። ከሁሉም የባሰው ደግሞ በሕዝብ ተሳትፎ እና ሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ነው – በእነዚህ ኢትዮጵያ 39ኛ ሆና ከአፍሪቃም በመጨረሻዎቹ ተርታ ትገኛለች።

የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ይህችን ታላቅ አገርና ይህን ታላቅ ሕዝብ ከሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ጋር ሲወዳደር ለእንዲህ ዓይነት ዝቅተኛ ውጤት እንደዳረጋት ልብ ይሏል።

2.    ዘርፈ-ብዙ የድህነት መለኪያ (Multidimensional Poverty Index)

ዘርፈ-ብዙ የድህነት መለኪያ፣ በቤተሰብ ደረጃ ያለ የድህነት መጠንን በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚለካበት መመዘኛ ነው።  ምግብ፣ መጠለያ፣ የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ የማገዶ አቅርቦት፣ ህክምናና ትምህርት የመሳሰሉት ሁሉ በዚህ መመዘኛ የተካተቱ በመሆናቸው ድህነትን ለመለካት ከሌሎች መመዘኛዎች የተሻለ ነው ተብሎ  ይታመናል።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሃግብር (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) ዘንድሮ ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት መሠረት 89 ከመቶው የኢትዮጵያ ቤተሰብ ድሃ ተብሎ የሚፈረጅ ነው። ቢሊየነር እና ሚሊየነር የሆኑ ወያኔዎችና አጫፋሪዎች መኖራቸው እውነት ቢሆንም የ89 በመቶው ሕዝቧ የቀን ገቢ ግን ከአንድ ዶላር ከሃያ አምስት ሣንቲም በታች ነው። ይህ ውጤት ኢትዮጵያን የዓለም ሁለተኛዋ ድሃ ያደርጋታል።

በዩ.ኤን.ዲ.ፒ መረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ ማንበብና መፃፍ የሚችለው ሕዝብ 28 በመቶ ብቻ ነው።  ይህ ውጤት ኢትዮጵያ አገራችንን በትምህርት ስርጭት ከዓለም ከመጨረሻ ሁለተኛ ያደርጋታል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ወያኔ ትምህርትንና የጤና አገልግሎትን በማዳረስ የሚበልጠኝ የለም እያለ በሚፎክርበት አገር ውስጥ ነው።

3.       የኢኮኖሚ ነፃነት መለኪያ /Index of Economic Freedom/

“ሄሪተጅ ፋውንዴሽን” በዓለም ላይ ያሉ አገሮችን ኢኮኖሚዎችን በጥልቀት በመመርመር የቱን ያህል ነፃ መሆናቸውን ይለካል። ይህ ጥናት በሥራ ላይ ከዋለ ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ የሆነው ሲሆን ኢኮኖሚዎች ምን ያህል ወደ ገበያ ኢኮኖሚነት እየቀረቡ አለያም ከዚያ እየራቁ  እንደሆነ  በመለካት ረገድ አቻ ያልተገኘለት እና ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ መመዘኛ ነው። ይህ መለኪያ የኢኮኖሚ ነፃነትን በአስር የኢኮኖሚ ነፃነት አይነቶች ከፋፍሎ ይገመግማል። እነዚህም ሀ) የቢዝነስ ነፃነት፣ ለ) የኢንቬስትመንት ነፃነት፣ ሐ) የንግድ ነፃነት፣ መ) የበጀት ነፃነት፣ ሠ) የፋይናንስ ነፃነት፣ ረ) የንብረት ነፃነት፣ ሰ) የመንግሥት ወጪ፣ ሸ) ከሙስና ነፃ መሆን፣ ቀ) የገንዘብ ነፃነት፣ እና በ) የሥራ ነፃነት ናቸው።

በያዝነው የአውሮፓውያን 2012፤ 179 አገሮች ደረጃ ወጥቶላቸዋል።  ከዓለም ከሁሉም የተሻለ ነፃ ኢኮኖሚ ያላት አገር ሆንግ ኮንክ ስትሆን ያገኘቺው አጠቃላይ ነጥብ 89.9 ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ 52.0 አጠቃላይ ነጥብ በማምጣት 134ኛ ደረጃ ይዛለች። ይህ አጠቃላይ ውጤት ኢትዮጵያን “ኢኮኖሚያቸው ባብዛኛው ነፃ ያልሆነ” ከሚባሉ አገሮች ጋር መድቧቷል። ይህ የሚያመለክተው ወያኔ በኢትዮጵያ የገነባው የኢኮኖሚ ሥርዓትን የገበያ ኢኮኖሚ ነው ብሎ መጥራት የማይቻል መሆኑ ነው። አሁንም ለንጽጽር እንዲረዳን በአፍሪካ ደረጃ እንኳ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ፣ ኬኒያ፣ ማሊ፣ ሴኔጋል፣ ማላዊ እና ኮትዲቯር በኢኮኖሚ ነፃነት ከኢትዮጵያ በተሻለ ደረጃ ላይ ከሚገኙ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ጥቂቶቹ ናቸው።

4.    የጨነገፉ መንግሥታት መለኪያ /Index of Failed States/

“ዘ ፈንድ ፎር ፒስ” መንግሥታት ሕዝባቸውን በመምራት ረገድ ያሉባቸውን ድክመቶች በአስር ዋና ዋና መመዘኛዎች ይለካል።

እነዚህም

ሀ) ፈጣን የሕዝብ ብዛት የሚፈጥረው ውጥረት፣

ለ) የሕዝብ ከመኖሪያ ቦታው መፈናቀል፣

ሐ) የቡድኖች (የማኅበረሰብ) በሥርዓቱ መማረር፣

መ) ስደት፣

ሠ) አድሏዊ የሆነ ልማት፣

ረ) የኢኮኖሚ ድቀት፣

ሰ) የመንግሥት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማጣት፣

ሸ)  የመንግሥት አገልግሎት አናሳነት፣

ቀ) የፀጥታ ኃይሎች ብቃት ማነስ፣

በ) የፓለቲካ ልሂቃን የእርስ በርስ መቆራቆስ፣ እና

ተ) የውጭ ጣልቃ ገብነት ናቸው።

ይህን ጥናት የሚያካሄደው የውጭ ፓሊሲና የሰላም ፈንድ የተባለ የምርምር ተቋም ሲሆን የምርምር ውጤቶቹ ከፍተኛ ዓለም ዓቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ናቸው።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የ2011፣ የ179 አገሮች ዓመታዊ ውጤት በቅርቡ ወጥቷል። ዘንድሮም በጨነገፉ መንግሥታት መለኪያ ዓለምን የምትመራው ጎረቤታችን ሶማሊያ ስትሆን ያገኘችው አጠቃላይ ነጥብ 114.9 ነው። ኢትዮጵያ በ97.9 በሆነ አጠቃላይ ነጥብ 17ኛ ደረጃ ይዛ በቅርብ እርቀት ትከተላታለች። ለማነፃፀር ያህል ዩጋንዳ፣ ስሪላንካ፣ ብሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ ሩዋንዳ እና ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተሻለ አስተማማኝ መንግሥታት ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል።  እስከ ሠላሳ ሶስተኛ ተራ ቁጥር የተዘረዘሩት መንግሥታት “በመውደቅ ላይ ያሉ መንግሥታት” የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። ይህ ስያሜ በእነዚህ አገራት ውስጥ መንግሥት አለ ለማለት አያስችልም የሚል መልዕክት አለው። ወያኔ ሰላምና መረጋጋት ፈጠርኩ ብሎ የሚመፃደቅባት ኢትዮጵያ በመውደቅ ላይ ካሉ መንግሥታት አንዷ እንደሆነች ተገልጿል። ትርጉሙም ኢትዮጵያ ውስጥ “መንግሥት” ለመባል የሚበቃ ተቋም የለም ማለት ነው።

ከላይ የተጠቀሱት ድርጅቶች የሚጠቀሙት የየአገሩ መንግሥታት የሚሰጧቸውን መረጃ ነው። ድርጅቶቹ እንዲህ ዓይነቱ መረጃ ላይ የደረሱት ባብዛኛው ራሱ ወያኔ በሚሰጣቸው መረጃዎች መነሻነት ነው።

ወያኔ መረጃዎችን እንደሚያዛባ ብዙ የተባለበት በመሆኑ እዚህ ላይ ማንሳት አያስፈልግም። የሚገርመው ግን እነዚያ የተዛቡ መረጃዎችን ይበልጥ አዛብቶ “የሚያነባቸው” መሆኑ ነው። ራሱ ወያኔ የሚያወጣቸውን መረጃዎች በጥንቃቄ ያነበበ ሰው የሚያስጨፍርና የሚያስፈነድቅ ነገር እንደሌለባቸው ይረዳል።

ወያኔ በቴሌቪዥንና ራድዮ ስለድልና ልማት ሲያደነቁረን በራሱ መረጃ መነሻነት የተሰሩትን የጥናት ውጤቶችን ይዘን “ይሉሽን በሰማሽ ..” እያልን አገራችን ውስጥ እውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት፤ ማኅበራዊ ፍትህና ዲሞክራሲ እንዲያብብ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን መታገል ይኖርብናል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on October 29, 2012 in AMHARIC, NEWS

 

Tags: , , ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: