RSS

አቶ ኃይለማርያም እና ኤርትራ

20 Oct

ግርማ ካሳ ግርማ ካሳ
(muziky68@yahoo.com
October 18, 2012

“Hailemariam Desalegn a perfect mimic of Meles” በሚል ርእስ ሥር በኢትዮሜዲያ የቀረበች
አጭር ትንተና አነበብኩ። የአቶ ኃይለማርያም ባለቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬን እንዲሁም ልጃቸው ዮሃናን
በተመለከተ በተጻፈው ላይ ትንሽ የግሌን አስተያየት እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ።
1
የአቶ ኃይለማርያም ባለቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ ኤርትራዊት እንደሆኑ ተገልጿል። አቶ መለስ እናታቸዉ
አዲ ቋላ የተወለዱ ኤርትራዊት በመሆናቸዉ «ለኤርትራ ያደላሉ» ይባሉ እንደነበረዉ፣ አቶ
ኃይለማርያምም ባለቤታቸው «ኤርትራዊት» በመሆናቸዉ ልባቸው ሻእቢያ ጋር ነዉ የሚል እድምታን
ለማሳየት የተሞከረ ይመስላል።
ወ/ሮ ሮማን ኤርትራዊት መሆናቸዉን ለማሳየት ፣ ለመጀመሪያ ሴት ልጃቸው የተሰጠዉ «ዮሃና»
የሚለዉ ስም እንደ ዋና መረጃነት ቀርቧል። «ዮሃና» የሚለው ስም «እንኳን ቀናህ፤ እንኳን ተሳካልህ»
(Congratulation) ማለት እንደሆነና የብዙ ኤርትራዉያን ስም መጠሪያ እንደሆነ በመግለጽ ነዉ የወ/ሮ
ሮማን «ኤርትራዊነት» የታወጀዉ።
ወ/ሮ ሮማን የተወለዱት ጋሼኖ በምትባል የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዉ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን
በዚችዉ በጋቼኖ ካጠናቀቁ በኋላ ከአምስት እስከ ስምንተኛ ክፍል በሊጋባ፣ ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ክፍል
ደግሞ በወላይታ ሶዶ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል። ወላይትኛ ፣ አማርኛ እና
እንግሊዘኛ ቋንቋዎች የሚናገሩ ሲሆን እናታቸዉም አባታቸውም ኤርትራዉያን ሳይሆኑ ኩሩ ወላይታዎች
ናቸዉ።
የመጀመሪያ ሴት ልጃቸው ዮሃና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ዉስጥ የሕክምና ትምህርት እየተከታተለች
ያለች ትሁት ኢትዮጵያዊት ናት። አባቷ፣ ምንም እንኳን የአገር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር ቢሆኑም፣ ዮሃና
በምታመልክበት ቤተክርስቲያን ከአምልኮ በኋላ፣ ሻሂ በማፍላት ከእህቶቿ ጋር ምእመናን የምታገለግል
ወጣት ናት።
ወላጆቿ ዮሃና የሚል ስም የሰጧት እንደ አብዛኞች የወንጌላዊት አብያተ ከርስቲያናት አማኞች፣ መጽሃፍ
ቅዱስ ውስጥ ያለ ስም በመሆኑ ነዉ። ዮሃና የሚል ስም ያላቸዉ ሁለት ሴት ልጆችን አውቃለሁ።
ሁለቱም ቤተሰቦቻቸዉ ኤርትራዉያን አይደሉም። ዮሃና እንደ አፈወርቂ፣ ትርሃስ፣ ዘይዳ፣ ብርክቲ ፣
የማነ፣ ካሳይ ,… የኤርትራዉያን ወይን የትግሪኛ ተናጋሪዎች ስም ሳይሆን የመጽሃፍ ቅዱስ ስም ነዉ።
በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 8 ቁጥር 3 «መግደላዊት የተባለችዉ ማርያም፣ የሄሮድስ ቤት ሃላፊ የነበረዉ
የኩዛ ሚስት ዮሃና፣ ሶስና ፣ ደግሞም ሌሎች ብዙዎች በግል ንብረታቸው የሚያገለግሉት ነበሩ» የሚል
እናነባለን። ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያገለግሉት ከነበሩ ሴቶች መካከል ዮሃን የምትባል
እንደነበረች በግልጽ የሚያሳይ ነዉ።

1
http://www.ethiomedia.com/assert/4747.htmlጌታችን መድሃኒታችን ከመቃብር እንደተነሳ መጀመሪያ ያዩት ሴቶች ነበሩ። እነዚህ ሴቶች ያዩትን
የትንሳዔዉን ኃይል ለሐዋርያት መሰከሩ። በሉቃስ ወንጌል 24፡ 10 «ይህን (ጌታ መነሳቱን) ለሐዋርያት
የነገሯቸዉም መግደላዊት ማርያም፣ ዮሃና፣ የያእቆብ እናት ማርያም፣ ከነርሱ ጋር የነበሩት ሌሎች ሴቶች
ነበሩ » የሚል ቃል ተጽፏል። የጌታን ትንሳዔ በመጀምሪያ ካወጁት ሴቶች መካከል በግልጽ ዩሃና
የምታባል ሴት እንደነበረች እናያለን።
ዮሃና የእብራይስጥ ቃል ነዉ። «የእግዚአብሄር ስጦታ» ወይም «የእግዚአብሄር ጸጋ” ማለት ነዉ።
መዝሙረ ዳዊት «ልጆች የእግዚአብሄር ስጦታ ናቸው» ይላል። ወ/ሮ ሮማን እና አቶ ኃይለማርያም፣
የመጀመሪያ ሴት ልጃቸዉን «እግዚአብሄር የሰጠን ስጦታ» ብለዉ ዮሃና ማለታቸው፣ እግዚአብሄርን
የሚያከብሩ መሆናቸዉን የሚያሳይ ነዉ እንጂ ኤርትራዊ መሆናቸዉን የሚያሳይ አይደለም።
በነገራችን ላይ ኤርትራዊ ናቸው ብለን ብንቀበልም ደግሞ እንኳ ምን ችግር ሊኖረዉ እንደሚችል
አይታየኝም። ዘራይ ደረስ፣ ጄነራል አማን፣ ሞገስ አስግዶም፣ አብርሃም ደቦጭ ኤርትራዉያን ነበሩ።
አሁንም እንደ ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን ያሉ የኢትዮጵያዉያንን እና የኤርትራዉያንን ወንድማማችነት
የሚሰብኩ የሰላም ሐዋርያ የሆኑ ኤርትራዉያን አሉ። እንደ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ያሉ እምነት የለሽ፣
ጨካኝ ግለሰቦች ምክንያት ለሺሆች አመታት የነበረ ዝምድናና አንድነት ረስተን ለኤርትራዉያን
ወንድሞቻችን ጀርባ መስጠት የለብንም።
ኤርትራዉያን ወንድሞቻችን ናቸው። ተዋልደናል፤ ተዛምደናል። ከጥቂት አመታት በፊት ኤርትራ
የኢትዮጵያ ግዛት ነበረች። እግዚአብሄር ከፈቀደም እንደገና ልንገንኝ እንችላለን። ስለዚህ አንድን ሰው
«ኤርትራዊ ነዉ፣ ትግሬ ነዉ፣ ኦሮሞ ነዉ ፣ ከዚህ ዘር ነዉ፣ ከዚህ ጎሳ ነዉ» ከሚል የደም ሃረግ ስንጠቃ
ፖለቲካ መላቀቅ ያለብን ይመስለኛል። አንድ ሰው መመዘን ያለበት በሚሰራዉና በሚናገረው ነገር ብቻ
መሆን አለበት።
አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በሚሰሩትና በሚናገሩት ነገር መመዘን፣ ከአቶ መለስ ጋር የተመሳሰሉ ናቸው
የሚል፣ በማንነትና በዘር ላይ ያተኮረ ሳይሆን፣ በተጨባጭ ፖሊሲዎቻቸው ላይ ያተኮረ አስተያየቶችን
መሰንዘር ፣ አቶ ኃይለማሪያም መቃወምና መተቸት ተገቢ ነዉ። እዚያ ላይ ቅሬታ በፍጹም የለኝም።
አቶ ኃይለማሪያም ጠቅላይ ሚኒስቴር ከሆኑ ጀምሮ የሰጧቸው በርካታ ቃለ መጠይቆችን፣ ያቀረቧቸዉን
በርካታ ንግግሮች አድምጫለሁ። የተናገሩትን በሙሉ ስመዝነዉ፣ እምብዛም አቶ መለስ ከሚናገሩት
የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም። እነ እስክንድር ነጋን የመሳሰሉ ሰላማዊ ዜጎችን፣ «ሁለት ቆብ ያጠለቁ»
ማለታቸው በጣም አስከፍቶኛል። በፓርላማ አቶ ግርማ ሰይፉ ላቀረቡት ጥያቄ የመለሱት መልስ አሳዛኝ
ነዉ። «ሕገ መንግስት አላክብረም ብሎ ነፍጥ ካነሳ ከኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር ጋር ኢሕአዴግ ለመነጋገር
ፍቃደኛ ሆኖ፣ በሕግና በሰላም ከሚንቀሳቀሰው መድረክ ጋር ለመነጋገር ለምን ፍቃደኛ አይሆንም ? »
ብለው አቶ ግርማ ሰይፉ ያልተወሳሰብ ግልጽ ጥያቄ ነዉ የጠየቁት። አቶ ኃይለማርያም የመለሱት መልስ
ግን ዉሃ የማይቋጥር ፣ ከወዲሁ የሚያስገምታቸው፣ አምነዉበት ሳይሆን፣ ምናልባት «ለዚህ አይነቱ ጥያቄ
ይሄን መልስ መስጠት ያስፈልጋል» የሚል ስምምነት ከሥራ ጓዶቻቸው ጋር ስለተስማሙ የመለሱት
መልስ ይመስለኛል። ይህ አይነቱ መልስ ትልቅ ተስፋ ካደረገባቸው ሕዝብ ጋር ከወዲሁ ሊያጋጫቸው
የሚችል እንደሆነም አስባለሁ።
እንደዚያም ሆኖ ግን አሁንም አቶ ኃይለማርያም ከአቶ መለስ በተለየ መልኩ አዎንታዊ ለዉጦች ሊያመጡ
ይችላሉ የሚል ተስፋ አለኝ። ይሄንንም ስል ያለ ምክንያት አይደለም።
በስፋት በአገር ቤት እየተወራ ያለ አንድ ጉዳይ አለ። የቀድሞ የኢትዮጵያ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ አዜብ
መስፋን የአራት ኪሎ ቤተ መንግስትን ለመልቀቅ ፍቃደኛ አለመሆናቸው ነዉ። እንደሰማሁት «ወ/ሮ
አዜብ ሃዘን ላይ ናቸዉ፣ ባለቤታቸውን አጥተዋል » በሚል አቶ ኃይለማርያም ወ/ሮ አዜብን በሃዘኔታ
መጫን አልፈለጉም። «ሕዝቡ እኔን ምንም አያደርገኝም» በሚል ከዚህ በፊት እንደሚያደርጉት አጀባ ሳይበዛ ከቤታቸው ወደ ቢሯችው መመላለስ ፈለጉ። የደህንነት ሃላፊዎች አልተስማሙም። ፕሮቶኮል
ስለሆነ አቶ ኃይለማርያም በሞተር ሳይክሎች እየታጀቡ እንዲሄዱ፣ መንገዶችምን መዝጋት ተጀመረ።
ይሄን ጊዜ አቶ ኃይለማሩያም ««ሕዝቡን ««ሕዝቡን አላንገላታም አላንገላታም»» በሚል፣ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይኖር፣ ጠዋት »»
ከ11 ሰዓት (5 AM ) በፊት ወደ ስራቸዉ ይሄዳሉ፤ ማታ ደግሞ ከሥራቸዉ በጣም አምሽተዉ ይመለሳሉ።
ይህ መሆን ያልነበረበት ቢሆንም የአቶ ኃይለማርያምን ማንነት በትንሹ ሊያሳይ የሚችል ነዉ። እኝህ ሰው
እንዲህ አይነት ሃዘኔታ ለሕዝቡ ካላቸው፣ ከአራት ኪሎ ሕዝቡን የማስጨነቅ፣ የማፈን፣ የማሰር፣
የማንገላታት ነገር ሊያበቃ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ያመላክታል። በፓርላማም ሆነ
በአሜሪካ ድምጽ የተናገሯቸው አንዳንድ አሳዛኝ አባባሎች ቢኖሩም፣ ስልጣናቸዉን በሚገባ
እስኪያረጋግጡ፣ ደህንነቱን እና ወታደራዊ መዋቅሩን የሚቆጠጠሩ ጥቂት የኢሕአዴግ አክራሪ
አመራሮችን ለጊዜዉ ለማለዘብ ሲሉ የተናገሯቸው እንጂ፣ የታሰሩ የሕሊና እስረኞችን ላለመፍታት፣
እንደ መድረክ ካሉ ደርጅቶችም ጋር ላለመነጋገር ከልብ ፍላጎትና ዉሳኔ ኖሯቸው አይመስለኝም። ለዚህም
በተቻለ መጠንም በኢሕአዴግ ዉስጥ ሊኖር የሚችሉትን እንቅፋቶች አልፈው መሄድ እንዲችሉ፣ ትንሽ
ጊዜ ብንሰጣቸዉና ሊጠቅም ይችላል የሚል አስተያየት ያለኝ።
በነገራችን በዚህ አጋጣሚ ላይ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ፣ እያደረጉት ያለው
ነገር፣ የርሳቸዉን ብቻ ሳይሆን የሟቹ የአቶ መለስንም ክብር እያጎደፉ እንደሆነ ለመግለጽ እወዳለሁ።
ወደ ተዘጋጀላቸው ቤት መሄድ ነበረባቸዉ። ከአራት ኪሎ ቤተ መንግስት አልወጣም ማለት
አልነበረባቸዉም። ይህ አቶ ኃይለማሪያምን መናቅ፣ ፓርላማዉን መናቅ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ መናቅ ነዉ።
የደህንነት ሃላፊዎችም ከጅምሩ ይሄን አይነቱ ድራማ እንዲፈጠር ማድረግ አልነበረባቸዉም። ለዚህ ሁሉ
ዉዝግብም ከወ/ሮ አዜብ መስፍን በላይ፣ በቀዳሚነት ተጠያቂ መሆን ያለባቸው እነርሱ ናቸዉ።
አቶ መለስ ዜናዊ ሞተዋል። ወ/ሮ አዜብ የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት እንጂ የአሁኗ ቀዳማዊት እመቤት
አይደሉም። አራት ነጥብ። ከቤተ መንግስቱም በአስቸኳይ መልቀቅ አለባቸዉ። ይሄንን ካላደረጉ የደህንነት
አባላት ሕግን የማስከበር ሃላፊነት አላባቸዉና ሴትየዋን በኋይል የማስወጣት ግዴታ ይጠበቅባቸዋል።
በሚቀጥለዉ ጽሁፌ አቶ ኃይለማርያም በፓርላማ ባቀረቧቸው አንዳንድ ነጥቦች ላይ አስተያየቶችን
በስፋት ይዤ እቀርባለሁ።
እስከዚያዉ ለሁላችንም ቸር ይግጠመን !

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on October 20, 2012 in AMHARIC, ARTICLE

 

Tags: ,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: